Sunday, 01 September 2019 00:00

ከውዝግቦችና ፈታኝ ሥራዎች ጋር የተጋፈጠው ምርጫ ቦርድ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)


- ገለልተኝነት ሲባል ከመንግስት ብቻ ሳይሆን ከተቃዋሚዎችም ነው
- ፓርቲዎች በህጉ ውስጥ የተሻሻለውን ነገር ማየት አይፈልጉም
- የፓርቲዎች ውዝግብ የቦርዱን ሥራ እያጓተተ ነው

        አዲስ የተረቀቀው የምርጫና የፓርቲዎች ህግ ባለፈው ሳምንት በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ጸድቋል፡፡ ሆኖም ከ50 የማያንሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ በተለይ የፓርቲዎች መመስረቻ ህጉን  ክፉኛ ተቃውመውታል፡፡ ሰሚ አላገኙም እንጂ ፓርላማው እንዳያፀድቀው ቀድመው አቤት ብለው ነበር፡፡ የምርጫ ቦርድ በበኩሉ፤ በረቂቅ ሕጉ ላይ ከፓርቲዎች ጋር በቂ ውይይት መደረጉንና ያቀረቡት የማሻሻያ ሃሳቦች ሁሉም ባይሆኑም መካተታቸውን ይገልጻል። “ብዙ ፓርቲዎች እንደገና ስለተከለሰው የሕግ ክፍሉ አይናገሩም፤ ሁሉም አቤቱታቸው በፓርቲዎች ምዝገባ ጉዳይ ላይ ነው” የሚሉት የምርጫ ቦርድ የሕዝብ ግንኙነት አማካሪዋ ሶሊያና ሽመልስ፤ ክርክሩ ግን ለዲሞክራሲ ሂደቱ ጠቃሚ በመሆኑ ችግር የለውም ባይ ናቸው፡፡
ቦርዱ ገና ብዙ ፈታኝ ሥራዎችና ውዝግቦች ይጠብቁታል፡፡ ከመጪው አገራዊ ምርጫ በፊት የሲዳማን የክልልነት ጥያቄ ሕዝበ ውሳኔ ማስፈጸም ይጠበቅበታል፡፡ የፓርቲዎች የእርስበርስ ውዝግቦችንና ንትርኮችን መፍታት ሌላው ዕዳው ነው፡፡ በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የሚመራውና እንደ አዲስ የተዋቀረው ምርጫ ቦርድ በምን አቋም ላይ ነው? እስካሁን ምን ሰራ? ምንስ አቅዷል? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ በቦርዱ አጠቃላይ እንቅስቃሴ ዙሪያ የህዝብ ግንኙነት አማካሪዋን ሶሊያና ሽመልስን እንደሚከተለው አነጋግሯቸዋል፡፡


           ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ወደ ቦርዱ አመራርነት ከመጡ በኋላ ከፓርቲዎች ጋር የተለያዩ ውይይቶች ተደርገዋል፡፡ አዲስ የተዋቀረው ምርጫ ቦርድ ከቀድሞው በምን ይለያል?
የቀድሞው የምርጫ ቦርድ ተከታታይነት ያለው ውይይት ከፓርቲዎች ጋር እያካሄደ፣ የምክክር  መድረክ አያመቻችም ነበር፡፡ ብዙ ጊዜ የፖለቲካ ፓርቲዎችን መቆጣጠር ላይ ነበር የሚያተኩረው:: ፓርቲዎች ከቦርዱ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ከማሻሻል ይልቅ ትኩረቱ ቁጥጥር ላይ  ነበር፡፡ አዲስ የተዋቀረው ቦርድ፤ አገሪቱ ውስጥ ያሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በአንድ መድረክ እንዲወያዩ አድርጓል፡፡ ከዚህ በፊት በነበረው የፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት ላይ በርካቶቹ አይሳተፉም ነበር፡፡ በአሁኑ የጋራ ም/ቤት ግን ሁሉም የሚሳተፉበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ የጋራ የቃል ኪዳን ሰነዱንም ሁሉም ፈርመዋል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎችና የምርጫ ሕጉ በተቃዋሚዎች ዘንድ ለምን አወዛጋቢ ሆነ?
ለምን አወዛጋቢ እንደሆነ እኛ መመለስ አንችልም፡፡ በእርግጥ ሁሉንም አንድ ሕግ ሊያስማማ አይችልም፡፡
ምን ያህል ፓርቲዎች በወጣው ሕግ ተስማምተዋል?
አሁንም መገመት አንችልም፡፡ 139 ፓርቲዎች ናቸው ያሉት፡፡ ከእነዚህ ምን ያህሉ ሕጉን አንብበዋል የሚለው በራሱ ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ የትኞቹ ፓርቲዎችስ ናቸው አንቀጾቹን በትክክል አንብበው ጠቃሚ የሆኑትን የለዩት፤ የሚለውን ዘርዘር አድርጎ ማየት ይፈልጋል፡፡ በድፍኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋዜጣዊ መግለጫ ስለሰጡ፣ ሕጉ ተቀባይነት አላገኘም፤ የሚል ድምዳሜ ላይ እንዳንደርስ መጠንቀቅ አለብን:: አጨቃጫቂ የሚባሉት 10 ሺህ የምስረታ ደጋፊ ፊርማና የመንግስት ሰራተኛን አስመልክቶ የወጡት የሕግ አንቀጾች ናቸው፡፡ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ በቂ ማብራሪያ ተሰጥቶበታል፡፡ 10 ሺህ ፊርማ የማሰባሰብ ዋና አላማው፣ ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲፈጠሩ ነው፡፡ መራጩ ሕዝብ፣ በግልጽ የሚታይ፣ ጠንካራ የፖለቲካ አማራጭ እንዲኖረው ለማድረግ ነው፡፡
ተቃዋሚዎች ቅሬታ ካቀረቡባቸው ድንጋጌዎች ምን ያህሉ ተሻሽለዋል?
10ሺህ የድጋፍ ፊርማ የሚለው አልተሻሻለም፤ እንዳለ ነው፡፡ ነገር ግን ፓርላማ ባፀደቀው ሕግ ላይ የትኛው ተሻሽሏል፣ አልተሻሻለም የሚለውን አሁን አናውቅም፡፡ ሕጉ ተጠንቶ አልደረሰንም፡፡
ፓርቲዎች በጽሑፍ ቅሬታቸውን አቅርበው ነበር:: በጽሑፍ ከቀረቡት ውስጥ ምን ያህሉ ተቀባይነት አግኝተዋል?
ለምሳሌ “መድረክ” ያስገባው ቅሬታ አለ፡፡ የተወሰነው በማሻሻያው ተካቷል፡፡ አንቀበላቸውም የተባሉና የተተው ቅሬታዎችም ይኖራሉ፡፡ የመንግስት ሰራተኛን በተመለከተ ከፓርላማ ሪፖርት እንደተረዳነው፤ በረቂቁ ተካቶ የነበረው ሙሉ ለሙሉ ከሕጉ ተወግዷል፡፡ ይሄን ሕግ እንግዲህ፣ ተቃዋሚዎችም ሆኑ ኢህአዴግ አልወደዱትም:: ስለዚህ ሁሉም ተስማምተው ያስቀሩት ድንጋጌ ነው ማለት ነው፡፡ ከዚህ  ሌላ ፓርላማው ያጸደቀው ቅጂ ገና ስላልደረሰን፣ የትኛው ተካትቷል ወይም አልተካተተም የሚለውን ማወቅ አልቻልንም፡፡
ፓርቲዎቹ፤ ‹‹ሕጉ የተዘጋጀው እኛ ከተነጋገርነው ውጪ ነው›› የሚል ቅሬታም ያነሳሉ…
ለምን እንደዚህ እንደሚባል አይገባኝም፡፡ ሕጉ የተዘጋጀው በጠቅላይ አቃቤ ሕግ ስር ባለ የዴሞክራሲ ጉዳዮችን የሚመለከት የስራ ቡድን ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ባለድርሻ ከሆነው የምርጫ ቦርድም የዚህ ቡድን አባላት አሉ፡፡ በጋራ ነው የተሰራው፡፡ እኔ ለምሳሌ እዚህ ከመቀጠሬ በፊት የዚያ ቡድን አባል ነበርኩ፡፡ ያ የስራ ቡድን ነው ሕጉን ያረቀቀው፡፡ ሕጉ ከመረቀቁ በፊት የቀድሞው ሕግ የነበሩበት ክፍተቶች ምንድን ናቸው? የሚለው ጥናት ተደርጎበታል፡፡ በዚያ ጥናት ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሕግ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡ ከእነሱ በተገኘው ግብአት መሰረት፣ ምንድን ነው መደረግ ያለበት? የሚሉ ውይይቶች ተደርገው፣ ከፓርቲዎችም ከሕግ ባለሙያዎችም ግብአቶች ተወስደዋል፡፡ ከፓርቲዎች ግብአት ይወሰዳል ማለት እነሱ ያሉት በሙሉ ይካተታል ማለት ግን አይደለም:: ገዥው ፓርቲም ተቃዋሚዎችም ግብዓት ይሰጣሉ፡፡ ከአለማቀፍ ልምዶች የሚገኙ ግብአቶችም ተካተው ነው ሕጉ የሚዘጋጀው፡፡ ገለልተኝነት ሲባል ደግሞ ከመንግስት ብቻ ሳይሆን ከተቃዋሚዎችም ገለልተኛ መሆን ያስፈልጋል፡፡ አርቃቂው ቡድን ሁሉንም ግብአቶች መዝኖ ነው ሕጉን ያዘጋጀው፡፡
የፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት፤ ሕጉ ተግባራዊ እንዳይደረግ ተቃውሞ እንደሚያቀርብ ገልጿል፡፡ በዚህ ላይ ቦርዱ ምን ይላል?
ብዙ ፓርቲዎች እንደገና ስለተከለሰው የሕጉ ክፍል አይናገሩም፡፡ ሁሉም አቤቱታቸው በፓርቲዎች ምዝገባ ጉዳይ ነው፡፡ ሕጉ ውስጥ የተቀየረውንና የተሻሻለውን ነገር ማየት አይፈልጉም:: 10 ሺህ ፊርማ የሚለውን ብቻ ነው የሚያነሱት፡፡ እኛ ይሄንን በጣም ዝቅተኛ መስፈርት ነው ብለን ነው የምናምነው፡፡ በሌላ በኩል፤ በርካታ የቀረቡ የማሻሻያ ሀሳቦች በሕጉ ተካተዋል፡፡ ይሄን ግን ፓርቲዎቹ አይጠቅሱም፡፡ ሁሉም የጋራ ም/ቤቱ አባል ፓርቲዎች ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል። በርካታ ሀሳቦቻቸውም ተቀባይነት አግኝቶ በሕጉ ተካቷል፡፡ እነሱ የሚያነሱት ግን አንድ ሁለት ጉዳዮችን ነው፡፡
ሕጉ በጥድፊያ ነው የፀደቀው የሚል ቅሬታም ይደመጣል፡፡ እውነት ተጣድፏል?
ሂደቱ 8 ወር ነው የፈጀው፡፡ ጥናት ተደርጎ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት ተካሂዶ፣ የመጀመሪያው ረቂቅ ፓርላማ ገብቶ፣ እነሱም ለሁለት ጊዜያት በተገኙበት ውይይት ተደርጐ፣ በድጋሚ ግብአቶች ተጨምሮበትና ማሻሻያዎች ታክሎበት ነው የፀደቀው፡፡ እንደውም ረጅም ጊዜ የወሰደ ሂደት ነው፡፡ ይሄን ሕግ ተከትሎ የሚወጡ ገና 40 ያህል መመሪያዎች ይኖራሉ፡፡
ተመዝግበው የቦርዱን እውቅና ማግኘት የሚፈልጉ ወይም የሚጠባበቁ ፓርቲዎች የሚመዘኑት በአዲሱ ህግ ነው ወይስ በነባሩ?
አዲሱ አዋጅ የድሮውን አዋጅ ከሻረው የሚታየው በዚህ ይሆናል ማለት ነው፤ ምናልባት የተለየ መመሪያ ካልወጣ በስተቀር፡፡ ለምሣሌ ከ6 ወር በፊት መስራች ጉባኤ አድርገው፣ የቦርዱን ምዝገባ የሚጠባበቁ ፓርቲዎች፤ እንዴት ይሆናሉ የሚለው ነገር፣ በመመሪያ የሚታይ ሊሆን ይችላል፡፡
ከ57 በላይ ፓርቲዎችና የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት፣ ህጉን በይፋ እየተቃወሙ ባሉበት ሁኔታ፣ እንዴት መተማመን ላይ የተመሰረተ፣ ተቀባይነት ያለው ምርጫ ማካሄድ ይቻላል?
ጭቅጭቁ በጐ አይደለም ብለን አንወስደውም፡፡ ፖለቲካ ሁሌም ክርክር አለው፡፡ የመንግስትን ስልጣን ለመያዝ ጥረት የሚደረግበት ነው፡፡ ሂደቱ በአጠቃላይ አነጋጋሪ መሆኑ አይቀርም፡፡ ጉዳዮቹ በራሳቸው አነጋጋሪ ናቸው፡፡ ክርክሩ መኖሩ የባለድርሻዎቹን የነቃ ተሳትፎ ነው የሚያሳየን፡፡ ሕዝቡ ከዚህ ክርክር የሚወስደው የራሱ ነገር ይኖረዋል ብለን እናስባለን፡፡ ክርክሩም ለዲሞክራሲ ሂደቱ ጠቃሚ ነው ብለን ነው የምናምነው፡፡ የምርጫ ተአማኒነትና ውጤታማነት ደግሞ በምርጫ ቦርድ ላይ ብቻ የተመረኮዘ አይመስለኝም፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ማህበረሰቡ፣ መንግስት፣ ሌሎች አካላትም ኃላፊነት አለባቸው፡፡
ፓርቲዎች በአመራር ውዝግብ፣ በስያሜ ይገባኛልና በመሳሰሉት ጉዳዮች ቅሬታዎች ለቦርዱ ያቀርቡ ነበር፡፡ አሁንስ? እንደ “ኢዴፓ” እና “ኦነግ” ዓይነት ማለቴ ነው…
እውነቱን ለመናገር በፓርቲዎች መካከል በሚፈጠሩ ውዝግቦች እየቀረቡ ያሉ አቤቱታዎች ብዙ ጊዜያችንን እየበሉብን ነው፡፡ የቦርዱን የፖለቲካ ፓርቲ ዲፓርትመንት ስራ በእጅጉ እየፈተኑት ነው:: እነ ኢዴፓ፣ ሲአን… በይፋ የሚታወቁ ቢሆኑም፣ በጣም በርካታ የማይታወቁ ፓርቲዎችም በአመራር ውዝግብ አቤቱታ ያቀርባሉ፡፡ ይሄ በእውነቱ ቦርዱ ሌሎች ስራዎችን እንዳይሠራ እያደረገው ነው፡፡ በተለይ የፓርቲዎች ምዝገባን እንዲሠራ የተቋቋመው የቦርዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዲፓርትመንት፤ የፓርቲዎች ንትርክ ብዙ ጊዜውን እየወሰደበት ነው፡፡
ለእነዚህ ዓይነት ችግሮች በአዲሱ ሕግ የተቀመጠ መፍትሔ የለም?
አንድ በህጉ የተቀመጠ ጉዳይ አለ፡፡ የግልግል ዳኝነትን ለመጠቀም የሚያስችል ህግ ተካትቷል:: አንድ ኮሚቴ ተቋቁሞ በየጊዜው የሚቀርቡ አቤቱታዎችን የሚመለከትና የሚያስማማ ወይም የግልግል ዳኝነት የሚሰጥ ይሆናል፡፡ ህጉ ላይ ያለውን ነገር ከፓርቲዎች ጋር ተወያይቶ፣ እንዴት መሰል ውዝግቦችን መፍታት ይቻላል ለሚለው፣ አንድ መፍትሔ ይገኛል የሚል ግምት አለን፡፡ በጣም ብዙ አቤቱታዎች ናቸው እየቀረቡ ያሉት:: የአመራር ይገባኛል፣ የማህተም መጥፋት፣ የቢሮ ጉዳይ የመሳሰሉ በርካታ አቤቱታዎች ይቀርባሉ፡፡ ይሄ አድካሚ ነው፤ ጊዜም ይፈጃል፡፡ የቦርዱንም ስራ ያጓትታል፡፡
ምርጫ ቦርድ በኢዴፓ ጉዳይ ለእነ አቶ ልደቱ ቡድን የሠጣቸው ምላሽ ምንድን ነው?
ምንም ምላሽ አልሰጣቸውም፡፡
ባለፈው ሳምንት እነ አቶ ልደቱ፣ ‹‹ህጋዊ ኢዴፓዎች ነን›› የሚል መግለጫ ሰጥተዋል…
አይደሉም! የኢዴፓ ጉዳይ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ኢዴፓ ያጋጠመው የአመራር መሰንጠቅ ነው፡፡ በአቶ ጫኔ የሚመራ አመራር ነበር፡፡ ያንን አመራር የፓርቲው ብሔራዊ ም/ቤት፣ ‹‹ከስልጣን አውርጃለሁ›› ብሎ ለምርጫ ቦርድ ደብዳቤ ይጽፋል:: ምርጫ ቦርዱ ደግሞ ‹‹ይህ ብሔራዊ ም/ቤት ትክክለኛ አይደለም›› ብሎ የአቶ ጫኔን መውረድ እንዳልተቀበለ ይገልፃል፡፡
‹‹ብሔራዊ ም/ቤቱ የስም ስህተት አለበት፤ ኮረም አልሞላም›› በሚል ቦርዱ፣ የእነ ዶ/ር ጫኔ አመራር መውረድን አልቀበልም ብሏል፡፡ በኋላ ፍ/ቤትም ሄደው ‹‹ምርጫ ቦርድ የአቶ ጫኔን አመራር የሚያውቀው ከሆነ ማህተምና ጽ/ቤት አስረክቡ›› ይላቸዋል፡፡ ከዚያም ‹‹ኢዴፓ ፈርሷል›› የሚል መግለጫ ይሰጣሉ፡፡ አዲስ ቦርድ ሲቋቋም፤ ‹‹ጉዳዩ እንደገና ይታይልን›› ብለው ደብዳቤ ይዘው ይመጣሉ፡፡ ቦርዱ ግን ያንን ደብዳቤ አይቶ ‹‹አዎ የቀድሞ ቦርድ ውሣኔ ስህተት ነው፤ የእናንተ ነው ትክክለኛው ኢዴፓ›› የሚል ምላሽ አልሰጣቸውም፡፡ ምንም አይነት ውሣኔ አልሰጠም፡፡
እርስዎ በሰጡት መግለጫ ‹‹የተጣለ እግድም ሆነ የሚነሳ እግድ የለም›› ብለዋል፡፡ ምን ማለት ነው?
የተጣለ እግድ የለባቸውማ! ቦርዱ የሚያውቀው የአቶ ጫኔን አመራር ነው ማለት ‹‹እናንተ ታግዳችኋል›› ማለት አይደለም፡፡ ቦርዱ ያገደው አካል የለም ነበር፡፡ ስለዚህ ያነሳው ወይም የሚያነሳው እገዳ የለም ማለት ነው፡፡ ‹‹ቦርዱ የሚያውቀው ትክክለኛ አመራር፤ የአቶ ጫኔን ነው›› ተባሉ እንጂ ‹‹እናንተ ታግዳችኋል ወይም የኢዴፓ አባል አይደላችሁም›› አልተባሉም፡፡ አሁንም በኢዴፓ አመራርነት ቦርዱ የሚያውቀው አቶ ጫኔን ነው፡፡
ቦርዱ እነ አቶ ልደቱን በኢዴፓነት ነው ወይስ በግለሰብነት የሚያውቃቸው?
በግለሰብነት ነው፡፡ ‹‹አቤቱታ ያቀረቡ ግለሰቦች›› ብሎ ነው የሚያውቃቸው፡፡ በነገራችን ላይ የቀድሞው ቦርድ ‹‹ተስማምታችሁ ጠቅላላ ጉባኤ ጥሩና አመራር ምረጡ እንጂ አቶ ጫኔን ለማውረድ ያደረጋችሁት ሙከራ ትክክል አይደለም ነው›› ያላቸው፡፡ እነሱም በጋራ ጠቅላላ ጉባኤ ለመጥራት ተስማምተው ነበር:: ግን ያንን ማድረግ አልቻሉም፡፡ በኋላ ላይ እነ አቶ አዳነ፣ አዲሱ ቦርድ ሲቋቋም ‹‹ጉዳያችን ይታይልን›› የሚል ደብዳቤ ጽፈውልናል፡፡ በየቦታው ‹‹እግድ ተጥሎብናል›› እያሉ ስለነበር፤ ‹‹ምንም አይነት እገዳ የለም›› የሚል ምላሽ ተሰጥቷቸዋል፡፡
ምርጫ ቦርድ የሚያውቀው እነ ዶ/ር ጫኔን ነው ማለት ነው?
አዎ እስካሁን የሚያውቀው የአቶ ጫኔን ቡድን ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሌላ ጉዳይም አለ፡፡ ለምሣሌ የአቶ ጫኔ አመራር ‹‹ኢዴፓን አክስሜያለሁ›› ብሏል:: ነገር ግን አላከሰመም፡፡ ከሰመ የተባለበት ጠቅላላ ጉባኤም ችግር እንዳለበትና ተገቢውን ማስተካከያ እንዲያደርጉ ከቦርዱ ደብዳቤ ተጽፎላቸዋል፡፡ ስለዚህ ‹‹ኢዴፓ ከስሟል›› የሚሉትን ነገር ቦርዱ እስካሁን አልተቀበለም ማለት ነው፡፡ ለቦርዱ መስጠት ያለባቸውን ዝርዝር ጉዳዮች አልሰጡም:: ይሄን አሟሉ ሲባሉም መልስ አልሰጡም፤ ጉዳዩ ተንጠልጥሎ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ ኢዴፓ አልከሰመም፡፡
የኢዴፓን ጉዳይ እንዲህ አጨቃጫቂ ያደረገው ምንድን ነው?
መተዳደሪያ ደንባቸው ነው፡፡ መተዳደሪያ ደንባቸው ከሌሎች ፓርቲዎች በተለየ መልኩ በጣም ጥብቅና አሣሪ ነው፡፡ ከፓርቲው ፕሬዚዳንት በስተቀር በደብዳቤ ላይ ሌላ ሰው መፈረም አይችልም ይላል፡፡ ስለዚህ ከፓርቲው ፕሬዚዳንት ፊርማ ውጪ የመጣን ደብዳቤ ቦርዱ አይቀበልም ማለት ነው፡፡ የበርካታ ፓርቲዎች ችግር የሚመነጨውም ከመተዳደሪያ ደንባቸው ነው፡፡
በቀጣዩ ምርጫ፤ የድምጽ መስጫ ኮረጆ፣ የድምጽ አሰጣጥ ሥርዓትና ቆጠራ ላይ የሚደረግ ለውጥ ይኖራል?
በተወሰነ ደረጃ ይለወጣሉ፡፡ በህጉ ላይም የተቀመጡ ነገሮች አሉ፡፡ ለምሣሌ የድምጽ ኮረጆው ውስጡ በግልጽ የሚታይ (Clear bag) ይሁን ይላል፡፡ ስለዚህ ከዚህ በፊት የነበረውን ለመጠቀም ብንፈልግ እንኳን አንችልም፡፡ በህግ ተከልክለናል ማለት ነው:: በዚህ መሰረት፤ የምርጫ ኮረጆዎች ይቀየራሉ፡፡ ሌላኛው የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ተከታታይ ቁጥር (Serial Number) እንዲኖራቸው ማድረግ ነው:: ከዚህ በፊት ቁጥር የላቸውም፤ ማንም በድጋሚ ሊያትማቸው ይችል ነበር፡፡ ለመጭበርበር ቀላል ነበሩ፡፡ ከሁሉም በላይ ትልቁን በጀት የሚወስድብን የምርጫ አስፈፃሚዎች ምልመላና ስልጠና ነው፡፡ በጀቱን ከፍ ያደረገውም ይሄው ጉዳይ ነው፡፡
የድምጽ መቁጠሪያ ቴክኖሎጂስ?
እሱ በቀጣይ ምርጫ አይኖርም፤ ከፍተኛ በጀት ይፈልጋል፡፡ የመራጮች ዝርዝርን ዲጅታል ማድረግና በወረቀት የተያዙ ሰነዶችን ወደ ዲጂታል መቀየር የመሳሰሉ እቅዶች አሉ፡፡ እነዚህ በራሣቸው ብዙ ነገር ይለውጣሉ፡፡ ከዚህ በፊት ስራዎች ሙሉ በሙሉ በወረቀት ነበር የሚሠሩት፡፡ የተደጋገመ የመራጮች ምዝገባ እንዳያጋጥም፣ የመራጮችን ዝርዝር በዲጂታል መቀየርና ሁሉም ዝርዝሩን እንዲያገኘው ለማድረግ ታቅዷል፡፡
የምርጫ አስፈጻሚዎች ምልመላና ሥልጠና ጀምራችኋል?
የምርጫ አስፈፃሚዎች ምልመላ ጋ ገና አልደረሰንም፡፡ ምልመላችንን እንዴት ማድረግ አለብን የሚለውን ከባለድርሻዎች ጋር እንመክራለን:: ምርጫውን ለማስፈፀም በኛ በኩል በሙሉ ሃይላችን ዝግጅት እያደረግን ነው፡፡

Read 7822 times