Saturday, 31 August 2019 12:44

“ኢትዮጵያን በኢኮኖሚ ከ5 የአፍሪካ ሃያላን አንዷ ለማድረግ እየሰራን ነው” - ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(11 votes)

ኢትዮጵያን በኢኮኖሚ ከ5 የአፍሪካ ሃያል አገራት አንዷ ለማድረግ መንግስት የኢኮኖሚ ሪፎርም በማካሄድ እየሠራ መሆኑን የገለጹት ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት በወጣቶች ስራ ፈጠራ ላይ እንዲያተኩሩ መክረዋል፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ በደቡብ ኮሪያና በጃፓን የነበራቸውን የአራት ቀናት የስራ ጉብኝት ባጠናቀቁበት ወቅት እንደተናገሩት፤ መንግስታቸው ሀገር በቀል የሆኑ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን በመተግበር፣ በኢትዮጵያ ስራ አጥነትን ለመቅረፍና የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ከአፍሪካ ሀገራት የላቀ ለማድረግ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡
አዲስ የተዘጋጀውን የሀገሪቱን የኢኮኖሚ እድገት ማሻሻያ እውን ለማድረግም፣ የጃፓንና የኮሪያ ባለሃብቶች፣ በኢትዮጵያ በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና በማዕድን ማውጣት ዘርፍ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ ከጃፓኑ ጠ/ሚኒስትር ሺንዝዋ አቤ ጋር ባደረጉት ውይይት፤ ኢትዮጵያውያን በጃፓን የስራ እድል እንዲያገኙ ጥያቄ ማቅረባቸውም ታውቋል፡፡ የጃፓኑ ጠ/ሚኒስትርም ሀገራቸው የኢትዮጵያን የለውጥ አጀንዳ እንደምትደግፍ፣ ዶ/ር ዐቢይ ከሀገራቸው አልፈው ለምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ሠላም መስፈን የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ ሀገራቸው ከፍተኛ ግምት እንደምትሰጠው ገልጸዋል፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ሠላም እንዲሰፍን፣ የደቡብ ሱዳን ፀበኞች እንዲታረቁ፣ የሱዳን ችግር በሠላም እንዲፈታ እንዲሁም በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት መካከል መቀራረብና ትምምን እንዲፈጠር ያደረጉትን አስተዋጽኦ ሺንዝዋ አቤ እንደሚያደንቁና የጃፓን መንግስት እውቅና እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል፡፡
ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ፣ በጃፓን ቆይታቸው፣ በ7ኛው አለማቀፍ የቶክዮ የልማት ትብብር (ቲካድ) ጉባኤ ላይ ከመሳተፋቸው ጐን ለጐን፣ ልዩ የአፍሪካ ቀንድ የሠላምና መረጋጋት ስብሰባ ላይ ተገኝተውም ንግግር አድርገዋል:: በዚህ ስብሰባ ላይ የጃፓኑ ጠ/ሚኒስትርን ጨምሮ፣ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት መሃመድ ፋርማጆ፣ የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፣ የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኡስማን ሳላህ፣ የጅቡቲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሐመድ አሊ የሱፍ ተሳትፈዋል፡፡ በስብሰባው ላይ ንግግር ያደረጉት ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ ባደረጉት ንግግርም፤ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በልዩ ሁኔታ በወጣቶች የስራ ፈጠራ ላይ አተኩረው እንዲሰሩ መክረዋል፡፡ በመደመር እሳቤም፣ሀገራቱ ለምስራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ ውህደት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል::
ጠ/ሚኒስትሩ በደቡብ ኮሪያና በጃፓን በነበራቸው ቆይታ፣ ከመንግስት ለመንግስት ግንኙነት ባሻገር፣ ከተለያዩ የአገራቱ ግዙፍ አለማቀፍ ኩባንያዎች ጋር ምክክር ያደረጉ ሲሆን ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ከተጋበዙት ኩባንያዎች መካከል የደቡብ ኮሪያዎቹ የመኪና አምራች ሃይውንዳይና በአሌክትሮኒክስ ምርቶቹ የሚታወቀው ሣምሰንግ ተጠቃሽ ሲሆኑ ፓስኮ የተሰኘው ኮረት አምራች የኮሪያ ኩባንያም በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል:: በተመሳሳይ የጃፓን ኩባንያዎችም በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን በተለይ ቶሺባ የተሰኘው የኢነርጂ ኩባንያ፣ በኢትዮጵያ በጂኦተርማል ኢነርጂ ዘርፍ እንዲሰማራ ጋብዘዋል፡፡  

Read 7621 times