Print this page
Saturday, 31 August 2019 12:45

“በኦሮሚያ ከ6ሺህ በላይ ግለሰቦች ታስረዋል” - ኦፌኮ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(14 votes)

በኦሮሚያ ክልል ባለፈው 1 ዓመት ጊዜ ውስጥ “ለውጡን ለማደናቀፍ ተንቀሳቅሳችኋል፤መንግስትን ተቃውማችኋል” በሚል ከ6ሺህ በላይ ግለሰቦች መታሰራቸውን የኦሮሞ ፌደራል ኮንግረስ (ኦፌኮ) አስታወቀ፡፡
በርካታ የፓርቲውን አመራርና አባላት ጨምሮ ከኢሊባቡር፣ ወለጋ፣ ጉጂና አምቦ አካባቢ ከ6ሺህ በላይ የሚሆኑ ግለሰቦች ተይዘው አምቦ በሚገኘው ሰንቀሌ ማረሚያ ቤት እንደታሰሩ የኦፌኮ ም/ሊቀ መንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ በነቀምት ከተማም፣ 200 ያህል ወጣቶች፣ በታሪካዊው የኩምሣ ሞረዳ ቤተ መንግስት ውስጥ በሚገኝ ወህኒ ቤት መታሰራቸውን ነው አቶ ሙላቱ የገለጹት፡፡
የኦፌኮ አባላትና አመራሮች እንዲሁም ሌሎች ግለሰቦች የታሰሩበትን ምክንያት ፓርቲያቸው ለማጣራት መሞከሩን የጠቆሙት ምክትል ሊቀ መንበሩ፤ በአመዛኙ “ከኦነግ እንቅስቃሴ ጋር በተገናኘ የህግ ማስከበር ስራ ለመስራት ነው” የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ይናገራሉ፡፡
“ይህ የመንግስት ምክንያት አሳማኝ አይደለም” ያሉት አቶ ሙላቱ፤”እስሩ ቀጣዩን አገራዊ ምርጫ ታሳቢ ያደረገ ነው” ብለዋል፡፡
ስለ እስረኞች አያያዝና የእስር ምክንያቶች የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ክትትል እንዲያደርጉ ያሳሰቡት የኦፌኮ ም/ሊቀ መንበሩ፤ “ሂውማን ራይትስዎች” ክትትል ለማድረግ ጠይቆ መከልከሉን እናውቃለን ብለዋል፡፡ የእነዚህን እስረኞች ጉዳይ መንግስት በአስቸኳይ አጣርቶ እንዲፈታ በተደጋጋሚ ብንጠይቅም “የህግ የበላይነትን እያስከበርን ነው” ከሚል ምላሽ ውጪ መፍትሄ አላገኘንም ብለዋል፤አቶ ሙላቱ ገመቹ፡፡  

Read 7493 times