Saturday, 31 August 2019 12:19

የሲዳማ ህዝበ ውሣኔን ተከትሎ የሐዋሳ እጣ ፈንታ እስከ መስከረም መጨረሻ ይታወቃል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)


 - ለህዝበ ውሳኔው ከ75 ሚ. ብር በላይ በጀት ይመደባል
- 8 ሺ 460 የምርጫ አስፈፃሚዎች ይመለመላሉ
- 1 ሺ 692 የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች ይደራጃሉ

             የሲዳማ የክልልነት ህዝበ ውሣኔ ህዳር 3 ቀን 2012 ዓ.ም እንዲካሄድ የወሰነው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ የደቡብ ክልል ም/ቤት የሐዋሳን የወደፊት እጣ ፈንታና የሃብት ክፍፍል አስመልክቶ እስከ መስከረም 22 ቀን 2012 ዓ.ም ውሣኔ እንዲሰጥ ጠይቋል፡፡ የህዝበ ውሣኔ ውጤቱም እስከ ህዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም ይታወቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ህዝቦች ክልል ም/ቤት የሃዋሣን እጣ ፈንታ እንዲሁም የሃብት ክፍፍልና በሲዳማ ዞን የሚኖሩ ሌሎች ብሔረሰቦች ሲዳማ ክልል ሲሆን የሚኖራቸውን መብትና የመብት ጥበቃ አስመልክቶ የህግ ማዕቀፍ እንዲያዘጋጅ ምርጫ ቦርድ ቀደም ብሎ ጠይቆ የነበረ ቢሆንም፣ ም/ቤቱ የተጠየቀውን ለማከናወን ከህገ መንግስቱ በተጨማሪ አስተዳደራዊና ህጋዊ ማዕቀፎችን ማዘጋጀት እንደሚያስፈልገው፣ ያንን ለማከናወን ዞኑ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር ስለሚገኝ አመቺ አይደለም፤ ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጠኝ ባለው መሠረት፤ ቦርዱ እስከ መስከረም 22 ቀን 2012 ዓ.ም እንዲያጠናቅቅ ጊዜ መስጠቱ ታውቋል፡፡
ቦርዱ ህዝበ ውሣኔውን ህዳር 3 ቀን 2012 ዓ.ም ለማስፈፀም፣ ከነሐሴ 30 ቀን 2011 ዓ.ም አንስቶ እንቅስቃሴ እንደሚጀምር ገልጿል፡፡
ቦርዱ፤ ከነሐሴ 30 ቀን ጀምሮ ባሉት ተከታታይ ቀናት፣ ስምንት ሺህ አራት መቶ ስልሳ (8,460) ምርጫ አስፈፃሚዎችን የመመልመል፣ አንድ ሺህ ስድስት መቶ ዘጠና ሁለት (1,692) የድምጽ መስጫ ጣቢያዎችን ማደራጀት፣ የህዝበ ውሣኔ መመሪያዎችን የማውጣትና የድምጽ መስጫ ወረቀቶችን የማተም ስራዎችን እንደሚያከናውን አስታውቋል፡፡
መስከረም 7 ቀን 2012 ዓ.ም የህዝብ ውሣኔ የፀጥታና ደህንነት ጥበቃ እቅድን ከፌደራል፣ ከክልልና ከዞን የፀጥታ አካላት ጋር በጋራ እንደሚያወሳ ቦርዱ አስታውቋል፡፡
ለዚህ ህዝበ ውሣኔ ማስፈፀሚያ የደቡብ ክልል ም/ቤት ሰባ አምስት ሚሊዮን ስድስት መቶ አስራ አምስት ሺህ አስራ አምስት (75,615,015) ብር በጀት አጽድቆ፣ ለቦርዱ እስከ መስከረም 12 ቀን 2012 ዓ.ም እንዲያስረክብም ምርጫ ቦርድ በመግለጫው ያመለከተ ሲሆን የህዝበ ውሣኔ ሂደቱ ህዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅም አስታውቋል፡፡

Read 1817 times