Saturday, 31 August 2019 12:16

የአስቴር አወቀ ‹‹ጨዋ›› ኮንሰርት የፊታችን ረቡዕ በሸራተን ይካሄዳል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 በኮንሰርቱ ላይ 15 ሺህ ሰው ይታደማል ተብሎ ይጠበቃል
                                 
          የእውቋና ተወዳጇ የሶል ንግስት አስቴር አወቀ ‹‹ጨዋ›› ኮንሰርት የፊታችን ረቡዕ (ጳጉሜ 6) ምሽት በሸራተን አዲስ ሆቴል ይካሄዳል፡፡ በዚህ የአዲስ ዓመት ዋዜማማ ኮንሰርት ላይ 3 ሺህ ያህል ቪአይፒና ከ12 ሺህ በላይ መደበኛ በድምሩ ከ15 ሺህ በላይ ሰው ይታደማል ተብሎ እንደሚጠበቅ የኮንሰርቱ አዘጋጅ ኢዮሃ ኢንተርቴይመንትና ኢቨንት ትላንት በሸራተን ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ጠቁሟል፡፡
ድምፃዊቷ ከሰኞ ጀምሮ ከተለያየ ባንድ ከተውጣጡ የሙዚቃ ቡድኖች ጋር ለተከታታይ 10 ቀናት የሚቆይ ልምምድ የምትጀምር ሲሆን ትላንት ከውጭ አገር ወደ ኢትዮጵያ መግባቷም ታውቋል፡፡ የዘመን መለወጫን ምክንያት በማድረግ ተወዳጇን የሶል ንግስት ከደማቅ የርችት ሥነ ሥርዓት ጋር ለኢትዮጵያ ሕዝብ እናቀርባለን ያሉት የኢዮሃ ኢንተርቴይመንትና ኢቨንት ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ አዩ አለሙ፤ ከዋሊያ ቢራ ጋር በመተባበር ደረጃውን እንዲጠብቅ ደፋ ቀና እያሉ መሆናቸውን ጨምረው ገልጸዋል፡፡ የአስቴር አወቀን ኮንሰርት በማዘጋጀታችን ዕድለኝነትና ክብር ይሰማናል ብለዋል - ወ/ሮ አዩ፡፡
በዚህ ኮንሰርት 15 ሺህ ያህል ትኬቶች የተዘጋጁ ሲሆን በዳሽን ባንክ አሞሌ በሁሉም ቅርንጫፍ፣ የአስቴርን አልበም ሽያጭ ሲያከናውን የነበረው ‹‹ደራሽ›› የተባለ ድርጅት ባዘጋጃቸው በክልል 17፣ በአዲስ አበባ 250 ኤጀንቶች እንዲሁም በሸራተን ሆቴል፣ በማሪዮት ሆቴል፣ በፒዛ ሀት፣ በሮሚና ሬስቶራንት፣ በዋው በርገርና በሩሚ በርገር ለሽያጭ መቅረባቸውን የደራሽ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ወጣት አለማየሁ ወርቅ እሸት ጠቁሞ አንድ ሰው ትኬቱን ሲገዛ ትኬቱ ከጀርባው QR ኮድ መኖሩን፣ ለሻጭ ስምና ስልክ ቁጥር መስጠት እንዳይረሳ አሳስቧል።  
በኮንሰርቱ ላይ ወጣቷ ድምፃዊት ራሄል ጌቱና ወንዲ ማክ ከአስቴር አወቀ ጋር ምሽቱን የሚይደምቁት ሲሆን ‹‹የተመስገን ልጆች›› የዳንስ ቡድን 6 ያህል ዘፈኖችን ለማጀብ ከፍተኛ የኬሪዮግራፊ ስልጠና እየወሰዱ መሆኑም ታውቋል፡፡ የመግቢያ ዋጋ ለቪአይፒ አራት ሺህ ብር ሲሆን አፕን የእራት ግብዣ (ብፌ)፣ የእንኳን ደህና መጣችሁ ልዩ መጠጥ፤ ብላክ ሌብል፣ ሬድ ሌብል፣ ዊንተር ፓላስ፣ ቮድካ፣ ጎርደን ጅን፣ ቢራ፣ የአገር ውስጥ ወይኖችና ለስላሳ መጠጦች ያካትታል ተብሏል፡፡ መደበኛው ደግሞ ስምንት መቶ ብር ሲሆን ሶስት ዋልያ ቢራ፣ ውሃና ለስላሳ  መጠጥን እንደሚያካትት ታውቋል፡፡
የርችት ማብራት ሥነ ሥርዓቱን አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡትና በዘርፉ የዳበረ ልምድ ያለው የወዛም ኮሚዩኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ፀጋዬ ተክሉ እስካሁን የርችት ደረጃ

በዓለም ላይ 11G (አስራ አንደኛው ጀነሬሽን) ላይ መድረሱን ጠቁመው፤ ድርጅታቸው በኢትዮጵያ ደረጃውን 4Gt (ከአራተኛው ትውልድ በላይ) ማድረስ መቻሉንና በኮንሰርቱም ላይ 4 Gt ደረጃ ያለውና የ20 ደቂቃ ርዝማኔ የሚኖረው የርችት ማብራት ሥነ ሥርዓት እንደሚከናወን አስታውቀዋል፡፡
የሶል ንግስቷ የአስቴር አወቀ ማናጀር ወ/ሮ አዳነች ውለታ በበኩላቸው፤ አስቴር የአዲስ ዓመት ዋዜማ ኮንሰርቱን ከአገሯ ልጆች ጋር ለማሳለፍ በእጅጉ ጓጉታለች፤ ለጥናት የተመረጡ ከ30 በላይ ዘፈኖችም ተዘጋጅተዋል፤ አስቴር መድረክ ላይ ስትወጣ በአንዴ አስርና ከዚያ በላይ የመጫወት አቅምና ፍላጎት ስላላት ሳትጠግቧት እንደማትለያዩ እርግጠኛ ነኝ” ብለዋል፡፡ ‹‹ጨዋ›› ከተሰኘው አዲሱ አልበምም 4 ዘፈኖቿ ለጥናት መቅረባቸውን ጨምረው ገልፀዋል፡፡
አስቴር በአዲስ አበባ ተገድባ እንዳትቀር በየክልሉ ከተሞች ኮንሰርት ለማዘጋጀት ኢዮሃ ከዋልያ ጋር እየተነጋገረ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ዋልያ ቢራ የአንጋፋዋንና የተወዳጇን ድምጻዊት አስቴር አወቀን ኮንሰርት ስፖንሰር በማድረጉ ኩራት እንደሚሰማው በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የተገኙት የሄይንከን የሕዝብ ግንኙነት ሀላፊ ወ/ሮ ሰራዊት በዛብህ ተናግረዋል፡፡ የድምፃዊ ወንደሰን መኮንን (ወንዲ ማክ) ተወካይ ሙዚቀኛ ታደለ ከፍያለው በበኩሉ፤ ወንዲማክ አልበም ሳያወጣ ኮንሰርት ላለመስራት ወስኖ ነበር፤ ለአስቴር ኮንሰርት ጥሪ ሲቀርብለት ግን አለመቀበል አልቻለም፤ በከፍተኛ ደስታም እየተዘጋጀ ነው ብሏል፡፡


Read 1362 times