Print this page
Saturday, 31 August 2019 12:12

በ12ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

    • ኢትዮጵያ እስከትናንት ድረስ በ21 ሜዳልያዎች (6 የወርቅ፤ 4 የብርና 11 የነሐስ ሜዳልያዎች)
    • 26 የስፖርት አይነቶች ፤ 341 የውድድር መደቦች ፤ 53 የአፍሪካ ብሄራዊ ኦሎምፒክ ኮሚቴዎች ፤ 4386 አትሌቶች
    • በ2023 እኤአ ላይ በ13ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች በጋና፤ አክራ ላይ ይቀጥላል
    • ባለፉት 11 የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ 151 ሜዳልያዎች (39 የወርቅ፤ 49 የብርና፤ 63 የነሐስ ሜዳልያዎች) በምንግዜም ከፍተኛ           የሜዳልያ ስብስብ 10ኛ

     ባለፈው ሳምንት በሞሮኮ ዋና ከተማ ራባት የተጀመረው 12ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች ነገ የሚፈፀም ሲሆን፤ ኢትዮጵያ እስከትናንት ድረስ በ19 ሜዳልያዎች (6 የወርቅ፤ 5 የብርና 10 የነሐስ ሜዳልያዎች) በ9ኛ ደረጃ ላይ ናት፡፡ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጨዋታዎቹ ላይ 176 ስፖርተኞችን በ12 የስፖርት መደቦች እያወዳደረች ሲሆን እነሱም የአትሌቲክስ፤ ባድሜንተን፤ ቦክስ፤ ብስክሌት፤ ቼዝ፤ ጅምናስቲክ፤ ካራቴ፤ ውሃ ዋና፤ ጠረጴዛ ቴኒስ፤ ሜዳ ቴኒስ፤ ቴክዋንዶና ክብደት ማንሳት ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቶች በሁለቱም ጾታዎች በ10ሺና 5ሺ ሜትር፤ በ3ሺ ሜትር መሰናክል፤ በቴክዋንዶ፤ በብስክሌት እንዲሁም በሴቶች ግማሽ ማራቶን አበረታች ውጤቶች ማስመዘገባቸው በ2020 እኤአ የጃፓኗ ቶኪዮ ከተማ ለምታስተናግደው 32ኛው ኦሎምፒያድ ተስፋ የሚሰጥ ይሆናል፡፡
የአፍሪካ ጨዋታዎች በሞሮኮ ራባት
 በ26 የስፖርት አይነቶች እና 341 የውድድር መደቦች በሚካሄዱበት 12ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች ላይ 54 የአፍሪካ ብሄራዊ ኦሎምፒክ ኮሚቴዎችን የወከሉ 4386 አትሌቶች እየተሳተፉ ናቸው:: የተሳታፊዎቹ ብዛት በውድድሩ ታሪክ አዲስ ክብረወሰን ሲሆን አዘጋጇ ሞሮኮ የውድድሩ መስተንግዶ በማግኘት ወደ የአፍሪካ ጨዋታዎች የተመለሰችው ከ32 ዓመታት በኋላ ነው፡፡ የአፍሪካ ህብረት ሞሮኮን ከ8 የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ተሳትፎ አግዷት የነበረ ሲሆን ዋናው ምክንያት  ከምዕራብ ሳሃራ ጋር በገባችው የድንበር ግጭት ነበር:: በ2017 እኤአ ላይ ሞሮኮ በጉዳዩ ላይ ከአፍሪካ ህብረት ጋር የህብረት ስምምነት ከፈፀመች በኋላ ወደ ውድድሩ  በአዘጋጅነት እንድትመለስ ተፈቅዶላታል፡፡ ሞሮኮ የአፍሪካ ጨዋታዎችን መስተንግዶ ከ1 ዓመት በፊት ልታገኝ የበቃችው 33ኛውን ኦሎምፒያድ በ2024 እኤአ በአፍሪካ አህጉር በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ለማስተናገድ ያደረገችው ጥረት ካልተሳካላት በኋላ ነው፡፡ በመጀመርያ 12ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎችን  እንድታዘጋጅ እድል ተሰጥቷት የነበረችው የኢኳቶርያል ጊኒ ዋና ከተማ ማላቦ ከተማ ስትሆን በበጀት እጥረት ተሳትፎውን ለመተው ተገድዳለች፡፡  የሞሮኮ ንጉስ መሐመድ አምስተኛ የበላይ ጠባቂ ሆነው የአፍሪካ ጨዋታችን በ6 ከተሞች ማለትም በዋና ከተማዋ ራባት፤ ሳሌ፤ ቴማራ፤ ካዛብላንካ፤ ቤንስሊማኔና ኤል ጃዲዳ ከተሞች ለማስተናገድ ችላለች፡፡ በራባት የሚገኘው ዓለም አቀፍ ዩኒቨርስቲ በአፍሪካ ጨዋታዎቹ ላይ 4ሺ አትሌቶችን የሚያስተናግደውን መንደር ያቀረበ ሲሆን ቀሪዎቹ ተሳታፊዎች ቆይታቸው በካዛብላንካ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ራባት የወንዶች እግር ኳስ፤ አትሌቲክስ፤ ካራቴ፤ ጁዶ፤ትራይተሎን መረብ ኳስ በቤት ውስጥና የባህር ዳርቻ እንዲሁም 3 በ3 የቅርጫት ኳስ ውድድሮችን የምታስተናግድ ከተማ ሲሆን የቦክስ እና ሻሞላ ውድድሮች በሳሌ ከተማ፤ የሴቶች እግር ኳስ በኬኒተራ ፤ እጅ ኳስ፤ ዋና፤ ብስክሌት በካዛብላንካ እንዲሁም ነፃ ትግል በኤል ጃዲዳ ከተሞች እንዲስተናገዱ ሆኗል፡፡ በአፍሪካ ጨዋታዎቹ ላይ የጂምናስቲክ ውድድር በሞሮኮ በድጋሚ እንዲጀመር በመወሰኑም ውድድሩ በራባት ከተማ የተካሄደ ነው፡፡
በ12ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች ላይ ኬንያ እና ኢትዮጵያ በመካከለኛ እና በረጅም ርቀት የአትሌቲክስ ውድድሮች የበላይነት እንደሚያሳዩት ሁሉ በመረብ ኳስ ካሜሮን፤ ኬንያና ግብፅ፤ በቀስት ውርወራ ግብፅ እና ደቡብ አፍሪካ፤ በጅምናስቲክ አልጄርያ፤ ደቡብ አፍሪካ እና ናይጄርያ፤ በክብደት ማንሳት ግብፅ፤ ቱኒዚያና ናይጄርያ፤ በነፃ ትግል ደቡብ አፍሪካ ናይጄርያ፤…. የሜዳልያ ስብስባቸውን አብዝተዋል፡፡ 12ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች  በውድድሩ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜወደ ኦሎምፒክ ለማለፍ የማጣርያ መድረክ ሊሆን መብቃቱ የፉክክር ደረጃውን አሳድጎታል:: በውድድሩ ላይ ከሚካሄዱ 26 የስፖርት መደቦች መካከከል በ17   ውድድሮች በ2020 እኤአ ላይ ቶኪዮ ለምታስተናግደው 32ኛው ኦሎምፒያድየሚያሳልፍ ውጤት ይመዘገብባቸዋል፡፡ የአፍሪካ ጨዋታዎች ከአትሌቲክስ ስፖርት ባሻገር በሌሎች  የስፖርት አይነቶች ወደ ኦሎምፒክ ለመሸጋገገር የሚያመች የውድድር መድረክ ከመሆኑም በላይ አፍሪካ በስፖርቱ ላይ ያሏትን  አዳዲስ ስፖርተኞች ለማውጣት፤ በትልልቅ የስፖርት መድረክ መስተንግዶና የመሰረተልማት አቅም ያላትን አቅም ለማሳየት እንዲሁም  አህጉራዊ አንድነትና መነሳሳትን ለመፍጠር ያግዛል፡፡
ከፍፃሜው በፊት የኢትዮጵያ ውጤቶች
በ12ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች ላይ ከፍፃሜው በፊት ለኢትዮጵያ 6 የወርቅ ሜዳልያዎችን ያስገኙት በቴክዋንዶ በወንዶች 63 ኪግ ታሪኩ ግርማ ደምሱ፤ በወንዶች 10ሺ ሜትር ብርሃኑ ወንድሙ፤ በሴቶች 800 ሜትር ሂሩት መሸሻ፤ በሴቶች 3ሺ ሜትር መሰናክል መቅደስ አበበ፤ በሴቶች 10ሺ ሜትር ፀሃይ ገመቹና በሴቶች ግማሽ ማራቶን የአለም ዘር የኋላው ናቸው፡፡ 5 የብር ሜዳልያዎች ያስመዘገቡት  በወንዶች 3ሺ ሜትር መሰናክል ጌትነት ዋለ፤ በሴቶች 5ሺ ሜትር ሃዊ ፈይሳ፤ በወንዶች 20 ኪሜ ዮሐንስ አልጋው፤ አበበ፤ በሴቶች 10ሺ ሜትር ዘይነባ ይመር ፤ በሴቶች ግማሽ ማራቶን ደጊቱ አስመራው ሲሆኑ፤ 11 የነሐስ ሜዳልያዎች ያስመዘገቡት ደግሞ በቴክዋንዶ 53 ኪሎ በታች ፀባኦት ተስፋዬ፤በሱሉስ ዝላይ አርያት ዲቦ፤ ሰለሞን ቱፋ ከ54 ኪሎ በታች ፤ በሴቶች ቡድን የታይም ትራየል ፤ በሴቶች 5ሺ ሜትር አለሚቱ ታሪኩ፤በወንዶች 10ሺ ሜትር ጀማል ይመር፤በወንዶች 20 ኪሜ የርምጃ ውድድር ዮሃልዬ በለጠው፤ በሴቶች 3ሺ ሜትር መሰናክል ወንሸት አንሳ አበበ፤ በሴቶች 10ሺ ሜትር ደራ ዲዳ፤ በሴቶች ግማሽ ማራቶን መሰረት በለጠ ናቸው፡፡
ከፍፃሜው በፊት የሜዳልያ ደረጃ
በ12ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች ላይ ከፍፃሜው በፊት  በአጠቃላይ የሜዳልያ ደረጃ ግብፅ በ229 ሜዳልያዎች(79 የወርቅ፤ 87 የብርና 63 የነሐስ ሜዳልያዎች) በመሰብሰብ እየመራች ሲሆን ፍፁም የበላይነት ያሳየችው በተለይም በዋና፤ በእጅ ኳስ፤ በጁዶ፤ በቢሊያርድና ሌሎች ስፖርቶች የላቁ ስፖርተኞችን በማሰለፏ ነው፡፡  እስከትናንት ድረስ ባገኙት የወርቅ ሜዳልያ ብዛት በወጣው ደረጃ መሰረት ናይጄርያ በ103 ሜዳልያዎች(40 የወርቅ፤ 28 የብርና 35 የነሐስ ሜዳልያዎች)፤ ደቡብ አፍሪካ በ77 ሜዳልያዎች(32 የወርቅ፤ 24 የብርና 21 የነሐስ ሜዳልያዎች)፤ አልጄርያ በ113 ሜዳልያዎች(31 የወርቅ፤ 27 የብርና 55 የነሐስ ሜዳልያዎች)፤ ሞሮኮ በ93 ሜዳልያዎች(27 የወርቅ፤ 26 የብርና 40 የነሐስ ሜዳልያዎች)፤ ቱኒዚያ በ79 ሜዳልያዎች(23 የወርቅ፤ 28 የብርና 28 የነሐስ ሜዳልያዎች)፤ ሞሪሽየስ በ24 ሜዳልያዎች(6 የወርቅ፤ 6 የብርና 12 የነሐስ ሜዳልያዎች)፤ ማዳጋስካር በ12 ሜዳልያዎች(6 የወርቅ፤ 4 የብርና 2 የነሐስ ሜዳልያዎች) የኢትዮጰያን ሰባተኛ ደረጃ ጨምሮ እስከ ዘጠነኛ ደረጃ አከታትለው ሲይዙ ፤ የኢትዮጵያ የቅርብ ተቀናቃኝ የሆነችው ኬንያ በ18 ሜዳልያዎች (4 የወርቅ፤ 6 የብርና 8 የነሐስ ሜዳልያዎች) 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡ በሌላ በኩል በሻምፒዮናው ከተሳተፉ 53 አገራት ከፍፃሜው በፊት 37 አገራት አንድና ከዚያም በላይ ሜዳልያ በመሰብሰብ የደረጃ  ዝርዝር ውስጥ ገብተዋል፡፡
የአህጉራዊው የስፖርት መድረክ የታሪክ
ሂደት እና አዘጋጆቹ
አሁን የአፍሪካ ጨዋታዎች African Games የተባለውና አስቀድሞ ላለፉት 53 ዓመታት የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች All-Africa Games ወይም የፓን አፍሪካ ጨዋታዎች Pan African Games የሚካሄደው እንደ ኦሎምፒክ በአየአራት ዓመቱ ነው፡፡ በትብብር የሚያዘጋጁት የአፍሪካ ብሄራዊ ኦሎምፒክ ኮሚቴዎች ማህበር Association of National Olympic Committees of Africa (ANOCA)  እና  የአፍሪካ ስፖርት ኮንፌደሬሽኖች ማህበር Association of African Sports Confederations (AASC) ናቸው:: በርካታ የስፖርት ውድድሮችን የሚያካትተው እና እንደ አህጉራዊ ኦሎምፒክ የሚታየውን የስፖርት መድረክ ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ እን የኤሽያ ጨዋታዎች Asian Games እና እን ፓን አሜሪካን ጨዋታዎች  and Pan American Games እውቅና የሰጠው ሲሆን ከ1999 እኤአ ጀምሮ አካል ጉዳተኛ አትሌቶች በፓራ ጌምስ እንዲሳተፉ አድርጓል፡፡
የአፍሪካ ጨዋታዎችን በሙሉ ሃላፊነት ሲያዘጋጅ የቆየው አህጉራዊ ተቋም ደግሞ የአፍሪካ ስፖርት የላዕላይ ምክር ቤት The Supreme Council for Sport in Africa (SCSA) የነበረ ሲሆን ከ6 ዓመታት በፊት በአይቬሪኮስቷ ከተማ አቢጃን ላይ የአፍሪካ የስፖርት ሚኒስትሮች ለአምስተኛ ጊዜ በአፍሪካ ህብረት ስር ባደረጉት ኮንፍረንስ የአፍሪካ ስፖርት የላዕላይ ምክር ቤትን በማፍረስ ያሉትን አደረጃጀቶች፤ ንብረቶች እና ሌሎች ሃላፊነት ወደ አፍሪካ ህበረት ኮሚሽን እንዲያስተላልፍ ወስነዋል፡፡ ስለሆነም የአፍሪካ ጨዋታዎችን በባለቤትነት የአፍሪካ ህብረት ሲይዘው፤ የአፍሪካ ብሄራዊ ኦሎምፒክ ኮሚቴዎች ማህበር (ANOCA) የቴክኒክ ሂደቱን እንዲሁም የአፍሪካ ስፖርት ኮንፌደሬሽኖች ማህበር (AASC) ደግሞ የማርኬቲንግ ፖሊሲ፤ የስፖንሰርሺፕ እንዲሁም የጥናትና ምርምር ስራዎችን በሃላፊነት የሚያስተዳደሩ ሆነዋል፡፡
ከ12ኛው በፊት ከ1965 እኤአ ጀምሮ እስከ 2015 እኤአ አህጉራዊው ውድድር ለ11 ግዚያት የተካሄደው  የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች በሚለው ስያሜ ነበር:: በ2012 እኤአ ላይ የአፍሪካ ህብረት በአዲስ አበባ ባካሄደው ጉባኤ የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች የሚለው የአፍሪካ ጨዋታዎች በሚል ስያሜ የወሰነ ሲሆን በ2019 እኤአ ላይ ውድድሩ በሞሮኮ ራባት ሲካሄድ 12ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች በሚል ሆኗል:: በነገራችን ላይ ተመሳሳይ አህጉራዊ የበርካታ ስፖርቶች የውድድር በመድረክን ለአፍሪካ በመፍጠር ግንባር ቀደም የነበሩት ፈረንሳዊው የኦሎምፒክ መስራች ፒዬር ደ ኩበርቲን ነበሩ፡፡ ፒየር ደ ኩበርቲን በ1920 እኤአ ላይ ፓን አፍሪካን ጌምስ ውድድርን ለመጀመር ሃሳቡን ቢጠነሰሱም በወቅቱ ቅኝ ገዢ አገራት የስፖርት መድረኩ አፍሪካውያንን በአንድነት የሚያስተሳስር እና ለነፃነታቸው እንዲታገሉ ያነሳሳል በሚል ስጋት ተግባራዊ እንዳይሆን አድርገውታል፡፡ ከፒየር ደኩበርቲን በኋላ በ1925 እኤአ ላይ አልጄርያ በዋና ከተማዋ አልጀርስ እንዲሁም በ1928 አኤአ ላይ ግብፅ በአሌክሳንድሪያ ከተማ ተመሳሳይ አህጉራዊ የስፖርት መድረክ ለማካሄድ በሙሉ ዝግጁነት ቢንቀሳቀሱም ማካሄድ አልሆነላቸውም፡፡ በዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ የመጀመርያው አፍሪካዊ አባል የነበረው፤ በትውልዱ ከግሪክ ቢሆንም የግብፅ የአጭር ርቀት ሯጭ የነበረው አንጀሎ ቦላንናኪ ሁለገብ የስፖርት ስታድዬም እንዲገነባ  ገንዘብ ቢደግፍም ለቀጣይ 30 ዓመታት የስፖርት መድረኩን በአፍሪካ እውን ማድረግ ሳይቻል ቀረ፡፡ በ1960ዎቹ መግቢያ ላይ ደግሞ በፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪ የአፍሪካ አገራት እና በፈረንሳይ ትብብር አህጉራዊውን የስፖርት መድረክ ፍሬንድሺፕ ጌምስ  Friendship Games በሚል ስያሜ ለመሰካሄድ ተወስኖ በ1960 እኤአ ላይ ማዳጋስካር እንዲሁም በ1961 እኤአ ላይ ኮትዲቯር አዘጋጁ፡፡ በ1963 አኤ ላይ ሶስተኛው የፍሬንድሺፕ ጌምስ በምዕራብ አፍሪካዋ ሴኔጋል ከመካሄዱ አንድ አመት ቀደም ብሎ በ1962 እኤአ ላይ የአፍሪካ ስፖርት ሚኒስትሮች በፓሪስ ባደረጉት ጉባኤ የስፖርት መድረኩ እንግሊዘኛ የሚናገሩ ሌሎች የአፍሪካ አገራትን በማካተት እንዲካሄድ መክረው ስያሜውንም ወደ ፓን አፍሪካን ጌምስ እንዲቀየር አደረጉ፡፡ ይሄው አህጉራዊ የስፖርት መድረክም ከ1965 እኤአ ጀምሮ በዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ እውቅና በማግኘት መካሄድ ጀመረ፡፡
የመጀመርያው አዘጋጅ በ1965 እኤአ ላይ ኮንጎ በዋና ከተማዋ ብራዛቪል ነበር፡፡ በ1ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች ላይ 30 አገራትን የወከሉ 2500 አትሌቶች ሊሳተፉ በቅተዋል፡፡ በ1969 እኤአ ላይ ሁለተኛውን የአፍሪካ ጨዋታዎች ማሊ በባማኮ ከተማ እንድታዘጋጅ ቢወሰንም በአገሪቱ ላይ በተከሰተው መፈንቀለ መንግስት አዘጋጅነቱን በ1971 እኤአላይ ናይጄርያ በሌጎስ እንድታስተናግደው ተለልፎ ተሰጠ፡፡ ይሁንና በነማይጄርያ በነበረው የርስበርስ ጦርነት ሁለተኛው የአፍሪካ ጨዋታዎችን ሌጎስ ያስተናገደችው በ1973 እኤአ ሆነ፡፡ ከዚያ በኋላ በ1977 እኤአ ላይ 3ኛውን የአፍሪካ ጨዋታዎች እንድታዘጋጅ ለአልጄርያ እድሉ ተሰጥቷት በቴክኒካዊ ችግሮች  ሳቢያ ለማስተናገድ የበቃችው በ1978 እኤአ ላይ ነበር፡፡ አራተኛውን የአፍሪካ ጨዋታዎች በ1983 እኤአ ላይ የምስራቅ አፍሪካዋ ኬንያ እንድታዘጋጅ እድሉ ሲሰጣትም በመጀመርያ መስተንግዶውን ወ1985 ካራዘመች በኋላ የተሳካላት በ1987 እኤአ ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ የአፍሪካ ጨዋታዎቹን ካይሮ፤ ሃራሬ፤ ጆሃንስበርግና የአቡጃ ከተሞች ሊያስተናግዱ በቅተዋል፡፡ በ2007 እኤአ ላይ አልጄርያ ለሁለተኛ ጊዜ የአፍሪካ ጨዋታዎችን በማስተናገድ የመጀመርያዋ አፍሪካዊ አገር ሆነች:: በ2011 እኤአ ላይ 10ኛው የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች በሞዛምቢክ ማፑቱ ተካሄደና የአፍሪካ ጨዋታዎቹን 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ ምክንያት በማድረግ የኮንጎዋ ብራዛቪል ከተማ 11ኛውን የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች አስተናግዳለች፡፡ ሞሮኮ በ2019 እኤአ ላይ 12ኛውን የአፍሪካ ጨዋታዎች ካስተናገደች በኋላ በ2023 እኤአ ላይ 13ኛውን የአፍሪካ ጨዋታዎች ጋና እንደምታዘጋጅ ታውቋል፡፡
ባለፉት 11 የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች
ከ12ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች በፊት ከ1965 እኤአ ጀምሮ እስከ 2015 እኤአ በተካሄዱት 11 የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች በምንግዜም ከፍተኛ የሜዳልያ ስብስብ በውድድሩ ከሚሳተፉ 54 የአፍሪካ ብሄራዊ ኦሎምፒክ ኮሚቴዎች 50ዎቹ በተሳተፉባቸው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ቢያንስ አንድ ሜዳልያ እና ከዚያም በላይ በላይ አስመዝግበዋል፡፡ በተጨማሪ በ11 የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ላይ አንድ እና ከዚያም በላይ የወርቅ ሜዳልያ ያገኙ አገራት ደግሞ 42 ናቸው:: በሌላ በኩል አህጉራዊ የስፖርት መድረኩ የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች በሚል  ሲያሜ እስከ 2015 እኤአ ለ11 ጊዜያት ሲካሄድ የሜዳልያ ሰንጠረዡን በአንደኝነት በመቆጣጠር ግብፅ ለአምስት ጊዜያት ሲሳካላት ደቡብ አፍሪካ በ3 አንደኛ ነበረች፡፡
ከ12ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች በፊት በተካሄዱት 11 የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች 6317 ሜዳልያዎች(1984 የወርቅ፤ 1940 የብርና፤ 2393 የነሐስ ሜዳልያዎች) ለአሸናፊዎቻቸው የተሸለሙ ሲሆን በምንግዜም ከፍተኛ የሜዳልያ ስብስብ የደረጃ ሰንጠረዥ ላይ በአንደኛ ደረጃ የተቀመጠችው በ11 የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች በመሳተፍ 1362 ሜዳልያዎች(548 የወርቅ፤ 406 የብርና፤ 408 የነሐስ ሜዳልያዎች) የሰበሰበችው ግብፅ ናት፡፡ ናይጄርያ በ11 የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች በመሳተፍ 1199 ሜዳልያዎች(424 የወርቅ፤ 395 የብርና፤ 380 የነሐስ ሜዳልያዎች)፤ ደቡብ አፍሪካ በ6 የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች በመሳተፍ 967 ሜዳልያዎች(361 የወርቅ፤ 336 የብርና፤ 270 የነሐስ ሜዳልያዎች)፤ አልጄርያ በ11 የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች በመሳተፍ 897 ሜዳልያዎች(277 የወርቅ፤ 280 የብርና፤ 340 የነሐስ ሜዳልያዎች) እንዲሁም ቱኒዚያ በ11 የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች በመሳተፍ 684 ሜዳልያዎች(234 የወርቅ፤ 208 የብርና፤ 242 የነሐስ ሜዳልያዎች) በማግኘት በከፍተኛ የሜዳልያ ስብስባቸው ከ2 እስከ 5ኛ ደረጃ ላይ ተከታትለው ተቀምጠዋል፡፡
በኦሎምፒክ መድረክ የአፍሪካ ከፍተኛ ውጤት የሚያስመዘግቡት እና በመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ላይ በአትሌቲክ ስፖርት ከፍተኛ የሜዳልያ ስብስብ የሚኖራቸው ኬንያ እና ኢትዮጵያ ከ12ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች በፊት በተሳተፉባቸው 11 የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች በሜዳልያ ስብስባቸው  እስከ 10ኛ ባለው ደረጃ ቢገቡም በመካከላቸው ከፍተኛ ልዩነት ይስተዋላል፡፡
ኬንያ በ11 የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች በመሳተፍ 411 ሜዳልያዎች(123 የወርቅ፤ 134 የብርና፤ 114 የነሐስ ሜዳልያዎች) በማግኘት ከ12ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች በፊት በምንግዜም ከፍተኛ የሜዳልያ ስብስብ 6ኛ ደረጃ ላይ ስትጠቀስ፤ ሴኔጋል በ11 የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች በመሳተፍ 267 ሜዳልያዎች(64 የወርቅ፤ 66 የብርና፤ 137 የነሐስ ሜዳልያዎች) ፤ ካሜሮን በ11 የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች በመሳተፍ 220 ሜዳልያዎች(36 የወርቅ፤ 56 የብርና፤ 128፤ ጋና በ11 የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች በመሳተፍ 172 ሜዳልያዎች(34 የወርቅ፤ 52 የብርና፤ 86 የነሐስ ሜዳልያዎች) እስከ9ኛ ደረጃ ሲወስዱ ኢትዮጵያ ከ12ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች በፊት በ11 የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች በመሳተፍ 151 ሜዳልያዎች(39 የወርቅ፤ 49 የብርና፤ 63 የነሐስ ሜዳልያዎች) በመሰብሰብ በምንግዜም ከፍተኛ የሜዳልያ ስብስብ 10ኛ ናት፡፡ ከ12ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች በፊት ባለፉት 11 የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ላይ ምንም አይነት ሜዳልያ ያልወሰዱት የኮሞሮስ፤ ኢኳቶርያል ጊኒ፤ ሞሪታኒያ እና ደቡብ ሱዳን ብሄራዊ ኦሎምፒክ ኮሚቴዎች  ናቸው፡፡

Read 1140 times