Saturday, 24 August 2019 14:50

ሳቂ! እንደ ጸሐይ ያለማቋረጥ እንደሚፈስ ጅረት…

Written by 
Rate this item
(4 votes)


           እንደሚገማሸር የባህር ማዕበል ግለ-ታሪኳን ታዘንበው ቀጠለች፡፡ ድምጽ መቅጃዬን አስተካክዬ ጠረጴዛው ላይ ቁጭ አደረግሁ፡፡ እየተቀዳች መሆኗንም ነገርኳት፡፡ አንዳንድ ሰዎች ድምጻቸው ሲቀዳ ቃላት በመምረጥ ይጨናነቃሉ፡፡ እሷ ምንም አልመሰላት፡፡ አልፎ አልፎ የተናገረችውን መልሳ ከመድገም በቀር የማስታወስ ችሎታዋ የተመሰገነ ነበር፡፡ ጥቃቅን ነገሮችን እንኳ አልረሳችም፡፡ ስለ ማንነቴ ለማወቅ መፈለጓ አልቀረም፡፡ ዳሩ ከእርጅና ዘመን ብቸኝነት ስለገላገልኳት ጥያቄ ማብዛቴን አልጠላችውም፡፡ ከልቧ ተቀብላኝ ነበር፡፡ መደባበቅ የማታውቅ ነፃ ሰው ነበረች፡፡ ከመነሻው በአንቱታ እንድጠራት ባለመፍቀዷ ቀለለኝ፡፡
‹‹ቤት መኻእ የሚባለውን ዓዲ ታውቀዋለህ?››
‹‹አውቀዋለሁ፡፡››
‹‹እዚያ ተወለድኩ።››
‹‹መቼ ማለት ነው?››
‹‹ቁጥሩን አላውቀውም፡፡ አባቴ አብርሃ ገብረመድህን ንጉሰ ይባላል፡፡ ባረንቱ ሲገደል እኔ የአምስት አመት ልጅ ነበርኩ፡፡››
‹‹አባትሽ መቼ ተገደለ?››
‹‹የጣልያን ወታደር ሆኖ ከእንግሊዝ ጋር ሲዋጋ በዚያው ጦርነቱ ላይ ሞተ፡፡ ጣልያን መውደቁ ላይቀር አባቴ ህይወቱን አጣ፡፡ አሁን ገብቶሃል? በል እንግዲህ እድሜዬን ንገረኝ?››
አሰላሁና ነገርኳት፣
‹‹የተወለድሽው 1936 አካባቢ ነው፡፡ በዚህም የ82 አመት የእድሜ ባለጸጋ ሆነሻል፡፡ እድለኛ ነሽ በ’ውነቱ፡፡››
‹‹እውነት ብለሃል፡፡ Sono molto (በጣም እድለኛ ነኝ፡፡) በሽታ አያውቀኝም፡፡ እርጅና ብቻ ነው ህመሜ፡፡ ያም ሆኖ ቡናዬን ራሴ አፈላለሁ፡፡ ምግብ አዘጋጁልኝ ብዬ አላስቸግርም፡፡››
‹‹ከአባትሽ መገደል በሁዋላ ምን ሆነ?››
‹‹ምንም የሆነ ነገር የለም፡፡ እኔ እዚህ ዕዳጋ አርቢ አክስቴ ዘንድ መኖር ጀመርኩ፡፡ እናቴ ተኽለ ተኽለማርያም ትባላለች፡፡ ደከመኝ የማታውቅ ብርቱ ሴት ነበረች፡፡ ቤት መኻእ ትኖር ነበር፡፡ እዚያም እሄዳለሁ፡፡ እዚህም እኖራለሁ፡፡ በቃ እንደሱ ነበር…››
‹‹ትምህርት ቤት አልሄድሽም?››
‹‹እምቢ አልኩ፡፡ ተለምኜ ነበር፡፡ እናቴ ሁለት ስራ ትሰራ ነበር፡፡ ከጣልያናውያን ቤቶች ትሰራ ነበር፡፡ በፋብሪካም እንዲሁ ትሰራለች፡፡ በጥሩ ሁኔታ ልታስተምረን ትጥር ነበር። ታናሽ ወንድሜ አስመላሽ አብርሃ Scuola Italiana (ጣልያን ትምህርት ቤት) ገብቶ ሲማር እኔ እምቢ አልኩ፡፡ አስመዝግበውኝ ነበር፡፡ ትምህርት ቤት እሄዳለሁ እያልኩ ከተማ ውስጥ እዞራለሁ፡፡ ጨዋታ ብቻ ሆንኩ፡፡››
‹‹የልጅነት ትዝታሽ ምንድነው?››
‹‹No ho una memoria speciale (ምንም የተለየ ትዝታ የለኝም፡፡) የአክስቴ ባል ስለ ሼኽ ዓምር ሴት ልጅ ማውራት ይወድ ነበር፡፡ ታሪኩን ከየት እንዳመጣው አይታወቅም፡፡ አውርቶ ሲጨርስ ‹እንዳንቺ ቆንጆ ነበረች› ይለኝ ነበር፡፡ ይሄ አይረሳኝም፡፡ ያኔ ገና ልጅ ነበርኩ፡። ቁንጅናዬ ግን ታውቋል፡፡ ቁመቴ ተመዟል፡፡ ሃይለኛ ነበርኩ፡፡ ልጅ ብሆንም ከተቆጣሁ ድመት ነበርኩ፡፡ እቧጨራለሁ:: ለማንም አልመለስም፡፡ ‹እንደ አባቷ ናት› ይሉኛል:: አባቴ እንዴት እንደነበር አላውቅም፡፡ ባረንቱ ላይ ሲሞት ልጅ ነበርኩ…››
ቡና ልታፈላ ምድጃው ተቀጣጥሎ ነበር፡፡
መንከሽከሽ ፈልጋ ጓዳ ገብታ ተመልሳ መጣች፡፡
‹‹…ባረንቱ ላይ በከንቱ ሞተ አባቴ፡፡›› ስትል ወጓን ቀጠለች ‹‹…ክተቱ ብለው ከሰንዓፈ ነበር የወሰዱት፡፡››
‹‹ሰንዓፈ ምን ይሰራ ነበር?››
‹‹ሰንዓፈ ነው አገራችን፡፡ እንግሊዝ እየበረታ ሲመጣ ከተቱ ተባሉ፡፡ ከዚያም ስንቱ የሰንዓፈ ጎበዝ ትዳሩን እየተወ ለጥልያን ወታደር ሆኖ ባረንቱ እየሄደ አለቀ። Ecco, cosa ti dico di an-cora? (በቃ፡፡ ይኸው ነው፡፡ ሌላ ምን ልንገርህ?)
‹‹መማር ነበረብሽ፡፡››
‹‹ልክ ነው፡፡ ‹ተማሪ› ተብዬ እምቢ አልኩ:: ልጅነት አታለለኝ፡፡ አባቴ ባለመኖሩ በቅርብ የሚከታተለኝ ሰው አልነበረም፡፡ ያኔ ተምሬ ቢሆን ኖሮ ዛሬ ሌላ ሰው በሆንኩ ነበር፡፡››
ትክዝ ብላ አቀርቅራ ቆየችና ቀና አለች፣
‹‹ለምንድነው ታሪኬን የምትጠየቀኝ?››
‹‹ልጽፈው ነው፡፡››
‹‹የሚጻፍ ታሪክ የለኝም፡፡ ተራ ሰው ነኝ፡፡››
‹‹የታሪክ ተራ የለውም፡፡ ይልቁን ቀጥይልኝ?››
‹‹ምን ልንገርህ?››

Read 3693 times