Saturday, 24 August 2019 14:17

የተማሪው ፀሎት

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(7 votes)

እናቱ ወደ ቤተ ክርስቲያን እንደሄደች ያየው ህፃን፣ ሮጦ መኝታ ቤት ገባና በሩን ዘጋው፡፡ ወዲያው እናቱ ስታደርግ እንዳየው፣ ግድግዳ ላይ ከተለጠፈው የመድሀኒዓለም ምስል ሥር ተንበርክኮ፡-
“አንተ የእናቴ አባት ስለሆንክ፣ አያቴ ነህ አይደል? አያት ደሞ ጥሩ ነው…” ዝም ብሎ ምስሉን እያየ መናገር ቀጠለ - ሕጻኑ፡፡
“በቀደም ቡሄ የጨፈርንበትን ሳንቲም እማዬ ወሰደችብኝ፤ እኔን ሣንቲም እንዳትሠርቅ  ስትለኝ፣ እሺ እያልኳት፣ እሷ ግን ወሰደችብኝ፡፡ ጓደኞቼ እነ ሮቤልና ሠለሞን ግን አልተወሰደባቸውም፡፡
“ደሞ የወሰደችብኝ ‹ደብተር መግዣ ይሆንሃል› ብላ ነው፡፡ የሮቤል እናት ግን ‹በዚህ ዓመት ዶክተር ዐቢይ ደብተር ይገዛላችኋል› ብለዋል፡፡ እኔም በዚህ ዓመት ትምህርት እጀምራለሁ፡፡ እባክህ ለናቴ ቤተስኪያን ውስጥ ንገራት፡፡ ብስኩትና ከረሜላ መብላት እፈልጋለሁ፡፡ ጓደኞቼን እየለመንኩ መብላት አስጠልቶኛል፡፡”
ከውጭ የእግር ኮቴ ሰማና ደነገጠ፡፡ ወደ ኋላ ዘወር ብሎ አየ፡፡ እናቱ ከመጣች አንጠልጥላ ታስወጣዋለች፡፡ ጆሮውን ተክሎ አዳመጠ፡፡ እህቱ ፌቨን ናት፡፡
“ሳሚ የት ሄዶ ነው? ሲንቀለቀል ደሞ መኪና እንዳይገጨው” ስትል ሰማትና ሳቁ መጣ፡፡
“መድሃኔዓለም አጠገቤ እያለ መኪና ይገጭሃል ትላለች!” ድምፁን ቀንሶ፣ ለራሱ አጉተመተመ፡፡
“አሁን ለእንቁጣጣሽ አበባ የሚስልልኝ በቃሉም የለም፡፡ ሞቷል፤ አንተ ነህ የወሰድከው አይደል፡፡ እናንተ ጋ ችቦና ሆያ ሆዬ አለ እንዴ? አንተ ጋ ሲመጡ ስንት ብር ትሰጣቸዋለህ? ብሩን ምን ያደርጉበታል? በቃሉ ጥሩ ልጅ ነበር፡፡ አምና አበባ የሠራልኝ እርሱ ነበር፡፡ ክንፍ ያለው መልዐከ ነበር የሳለልኝ፣ እርሱ መቼም አንተ ጋ ሲመጣ… ክንፍ ያወጣል፡፡ ለእኔም ክንፍ ብታወጣልኝ ደስ ይለኛል፡፡ ታክሲ ውስጥ ወያሎቹ ‹ይክፈል፤ ወይም አስወርጂው!” እያሉ ያሳቅቁኛል፡፡ እናቴንም ‹‹በሌላ ታክሲ ሂጂ›› እያሉ ያበሳጩዋታል፡፡ ያኔ ልቤ ድው ድው ይላል፡፡ ዶክተር ዐቢይ ለልጆች ታክሲ እንዲገዛልን ንገረው፡፡›› አለና ቆም ብሎ አየው - መድሃኒያለምን፡፡ የበግ ግልገል ታቅፎ ቆሟል፡፡
“እኔ ግን ከበግ የበለጠ ድመቴን እወዳታለሁ፣ ማታ ማታ በተኛሁበት መጥታ ታቅፈኛለች፤ ታሞቀኛለች፡፡  ጅብ ከመጣ ግን ገና ድምፁን ስሰማ እናቴ ሥር እገባለሁ፡፡››… (አንተ ያቀፍካትን ግልገል ስታድግ ታርዳታለህ እንዴ? እባክህ አትረዳት፤ ታሳዝናለች፡፡ የሮቤል አባት ግን ጨካኝ ናቸው፡፡ ቤታቸው ያደገችውን በግ ለፋሲካ አረዷት፡፡ አንተ ከሞት የተነሳህበት ቀን ነው ብለው እርሷን አረዷት:: የዛን ዕለት ሮቤል ሲያለቅስ ነው የዋለው፡፡ በጣም ይወዳት ነበር፡፡ ማታ ግን ሥጋዋን በልቷል፡፡ በግ ሳይታረድ ሥጋ መፍጠር አትችልም እንዴ? በናትህ ሞክር…
ዶክተር ዐቢይ ደስ የሚለኝ… በግ አያርድም፡፡ “ሠላም ፍቅር” ነው የሚለው፡፡ ‹‹መግደል መሸነፍ ነው” ሲል አልሰማኸውም? ለህፃናት የትምህርት ቤት ቦርሳ ሲሸልም በቲቪ አይቼዋለሁ፡፡ ዘንድሮ ትምህርት ቤት ስገባ፣ ዶክተር ዐቢይ የሚሰጠንን ቦርሣ ነው የምይዘው፡፡
‹‹የኔ እህት ሰላም ግን ትምህርት ቤት የገባችው የአጐታችንን ልጅ አሮጌ ቦርሳ ይዛ ነው፡፡ አንተንም ዶክተር ዐቢይንም አመሰግናለሁ፡፡ በቀደም ይህንን ስሰማ ቆንጆ መዝሙር ዘምሬልሃለሁ፡፡
ምሥጋና ይገባሃል
ምሥጋና ይገባሃል
አባቴ እግዚብሔር.. ብዬ፡፡
እማዬ ብትሰማ ግን ምን ትላለች? የእናት አባት አያት አይደለም እንዴ? አንተ የኔ አያት ነህ ወይስ አባት?...››
እህቱ ሠላም ድንገት መጥታ በሩን በረገደችው፡፡ ለካ በሩን በደንብ አልዘጋውም፡፡ ድንግጥ አለ፡፡
“አ…ን…ተ!”
መልስ አልሰጣትም፡፡
“እኔ የት ሄደ ብዬ መከራ ሳይ እዚህ ተንበርክከህልኛል? ደሞ ማን ፀልይ ብሎህ ነው? የሆያሆዬ ገንዘብ ወሰዱብኝ›› ብለህ እያሳበቅህ ነው››
“ለኑሮ ውድነቱ እንደሆነ እናትህ አቤት የምትልበት አጥታ ወደ ፈጣሪ ልትጮህ ሄዳለች፡፡ ዘይት ተወደደ፣ ጤፍ ሰማይ ነካ፣ ምስር የለም፣ ሽሮ ጠፋ፣ ቤታችን የቀበሌ ባይሆን በረንዳ ወድቀን ነበር:: ኢንጂነር ታከለ ዑማ፤ ጐዳና ተዳዳሪ እየሰበሰበ ወደ ቤት ሲያስገባ፣ ቤት ያለው ህዝብ የሚበላው አጥቶ ሊበተን ነው፡፡ ይሄም ጀግና የተባለ ህዝብ፣ ጀግንነቱን የሚያሳየው ወንድሙን በመግደል እየሆነ ነው፡፡ አየኸው ረሃብ ውስጥ ሆኖ እንኳ ወገኑን ለመግደል ቢላ ይስላል?
እውነትህን ነው… አዋቂው ቂመኛ ስለሆነ ፀሎቱ መልስ አጥቷል፡፡ አንተ በንፁህ ልብህ ብትፀልይ ነው የሚሻለው››
መልስ በሩን ዘግታበት ሄደች፡፡ ትንሽ ቆየና ተንበረከከ፡፡
“ጌታ  ሆይ፤ ጉዴ ፈላ! እማዬ ትገድለኛለች፡፡ እህል ከተወደደ፣ ጉሊት ገበያ ከሌለ፣ “አፈር ብላ! ያንተን ከርስ ከየት አምጥቼ ልሞላ ነው?...” ትላለች:: እባክህ ድህነትን አጥፋልን፣ ሁሉ ነገር ከተወደደ መሞታችን ነው፡፡››
እንባው ሳያውቀው በጉንጮቹ ወረደ፡፡
“ምሣ የለም፣ ከየት አባክ ላምጣልህ? ትለኛለች:: ሮቤል ግን በሚቀጥለው ዐመት ትምህርት ቤት ምሳ ይዘጋጃል ብሎኛል፡፡ ዶክተር ዐቢይ ብር ከየት ነው የሚያመጣው? ቦርሳ፣ ዩኒፎርም፣ ምሳ… እባክህ ለርሱ ገንዘብ በደንብ ስጠው፡፡
‹‹አንተ አባትዋ ከሆንክ ግን እሷ ለምን ደሀ ሆነች? ሁሌ መድኃኔዓለም አባቴ ነው… ትል የለ? አባት ደሞ ገንዘብ ይሰጣል፡፡ የሮቤል አባት አንዳንዴ ኬክ ቤት ወስዶ ይጋብዘዋል፡፡ አንተ እማዬን አንዴም ጋበዘሃት አታውቅም? የእንጀራ አባት ነህ እንዴ? …የእንጀራ አባት ደሞ ይማታል፡፡ ጓደኛችንን የእንጀራ እናቱ ብዙ ቀን ምሳ ትከለክለዋለች፡፡ አንተስ እናት አለህ? እናትህ ሳትወልድህ በፊት ዐለምን ፈጥረህ ነበር? ተወው በቃ! እማዬ ይህን ብትሰማ ትገድለኛለች!
‹‹አንድ ቀን ልጅ፤ እንደ ልጅ አስብ!›› ብላ አናቴን ብላኛለች፡፡ ሌላ ቀን ደሞ ‹‹እግዚአብሔርን ማን ፈጠረው?›› ብዬአት ቀጥቅጣኛለች፡፡ ይሄን እንዳትነግራት፡፡
ወደ ግድግዳው ተጠግቶ ምስሉን ግጥም አድርጐ እየሳመ፤ ‹‹እኔ እወድሃለሁ… አንተም አሳድገኝ፤ ሳድግ ምርጥ መዝሙር አውጥቼ እዘምርልሃለሁ! አንተም ድምፄን አሳምርልኝ፤ ትምህርት የምጀምር ቀን ደግሞ መጥቼ እነግርሃለሁ!...
‹‹አደራ እንዳትረሳ ለዶክተር ዐቢይ ገንዘብ ስጠው፡፡ ለእርሱ ከሰጠኸው ሁሉን ነገር ይሰጠናል::›› እህቱ እየሮጠች መጣች፡፡
“ሳሚ ተነስ! እማዬ እየመጣች ነው፤ ትጠፈጥፍሃለች! ማን ፀልይልኝ አለህ ነው የምትለው! የአባታችንን ቂም በእኛ ልትወጣ ነው መሰለኝ፡፡ ቀድሞውኑ ወታደር ማን አግቢ አላት? እዚያ በረሃ እየኖረ ብቻውን እንዲሆን ፈልጋ ነው? ተሳሳትኩ ካለ ይቅርታ አታደርግለትም?”
“አባዬ አለ እንዴ?” ህጻኑ ጠየቀ፡፡
“አታውቅም ነበር?”
“እማዬ ሞቷል ብላኛለች?”
“ተናድዳ ነው! እኔ በፌስ ቡክ አግቻቸዋለሁ
“እባክሽ ፌስ ቡክ አሳዪኝ!”
“ቀስ ብለህ እደግ!” ጥላው ሄደች፡፡
በጥድፊያ፤ “እባክህ ጌታዬ አባዬና እማዬን አስታርቃቸው!”
እንባው ጉንጩን አለበሰው፡፡
“ቡሄ የጨፈርኩበትን ገንዘብ ተወውና… እማዬና አባዬን እንዲታረቁ አድርጋቸው! ባክህ እኔም አባቴን አጠገቤ ላግኘው፡፡
“የኔ መድናኔዓለም ምን ይሳንሃል”
“እውነት” አለች ሠላም፡፡

Read 2998 times