Saturday, 24 August 2019 14:14

አሸንዳ - ሻደይ - አሸንድዬ - ሶለል

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(1 Vote)

  የዘንድሮው የአሸንዳ፣ ሻደይ፣ አሸንድዬና ሶለል በዓላት በትግራይና አማራ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብረዋል፡፡ በዓሉ በተለየ ሁኔታ በሚከበርባቸው በእነዚህ አካባቢዎች፤ በዓሉ ሀይማኖታዊና ባህላዊ መገለጫውን ጠብቆ እንዲቀጥል ሁሉም ዜጋ ኃላፊነት እንዳለበት ተገልጿል፡፡
በዘንድሮው የትግራይ ክልል የአሸንዳ በዓል አከባበር ሥነስርዓት ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እንደተናሩት፤ የአሸንዳ በዓል በተለይ ለሴቶች የሚሰጠው ክብር ከፍ የሚልበትና የሚገለጽበት በዓል እንደሆነ አውስተው፣ በዓሉ በሚከበርባቸው ቀናት ለአሸንዳ ሴት የሚሰጠው ክብር ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ሴቶች በ365ቱም ቀናት ሊሰጥ ይገባል ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ እንደ አሸንዳ ያሉ የበርካታ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ቅርሶች ባለቤት መሆኗን የገለፁት ፕሬዚዳንቷ፤ እነዚህን ሀብቶች ተንከባክበንና ጠብቀን ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ ይኖርብናል ብለዋል፡፡ የአሸንዳ በዓል እንደ መስቀል፣ ፊቼና ጨምበላላ በዓላት ሁሉ በዩኔስኮ የማይዳሰስ ቅርስነት እንደሚመዘገብ ያላቸውን ጽኑ እምነት  ተናግረዋል፡፡
‹‹በዓልን የፖለቲካ ድንበር አይገድበውም›› ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፤ የአሸንዳ በዓልን አለም እንዲያውቀው ሰፊ ሥራ መስራት እንደሚጠበቅም አሳስበዋል፡፡ የአሸንዳ በዓልን ተባብረን እንዳከበርን ሁሉ፣ ሀገራችንንም ተባብረን ልንጠብቅ ይገባል ሲሉም ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ተናግረዋል፡፡
በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ ውስጥ በተከባበረው በዚህ በዓል ላይ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል እንደተናገሩት፤ የትግራይ ህዝብ ባህሉንና ማንነቱን ለረጅም አመታት ተንከባክቦ ያቆየ ህዝብ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዓሉን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡ የአሸንዳ ልጆች የሰላምና የፍቅር መገለጫ የሆነ በዓላቸውን አጠናክረው መያዝ እንደሚገባቸው የገለፁት ዶ/ር ደብረጽዮን፤ ስለ ፍትህ፣ ሰላምና ልማት መረጋገጥ አንድነታቸውን ጠብቀው መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
በትግራይ ክልል የተከበረውን የዘንድሮውን የአሸንዳ በዓል ለየት ከሚያደርጉት ጉዳዮች አንዱ፤ በክልሉ ባለስልጣናት ስሞች የተሰሩ የአሸንዳ ልጃገረዶች የሚለብሱዋቸው አልባሳት በብዛት መኖራቸው ነው፡፡ ድንገት እግር ጥልዎ አንድ የልብስ መሸጫ መደብር ውስጥ ከተገኙ፤ ደብረጽዮን ወይም ጌታቸው አሰፋ አለ የሚል የሸማች ጥያቄ ሰምተው ሊደነግጡ ይችላሉ፡፡
አዳዲስ አልባሳትን ለብሶ መታየት በአሸንዳ በዓል ትኩረት የሚሰጠው ጉዳዩ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ዘንድሮ የትግራይ የልብስ ስፌት ባለሙያዎች፣ አዳዲስ ዲዛይኖች ያሏቸውን አልባሳት ሰርተው፣ በክልሉ ባለስልጣናት ስም ሰይመው ነው ለገበያ ያቀረቡት፡፡
“ደብረጽዮን፣ ጌታቸው አሰፋ፣ ጌታቸው ረዳና አባይ ፀሐዬ” የተባሉ የወቅቱን የአገሪቱን የፖለቲካ ግለት የሚያንፀባርቁ ስያሜዎችን ለአዳዲሶቹ ልብሶቻቸው ሰጥተዋል፡፡ በዘንድሮው የአሸንዳ በዓል “ደብረጽዮን” የሚል ስያሜ የተሰጠው ልብስ፤ በርካታ ፈላጊዎችን ማግኘቱንና በስፋት መሸጡን ቢቢሲ በአማርኛ ዘገባው ላይ ገልፆታል፡፡ በመቀሌው የአሸንዳ በዓል የአልባሳት ስያሜ በቅርቡ ህይወታቸውን ያጡት ጀነራሎችም ተወስተዋል፡፡
በአማራ ክልል ዋግ ኸምራ ዞን፣ ሰቆጣ ከተማ በደማቅ ሁኔታ የተከበረው የሻደይ በዓል ላይ በአንግድነት የተገኙት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ባደረጉት ንግግር፤ የሻደይ በዓል በትውልድ መሀል የታሪክ ቅብብሎሽ ለማጠናከርና ጥላቻን ለማስወገድ ትልቅ ጠቀሜታ አለው ብለዋል፡፡
የሻደይ በዓል ከባህላዊ ጠቀሜታው ባሻገር ከፍ ያለ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጠቀሜታ ጠቁመው፤ ህብረተሰቡ ለአካባቢው ትውፊታዊ ሃብት እንክብካቤ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል፡፡
በዓሉ በትውልድ መካከል የታሪክ ቅብብሎሽ ለማጠናከር፣ ጥላቻን ለማስወገድ መተባበርን ለማጐልበት ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለውም ርዕሰ መስተዳድሩ ገልፀዋል፡፡ የሻደይ በዓል በህዝቦች  መከባበር ላይ የተመሰረተ አንድነትን ከማጐልበት አንፃር ሚናው ከፍተኛ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
በዓሉ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ሁሉ እንዲከበር አለምአቀፋዊ እውቅናም እንዲያገኝ መጣር እንደሚገባም አቶ ተመስገን አሳስበዋል፡፡
ከአማራ ክልል ሰቆጣ ከተማ ውስጥ በተከበረው የሻደይ በዓል ላይ በርካታ የፌደራልና የክልል መስተዳድር የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡


Read 5803 times