Tuesday, 12 June 2012 12:26

የግሩም መሰናዶ ባለሟሎች

Written by  ቃልኪዳን ይበልጣል
Rate this item
(1 Vote)

(ሰባት ድንቅ የሬዲዮ ዝግጅቶች)
እንደ መግቢያ
በኤፍ ኤምም ሊደመጥ የሚችለውን ብሔራዊውን የኢትዮጵያ ሬዲዮ ሳንቆጥር በመዲናችን ያሉት የኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች ስድስት ናቸው፡፡ በመንግስት የሚተዳደረው ኤፍ ኤም አዲስ 97.1 የ24 ሰዓት ስርጭት ሲኖረው የተቀሩት በየዕለቱ ለ18 ሰዓታት ያህል “አሉን” የሚሏቸውን ዝግጅቶች ለታዳሚዎቻቸው ያደርሳሉ፡፡ ይህን ይዘን ሒሳቡን ብናሰላው የጣቢያዎቹ የጋራ ሳምንታዊ የአየር ሽፋን 798 ሰዓት ይሆናል፡፡
ቅጥ ባጣ የህዝብና የፎቅ እድገት ውስጥ የምትውተረተረው ከተማችን የሚበቋትን ያህል የብዙኃን መገናኛ ታድላለች በዚህ ረገድም ነዋሪዎቿ ጥማቸው በአግባቡ ተቆርጧል ባይባልም ቅሉ፤ ያለውንም በጥንቃቄ መጠቀም ብልህነት ነው፡፡ እና ከላይ የተጠቀሰውን በሚያህለው የጊዜ መጠን በየጣቢያዎቹ መደበኛ አዘጋጆችም ሆነ ከውጭ ጥንቅራቸውን ይዘው ወደ ስቱዲዮ በሚዘልቁ ተባባሪዎቻቸው እየተሰናዱ የሚቀርቡትን ዝግጅቶች፣ መርምሮ በማስረጃ የተደገፈ ሁነኛ መረጃ የሚሰጠን አካል እንጠብቃለን፡፡

እስከዚያው ግን እንዲያው በደፈናው ጆሮዋችንን ወዲያ ወዲህ ስናማትር ያለ ወጥ መርሃዊ መመሪያ በዘፈቀደ የሚከታተሉ ዝብርቅርቅ ዘፈኖች፣ ችግርን ከመቅረፍ ይልቅ በመደጋገም ላይ የሚያተኩሩ ጉንጭ አልፋ የስልክ ውይይቶች እና ሀሜታ የሚበዛቸው የስፖርት ወኪነጥበብ ከዋክብት ወሬዎች እንደሚበረክቱ ታዝበናል፡፡ ጥልቅ ፍተሻ የሚፈልግ ብዙ ታሪክ፣ በቅጡ መረዳትን የሚጠይቅ ድርጁ ባህል እንደየስሩ እንደየዘሩ የተዥጐረጐረ የአኗኗር ዘይቤ፣ ምርመራና መላ የሚሻ ገፀ ብዙ ማህበራዊ ውጥንቅጥ በተትረፈረፈባት ሀገር የመገናኛ ብዙሃን ሚና ከ”ማዝናናት” እና ማሳተፍ ሊሻገር ይገባል፡፡ የህትመቱ ሚዲያ ከየአቅጣጫው በሚወነጨፍ ውጋት የመሰነጉ እና በወጀብ ታጅቦ የመቸገሩ ጉዳይ ሲታሰብ፣ የቴሌቪዥን ጋዜጠኝነት “ልማታዊ” በሚሉት ቅፅል ታፍኖ ተጠናግሮ ሞት አፋፍ መቆሙ ሲጤን፣ ኢንተርኔትም ለአቅመ - አማርጭነት ደርሶ እንዳልጐለመሰ ሲታይ የሬዲዮ የተሻለ ዕድልና ተጠባቂነት አያስደንቅም፡፡
ከበርካታ ታዳሚያን ዘንድ ለመድረስ ከሌሎቹ የቀለለ መንገድ መሆኑ አንድና አንድ የለውምና፡፡ ታዲያ እውቀትና እውነት እየመሩት፣ ጥበብና ክሂል እየደገፉት ታዳሚውን አክብሮ የሚከበር ዘርፍ ቢሆን ምኞታችን ነው፡፡
የዚች ጦማር ዋነኛ ግብ በአቀራረብ ለዛቸው እና ዘወትር በሚቋጥሩት ቁምነገራቸው የላቁ፣ አትኩሮትን ቢለግሷቸው የማያስቆጩ ድንቅ የሬዲዮ ዝግጅቶችን መጠቆም ነው፡፡ እንዲህ የመነሳቱ አግባብ ያው ላይ ታች ወርደው፣ በጭብጨባ እና ሆይ ሆይታ ሳይደናበሩ ጥሩ ጥሩ መሰናዶዎችን ለማቅረብ ለበረቱ ትጉኃን ምስጋና ለመቸር፣ በዚያውም ዝግጅቶቹ የሬዲዮን እምቅ አቅም በጨረፍታም ቢሆን ለመመልከት በማሳያነት ይረዳሉ ብሎ በማመን ነው፡

ሸገር ካፌ
(በሸገር ኤፍ ኤም 102.1 ዘወትር እሁድ ማለዳ ከ3-5 ሰዓት)
አዲስ አበባችን የካፌዎች መፈልፈያ ሆና ልዩ ማንነት የማብቀሏ ጉዳይ መወጋት ከተጀመረ ሰነባብቷል፡፡ ምናልባትም ይህ የካፌ ትውልድ “መውጣትና መግባት”ን በመሳሰሉ መጽሐፍት ራሱን ያገኝ ይዟል፡፡ ሆኖም ተቺዎች ሌላኛዋን በካፌዎቿ ስም የገዛች ከተማ፣ ብርሃናማዋን ፓሪስን በማነፃፀሪያነት እያነሱ፣ የኛዎቹ የፈረንሳዩዋን መናገሻ ያህል የኪነ ጥበብ፣ ፍልስፍና እና ፖለቲካ ውይይት ሲደራባቸው አይስተዋሉም ይላሉ፡፡
የ”ሸገር ካፌ” መሰናዶ ይህንን ምልከታ ውድቅ ለማድረግ የተነሳ ይመስላል - በምናባዊነቱ ሳይገደብ፡፡
ቅርፁን ከምናውቃቸው ካፌዎች ተውሷል፡፡ ጉልበቱ የተሞላው ግን ይዘቱ ውስጥ ነው፡፡ የሀገራችንን ህግና ስርዓት ከስር መሰረቱ የሚተነትኑ፣ ወግና ልማዱን በእውቀት ተመርኩዘው፣ ጥናትና ንባብን በአስረጅነት ይዘው የሚያስረዱ፣ የኑሮ ይትባህሉን ከምርምርም ከግለሰባዊ ተሞክሮም እያጣቀሱ የሚያሄሱ፤ ሲያሻም የሚያሞግሱ፤ ምሁራንን እና ከያንያንን እየመረጠ፣ የመወያያ ጉዳይ እየሰጠ ማጨዋወት ነው ግብሩ፡፡ ረብ ያለው ቁምነገር እንዲህም አምሮ ይፈስሳል፣ እንዲህም ተቀንብቦ ይታፈሳል፤ እንዲህም ለበለጠ ትጋት ያነሳሳል፡፡

(በፋና ኤፍ ኤም 98.1 ዘወትር አርብ ከቀኑ 10-12 ሰዓት እና ቅዳሜ ከቀኑ 7-9 ሰዓት)
ይህ ዝግጅት በቅድሚያ ሙዚቃዊ እውቀትን የሚያደራጅ ትምህርት ቤት ነው፡፡ ቀጥሎም በሙዚቃ በር ዘልቆ ገብቶ ከሰፊ ማህበራዊ፣ ፍልስፍናዊ፣ ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ህልውናዊ እሳቤዎች ጋር የሚተያዩበት መድረክ ነበር፡፡ አቅራቢዎቹ ሰርፀ ፍሬስብሃት እና አብርሃም ተስፋዬ ከኛው የአዝማሪ ዘፈን እስከ ትውልደ አሜሪካዊው ጃዝ እስከ ብሉዩ ክላሲካል ሙዚቃን በሳይንሳዊ ልኬታ ይተነትናሉ፡፡ እየገነኑ አሊያም እየተገነኑ የሚታዩ አዝማሚያዎችንና ዝንባሌዎችን እያወሱ ሲያስፈልግ ያበረታታሉ፤ ግድ ሲሆን ይገስፃሉ፡፡ አንዳንዴ ዘመዳም የኪነት ዘርፎችን የሚነኩ ርዕሶችን ያነሳሉ፡፡ አልፎ አልፎ አልበሞችን ይገመግማሉ፡፡ ሩቅ ከሚመስሉን ሀገሮች (ለምሳሌ ቲቤት) ያልተጠበቀ መመሳሰል ይመዛሉ፡፡ እግረ መንገዳቸውንም ባህልና ህብረተሰብን ይዳስሳሉ፡፡
ዝግጅቱ በሳምንት የአራት ሰዓታት ዕድሜ ያገኘው በቅርቡ ከጥቂት ገውና ገጭ በኋላ ነው፡፡ ሆኖም ቆይታው ከአንድ ሰዓት ወደ  ሁለት ሰዓታት ከተራዘመ አንስቶና አሁንም የተወሰነ የትኩረት ማጣት እንደተስተዋለበት መካድ አይቻልም፡፡ አንዲት የምትጣል ገለባ ወደማይገኝበት ድንቅነቱ እንደሚመለስ ግን እምነቱ አለን፡፡

ከቤት እስከ ከተማ

(በሸገር ኤፍ ኤም 102.1 ዘወትር ማክሰኞ ምሽት
 ከ2-3 ሰዓት)
በዋናነት በህንፃ አገነባብ፣ ምህንድስናና የከተማ አኗኗር ላይ የሚያጠነጥን ሙያዊ ዝግጅት ነው፡፡ ኪነ - ህንፃ ለማይመስጠው ተርታ ግለሰብም ቢሆን እንኳን ብዙ የጥበብ ፍሬዎች ሰንቋል፡፡
በእድሜ ጠገብ ግንባታዎቻችን ኪነ - ህንፃዊ መዋቅር ዙሪያ ማብራሪያ በመስጠት ታሪካችንን ለመገንዘብም፣ ነባሩን እውቀት ለማሸጋገርም ጉልህ ሚና ይጫወታል፡፡ አብዝቶ ስለመዲናችን ትናንትና፣ ዛሬ እና ነገ ያወራል፡፡ ለያዥ ለገናዥ ባስቸገረ መልኩ እየተለወጠች ነው የጣይቱ ከተማ፡፡ ይህ የዝመና ሂደት እንደምን ሊከወን ይገባል? የበለጠ የምናተርፈው ምን ብንተገበር ነው? በጭፍን ሩጫ የምናጣቸው (ያጣናቸው) ማህበራዊ እንዲሁም ታሪካዊ ተቋማት ምን ያህል ዋጋ ያስከፍሉናል? - የኪነ ህንፃ ባለሞያው ማህደር ገ/መድህን በዝግጅቱ የሚያተኩርባቸው ነጥቦች ናቸው፡፡ ከምንም በላይ ኑሮዋችንን ይበልጥ እንረዳው ዘንድ ያግዘናል፡፡ አልፎ አልፎ በሌሎች የአውሮፓ፣ የአሜሪካ አሊያም የአፍሪካ ከተሞች እየተገኘ ከአዲስ አበባ ጋር ያወዳድርልናል፡፡ ምን ይጐድለናል? ምን ጨብጠናል? - ባለሙያው ይነግረናል፡፡

አዲስ ዜማ
(በኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ዘወትር ከሰኞ እስከ አርብ ከቀኑ 10-12 ሰዓት እንዲሁም ቅዳሜ ከቀኑ 7-12 ሰዓት)
አሁን ጥንቃቄ ያስፈልገናል - በተለያዩ ምክንያቶች፡፡ አንድ:- በብዙ ሂደት ውስጥ አልፏል - አዲስ ዜማ፡፡ እያየነው ያለው አሁን በሚገኝበት የብስለት ደረጃው ነው፡፡ ሁለት - ዝብርቅርቅ ገጽታ ያለው ዝግጅት ነው፡፡ ዋዛ ፈዛዛንና መረር ያለ ቁምነገርን በአንድ ገበታ አቅፏል፡፡ ስለዚህም ነጣጥሎ መመዘኑ የተገባ ይሆናል፡፡ ሶስት:- እስከቅርብ ጊዜ ድረስ በሳምንት የ19 ሰዓት ቆይታ ነበረው፡፡ ይህች ጽሑፍ በመጠናቀቅ ላይ ሳለች ግን የቅዳሜ ምሽቱ የ4 ሰዓት መሰናዶ የመሰረዙን ዜና ሰምተናል፡፡ ቅዳሜ ምሽት አንድ ድንቅ የዝግጅቱ ክፍል ይቀርብ ነበር፡፡ “ጀግኖቻችንን እናክብር” ይሰኛል፡፡
በየተሰማሩበት የሙያ ዘርፍ ለሀገራቸው ብሎም በሰው ልጅ በጠቅላላ ህይወት መሻሻል የየራሳቸውን አስተዋፅኦ ያበረከቱ ጀግኖችን ይዘክራል፡፡ በስራና በኑሮ የሚያውቋቸው አጋሮቻቸውን እየጋበዘም ምስክርነት ያስሰጣል፡፡ ትልቁ ስኬቱ ብዙም ወይም ከነአካቴው የማይወራላቸውን፣ የአደባባዩ ዕውቀት ሊዘነጋቸው የተቃረበውን ትንታጐች በርብሮ፣ የዋጣቸውን የዝንጋዔ ዳዋ መገላለጡ ነው፡፡ በእውነቱ አዲስ ዜማዎች ይህንን የብርታታቸውን በኩር ልጅ ሊያሳጡን አይገባም፡፡
ከዚህ በተረፈ የማክሰኞ አመሻሽ የቅዳሜ ከሰዐት በኋላ ዝግጅቶቻቸው ይበል ይሰኛሉ፡፡

እንዳልክና ማህደር
(በሸገር ኤፍ ኤፍ ዘወትር ረቡዕ ማለዳ ከ2፡30 – 4 ሰዓት እንዲሁም ሐሙስ ቀን ከ9 ሰዓት - 11፡30)
የሳተላይት ቴክኖሎጂ ወደየሳሎኖቻችን ያደርስልን የለመዳቸውን ምዕራባዊ የቴሌቪዥን ትርዒቶች የሚመስል ቃና ይዟል፡፡ ቢሆንም የትርዒቱ አውራዎች እንዳልካቸው ጥላሁን እና ማህደር በቀል ከድረ-ገፅ የሚቀራረሙ ወሬዎችን እየሰበሰቡ፣ ዘመንኛ ዘፈኖችን እያከታተሉ “ተዝናኑ” ሲሉ አይታክቱንም፡፡ ከመሰሎቻቸው ነጥለው የሚያወጧቸው ባህርያት አሏቸው፡፡ የመሰናዶዋቸው በጥንቃቄ መሰደር የመጀመሪያው ነው፡፡ ዓለም አቀፋዊ ሰሞንኛ ክስተት ላይ የዳበረና የተደራጀ መረጃ ያቀርባሉ፡፡ የአቀራረባቸው ጥንካሬ፣ ጥንቁቅ የቋንቋ አመራረጣቸውና የሚፈጥሩልን የቅርበት ስሜት ለምስጋና ያሳጫቸዋል፡፡ ስያሜውን ከጳውሎስ ኞኞ ዝነኛ የጋዜጣ አምድ የተዋሰው “አንድ ጥያቄ አለኝ” የሚል የዝግጅታቸው ክፍል የታዳሚን ተሳትፎ የሚጠይቁበት፣ በዋናነት ግን የእክልን መፍቻ ቁልፍ ከባለሞያው የሚሽቱበት ነው፡፡
የዝግጅቱ ድምቀት ግን ምናልባትም “ዘመድ ጥየቃ” ነው፡፡ ነዳያን ያለቅጥ በበረከቱባትና ጉስቁልና ገጦ በወጣባት ከተማችን መንገዶች ላይ እየተዘዋወሩ፣ መንደሮቿንም እያሰሱ የችግር ጡጫ በርትቶ ያደቀቃቸውን ምስኪኖች ህይወት ይቃኛሉ፡፡ ከበጐ አሳቢ የተዘረጋ ድጋፍንም ያደርሳሉ፡፡ ስሜትን የሚያናውጡና መንፈስን የሚሰንጉ በርካታ አጋጣሚዎችን መጭለፍ ይቻላል፡፡

ርዕዮት
(በኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ዘወትር እሁድ ማለዳ ከ4 ሰዓት -6፡30 እንዲሁም ሐሙስ ምሽት ከ3 ሰዓት -6 ሰዓት)
ሁሌም የ”ርዕዮት” መጀመር የሚበሰረው በአንዲት ድንቅ ግጥም ነው፡፡ የገጣሚውና ጋዜጠኛው ቴዎድሮስ ፀጋዬ የምናብ ፍሬ፡፡ የ”ርዕዮት” ዋልታ ቴዎድሮስ ነው፡፡ የአንደበቱ ርቱዕነት፣ የሚሰጣቸው አስተያየቶች ብስለት እና ጥልቀት እንዲሁም የአነጋገሩ ድፍረት ዝግጅቱን ቀጥ አድርጐ አቁሞታል፡፡ እነርሱን በማዳመጥ “አትርፎ መዝናናት” እንደሚቻል ሳያሰልሱ የሚነግሩን ርዕዮቶች፤ ግሩም ምልከታዎችን የዋጡ ወጐችን፣ ኪነጥበባዊ አስተያየቶችንና ሒሶችን፣ በአካል ጉዳተኝነት ላይ የተሰሩ ቅንብሮችን እና ጣፋጭ ዜማዎችን ይጋብዙናል፡፡
ሌላኛውን ቴዎድሮስ (ተ/አረጋይ) በሚያስታውስ መልኩ የቴዲን የጋዜጠኝነት ስብዕና የሚያስወድሰን “የህይወት ገጽ” የሚባለው የቃለ መጠይቅ ክፍል ነው፡፡ በህይወት ጉዟቸው በደረሱበት ከፍታ ያዩትን እንዲያካፍሉ የሚመረጡ ተጠያቂዎችን ማዋራት እና ማስወራት ይችልበታል፡፡ ለማፋጠጥም አይፈራም፡፡ በመረጃ ስንኩልና አይታማም፡፡ እውነትም “ርዕዮት”ን ታደሙና አትርፋችሁ ተዝናኑ፡፡

የቅዳሜ ጨዋታ
(በሸገር ኤፍ ኤም 102.1 ዘወትር ቅዳሜ ከቀኑ 7 ሰዓት እስከ ምሽቱ 1 ሰዓት ድረስ)
ልምድ ያስገኘው ብስለት፣ ንባብና ህይወት ያዳበሩት እውቀት እና ኢትዮጵያዊ ለዛ በአንድ ተጣምረውበታል፡፡ እሸቴ አሰፋ በ”መቆያ” የአለም መሪዎችን (በአብዛኛው) ጓዳ ጐድጓዳ ያስጐበኘናል፡፡ በተሟላ የድምጽ ግብአት እየታገዘ፡፡ ከእኩይነት መካከል በጐነትን፣ ከመልካም ዝና ውስጥ የክፋትን ነጠብጣቦች እናይ ዘንድ ሚዛኑን የጠበቀ ትረካ ይለግሰናል፡፡
ተፈሪ አለሙም በ”ትዝታ ዘ አራዳ” የአባት እናቶቻችንን ተጋድሎ በሚማርክ ድምጽ ያስኮመኩመናል፡፡ ታሪክን ከየስርቻው እየመዘዘ፣ መጽሐፍት እየጠቀሰ “እዚህ የደረስነው እንዲህ ነው” ይለናል፡፡ ከዚያ ተወዳጇ መዓዛ ብሩ እንግዶቿን ይዛ ትቀርባለች፡፡ የራሳቸውን የቴሌቭዥን “ቶክ ሾው” ንግስት ለማግኘት ያልታደሉ ተከታታዮቿ ከኦፕራ ዊንፍሬ ጋር ያወዳድሯታል፡፡ ስለ መዓዛ ምስክርነት መስጠት አዳጋች አይደለም፡፡
በቃለ - መጠይቅ አቀራረቧ ተወዳዳሪ አይገኝላትም፡፡ ለእንግዶቿ የምትፈጥረው የወዳጅነት ስሜት፣ ቀድማ የምታጠናቅቀው ዝግጅትና ስለምትጠይቀው ጉዳይ የምትሰንቀው የዳጐሰ መረጃ፣ ከሀገር አይንና ጆሮ ተከልለው የኖሩ ታላላቆችን ፈልፍላ የምታቀርብበት ሂደት፣ የእንግዶቿ የሙያ ስብጥር ወዘተ ጋዜጠኝነት እምር እልል ሲል እንዲስተዋል የሚያደርጉ ሥራዎቹ ናቸው፡፡
ከእርሷ በኋላ ተውኔት ወይንም ትረካ ይቀርባል፡፡ እንዲያ ስትባሉ ደግሞ ተራ ደንቃይ እንቶፈንቶዎችን አትጠብቁ፡፡ ለምሳሌ ያህል ባለፈው ክረምት የሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን የመድረክ ተውኔቶችን ነበር (ልደቱን ለማስታወስ) ያስተናገዱት፡፡
በመጨረሻ የከተማችንን የጃዝ ሙዚቃ ትንሳኤ ከጓደኞቹ ጋር ሆኖ ያቀላጠፈው ጊታር ተጫዋቹ ሔኖክ ተመስገን “ታይምለስ ክላሲክስ” በሚሰኝ ዝግጅቱ ቆየት ያሉ ድንቅ ዜማዎችን እያከታተለ ይጋብዛል፡፡
ከአንድ አንጋፋ ወደ ሌላ እያነጠረ የቅዳሜ ጨዋታ የማይጠገብ ጨዋታውን ያዘንብልናል፡፡
እንደመውጫ
እስቲ አንዳንድ ጥያቄዎችን እናንሳ፡፡ ኤፍኤሞቻችን ያሏቸው መልካም ዝግጅቶች እነኝህ ብቻ ናቸውን? በጭራሽ! አስቀድሞም እንደተገለፀው የበለጠ ፍተሻ ሌሎች በርካታ እንቁዎችን ያስገኝልናል፡፡ የተዘረዘሩትስ ስለምን በመዝናኛ፣ ኪነ ጥበብ እና ማህበራዊ ዝግጅቶች ላይ አተኮሩ? እንግዲህ የፀሐፊው ውስጣዊ ዝንባሌ አንድ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ ያለው ነባራዊ እውነታ ቁንጽል ነፀብራቅም ሊሆን ይችላል፡፡ ስለ ሀቅ እንነጋገርና የጠለቁና የበሰሉ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ሐይማኖታዊ ዝግጅቶች አሉን? ኧረ በጭራሽ! ዜናን እንኳ እናንሳ፡፡ ጥሩ የዜና ዘገባ የሚቀርብበት መሰናዶ አለ? ከተለመደው ተናገሩ፣ ገለፁ፣ ተሰበሰቡ፣ ስልጠና ወሰዱ እወጃ በዘለለ የዜና ትንታኔ የሚያቀርብ፣ ተቃራኒ ድምፆችን በስርዓቱ የሚያፋልም የዜና ሰዓት አለ? 
በአንፃራዊነት የሚሻሉትን ሁለቱን ልጥቀስ፡፡ “የሸገር ወሬዎች” ሌሎች መገናኛ ብዙኃን የማይነግሩንን ጥቂት ዘገባዎች ያቀብሉናል፡፡ ጥልቅ ፖለቲካዊና ምጣኔ ሀብታዊ ማብራሪያ ግን የለውም፡፡ የፋናዎቹ “60 ደቂቃ” እና “90 ደቂቃ” የአቀራረባቸው ማራኪነት ቢያስደንቃቸውም ከደቂቃዎቹ ብዙዎቹ የሚባክኑት የማይረቡ ትርኪምርኪ የውጭ ሀገር ወሬዎች ሲዥጐደጐዱ ነው፡፡ ቀላል የሀገር ውስጥ ዘገባዎችን መከሸንን ቢካኑበትም አንገብጋቢ ጉዳዮችን አይደፍሩም፡፡ ፖለቲካዊ ሚዛናዊነት ማጣትም ሌላኛው እንከናቸው ነው፡፡ለመደምደም ያህል የበረታችሁ ይበልጥ በርቱ፤ የተደበቃቸው ድንቆች ድምፃችሁን ከፍ አድርጉ፤ ስለ ሁሉም ጉዳይ ብስል ዝግጅቶች ጋብዙን እንላለን፡፡

Read 3140 times