Saturday, 24 August 2019 13:58

ታሪክን ለታሪክ ሠሪዎች

Written by  ደረጀ ይመር
Rate this item
(0 votes)

 “የስፓኛው ፈላስፋ ጆርጅ ሳንታያና “ታሪካቸውን በቅጡ ያልተረዱ ሰዎች ያንኑ (ታሪካቸውን) ለመድገም የተፈረደባቸው ወይም የተረገሙ ናቸው” ይላል፤ ጊዜ ቆሞባቸዋል፤ አይነቃነቁም፤ አይሻሻሉም፤ እንደ ወታደር እርግጫ ባለህበት ሂድ፤ እያሉ ይኖራሉ ማለቱ ነው፡፡--”
                
       ማሟሻ
የታሪክ ሊቃውንት የሚስማሙበት አንድ አንጓ እውነት አለ፡፡ ይኸውም፤ ”ታሪክ ስለ ትላንት መጠበብ፣ መጨነቅ እንጂ፤ ትላንት አይደለም::” የሚለው ሐሳብ ነው፡፡ ለትላንት መባተት፣ ከዛሬ የሚሻገር በረከትን ይዞ የማይመጣ ካልሆነ፤መጨነቅ መጠበቡ፣ ፋይዳ ቢሰ ነው፡፡
ታሪክ ጥሎ የሚያልፋቸው ዳናዎችን በቅጡ ካልመርመርናቸው፣ ዛሬ ለቆምንበት ኅላዌ የሚያበረክትቱ አስተዋጽኦ እምብዛም ይሆናል:: ዋናው ቁም ነገር፣ የትላንትን ውጣ ውረድ፣ ዛሬ ላለመድገም፤ ታሪክን በቅንነት መመርመር እንደሚገባን ማወቁ ላይ ነው፡፡  
ከፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም “እንዘጭ እንቦጭ” ድርሳን፣ አንዲት ሰበዝ ልምዘዝ፡- “የስፓኛው ፈላስፋ ጆርጅ ሳንታያና “ታሪካቸውን በቅጡ ያልተረዱ ሰዎች ያንኑ (ታሪካቸውን) ለመድገም የተፈረደባቸው ወይም የተረገሙ ናቸው” ይላል፤ ጊዜ ቆሞባቸዋል፤ አይነቃነቁም፤ አይሻሻሉም፤ እንደ ወታደር እርግጫ ባለህበት ሂድ፤ እያሉ ይኖራሉ ማለቱ ነው፡፡”
የሳንታያና ምሁራዊ ስላቅ፣ ከውስጥ ዘልቆ የሚገባ ቁም ነገርን አዝሏል፡፡ የውድቀት አዙሪትን አሁንም አሁንም ለመድገም፤ ታሪክን እጀ ሰባራ ማድረግን ይጠይቃል፡፡ እንደ ሀገር ባለንበት ለመርገጣችን፣ የልሂቁ ተግሳጽ በልቦናችን እንዳላደረ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡
በእዝነ-ልቦናችን ያደረው ታሪክ
ፕሮፌሰር ተሻለ ጥበቡ፡- “The Making of Modern Ethiopia 1896-1974” በሚለው ጥልቅ የጥናት መጽሐፍ፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ዙሪያ ያለውን ውዝግብ ቁልጭ አድርጎ ያሳያናል፡፡ ተሻለ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ ርዝማኔ በሦስት ዘርፍ እንደሚከፈል ያብራራል፤ “የመጀመሪያው፣ የኢትዮጵያን የታሪክ ርዝመት በሦስት  ሺህ ዓመት ልክ የሚያስቀምጥ ነው፤ ሁለተኛው፣ የጊዜው ርዝመት ከአጼ ምኒልክ ጀምሮ ያለውን ዘመን ያሰላል፤ ሦስተኛው፣ እ.ኤ.አ ከ1952 ኤርትራ በፌዴሬሽን ወደ ኢትዮጵያ ከተቀላቀለችበት ዘመን ጀምሮ ያለው ውጣ ውረድ ላይ ብቻ የተቀነበበ የዘመን ስሌትን ይከተላል፡፡” ይላል፡፡
የዘመን ሥሌቱ ሌጣ አይደለም፡፡ ከእያንዳንዱ ትርክት በስተጀርባ፣ ፖለቲካዊ ተልእኮ አለ፡፡ ታሪክን በታሪክነቱ ከመቀበል ወይም ከመፈተሽ ይልቅ፤ ታሪክን ለፖለቲካ ግብ ማዋል፣ የአብዛኛው የዘውግ ብሔርተኞች አቋም ነው፡፡ ለአብነት፣ የኢትዮጵያን ታሪክ በመቶ ዓመት ልክ ቀንብበው ትርክታቸውን የሚያስተጋቡ ኃይሎች፤ ዋንኛ ዓላማቸው፣ የበቀሉበትን ዘውግ ሉአላዊነት በማስረገጥ፣ ለዘመናት የሀገራችን ሕዝቦች እርስ በርስ የተሳሰሩበትን ማኅበራዊ ድር /social fabric/ መበጣጠስ ነው፡፡
እንግዲህ፤ ሌላው ይቅርና በዘመን ስሌት ላይ አንኳን ያለን ስምምነት ጉራማይሌ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት፤ ዓለም የሚደነቅባቸውን የታሪክ ሀብቶቻችንን እንደ ዋዛ አባክነናቸዋል፡፡ የአባይ ልጅ ውሃ ጠማው እንዲሉ፤ የታሪክ ባለጠጋ ሆነን፣ የታሪክ ጠኔ አጠናግሮናል፡፡
ታሪክ የራሱን የጊዜ ቦይ ቀዶ እንዳሻው መፍሰሱን ዘንግተን፤ ያለ ሥሪቱ፣ ወደ ኋላ ተመልሰን፣ ባጠለቅነው የዘውግ መነጥር፣ እንደ ኩሬ ከትረን ልንፈርጀው ይዳዳናል፡፡ ታሪክን በታሪክነቱ ከመመርምር ይልቅ፤ ታሪክን ለፖለቲካ ግብ መጠቀማችን፣ ቋንቋችንን እንደ ባቢሎዊያን ድብልቅልቅ አድርጎብናል፡፡ ትላንት ፀጉር ሰንጥቀን እንደ ዋዛ የዘራነው የተዛባ ትርክት፤ ዛሬ ዋርካ ሆኖ በፍሬው እያሳመመን ነው፡፡ በያ-ትውልድ ልቦና ላይ ያደረው መናኛ ትርክት፤ ለዛሬ የፖለቲካ ሲራራ ነጋዴዎች፣ ጥሩ ስንቅ ሆኖ እያገለገለ ነው፡፡
ታሪክን እንደ 1960ዎቹ ትውልድ የበደለ የለም ቢባል፣ እውነታውን ማበል አይሆንም፡፡ ያ-ትውልድ ትላንትናችንን በቁጭት ማእቀፍ ውስጥ ቀንብበን፣ እየረገምነው እንድንኖር ፈርዶብን ኖሯል:: በተምኔታዊ ገዳም ውስጥ ተከልለን፣ አንዳችን በሌላኛችን ላይ ምንም ዓይነት አሻራን ሳናሳርፍ፤ ዘመናትን እንደ ተሻገርን የሚሰብክ የተዛባ ትርክት የተበጃጀው በያ-ትውልድ መዳፍ ነው፡፡ ትላንት ታሪክን ያለ ስሪቱ ስለበደልነው፣ ዛሬ እዳውን እንደ ሕዝብ እያወራረድን እንገኛለን፡፡
በደብተራዊ (በቃል የማነብነብ) የእውቀት ባህል ተኮትኩቶ የጎለመሰው የ1960ዎቹ ትውልድ፤ በዘመኑ የገጠመውን ፈተና ለማለፍ የዘየደው መላ፣ባእድ ትንታኔዎችን እንደ ወረደ ማጥለቅ ነበር፡፡ በካርል ማርክስ ፍልስፍናዊ ዕይታ ላይ እንደ ገዢ ሆኖ የቀረበው የጨቋኝ መደብ (ከበርቴው) እና የተጨቋኝ መደብ (ላብአደሩ )፤ባልተገባ መልኩ የሀገራችንን የኋላ የሕዝቦች ትስስር ለመተንተን ውሏል፡፡ በጨቋኝና በተጨቋኝ ፍረጃ ምከንያት፣ በሕዝቦች መካከል “የበርሊን ግንብ”ን ሊተክል ችሏል፡፡ አብረን ወድቀን ከተነሳንባቸው ትላልቅ  የታሪክ ገድሎች ይልቅ፤ በጥቃቅን እንከኖቻችን እየባከንን ከዛሬ ላይ አድርሶናል፡፡
የዛሬ ቆፈን
አሁን እርስ በርስ የሚያናክሰን ሕገ መንግሥት፤ እንደ ማእዘን ድንጋይ የተጠቀመው እሳቤ የተበጃጀው፣ ያ-ትውልድ ባኖረው ጡብ ነው፡፡ በመንደርደሪያው፤ በብሔሮች መካከል የነበረውን የተዛባ ግንኙነት ለማረቅ የተዘጋጀ ሰነድ እንደሆነ ያትታል፡፡ የተዛባው ግን፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ሳይሆን፤ የታሪክ ዕይታችን ነው፡፡
ሀገራችን ያለፈችበት የኋላ ዘመን ሐዲድ፣ በሌላው ዓለም ፊት ባይተዋር አይደለም፡፡ መውደቅ፣ መነሳት የሁሉም ዓለማችን ሕዝቦች መገለጫ ነው፡፡ ጠንካራው ደካማውን እያሸነፈ፤ ተሸናፊው የአሸናፊው ወገንን ባህል፣ ቋንቋና እምነት በሙሉ እየተቀበለ፤ ሕዳጣኖች በገናናዎች እየተዋጡ ነው፣ ከዚህ ዘመን ላይ የደረሱት፡፡ ስለዚህ በእኛ ላይ የወረደ የዘመን መርገም የለም፡፡ ይህን ትስስር የተዛባ ብሎ መፈረጅ፣ ታሪክን እጀ ሰባራ ማድረግ ነው፡፡
ዛሬ፣ በታሪክ ገቢሮት /fact/ አይደለም እየተጓዝን ያለነው፡፡ በያ-ትውልድ የተዘራው ብሔራዊ ጭቆና የሚለው ልብ ወለዳዊ ትርክት፣ ፍሬ አፍርቶ በልዩነት ጫካ ተወረናል፡፡ የፋይናንስ፣ የእምነትና የማኅበራዊ ተቋማት በሙሉ፣ በዘውግ ጠረን የታወዱ ናቸው፡፡
የእውቀት ቧለሟሎችን ለፍሬ እንዲያበቁ የተቀለሱት መካነ-አእምሮዎቻችን፤ ማብሰልሰያው የመከነ፣ በፖለቲካ ነጋዴ እንዳሻው የሚጋለብ፣ ቡክን ትውልድን ለዐይነ ሥጋ በማብቃት፣ ለክሽፈቱ የድርሻቸውን እየተወጡ ነው፡፡
ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት፣ እንደ ሀገር እንደወደቅን የሚገባን፣ በእነዚህ ዘመናት ውስጥ የተፈራውን ታሪኩን ጠንቅቆ የማያውቅ፣ ግልብ ትውልድ ዞር ብለን ስንገመግም ነው፡፡ የመጽሐፍን አንዲት ቅጠል አንብቦ ከመደመም ይልቅ፤ የዘውግ ብሔርተኞች በየማኅበራዊ ሚዲያው፣ የሚያስተጋቡትን ቅንጭብ ጩኽቶች እየቃረመ የሚታበየው፣ ቁጥሩ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ታሪክን የመሰለ አንድን ሀገር ያቆመ ጉልላት የሚቀለሰው እንግዲህ፣ በዘመኑ የዘውግ ነጋዴዎች ነው፡፡ የዘውግ ማንነትን ማእከል ያደረጉ ትርክቶች ዘረ-መል፣ ተለንቅጦ የሚሠራው ደግሞ፤ በሴራ ንድፈ-ሐሳብ እንደሆነ ይታወቃል:: ይህንን የፖለቲካ ሸር መረዳት የተሳነው፣ ታሪኩን የማያውቅ፤ የትላንቱን ውድቀት የሚደግም፣ የባከነ ትውልድን ለመመልከት እንደተገደድን ማንም የማይክደው ሐቅ ነው፡፡
ሕዳግ
በትላንት ገመናዎቻችን መቋሰል፤ ባለንበት ተቸንክረን፣ ከማዝገም በዘለለ፣ አንዲት ጋት ፈቀቅ አያደርገንም፡፡ ታሪክን ወደ ኋላ ሄዶ ማበጃጀት አይቻልም፡፡ ይህ ለምን ተከሰተ ብሎ መብከንከን፣ በታሪክ ፊት የዋህ ያስብላል፡፡ ያለን ብቸኛ አማራጭ፣ ኹነቱን እንዳለ በጸጋ ተቀብሎ፤ ከዛሬ የሚሻገር ሥራ ለመሥራት፣ ከትላንት ገመና መሰነቅ ነው፡፡
ልሂቆቻችን የሀገራችንን ታሪክ በአግባቡ ፈትሸው፣ ለአውደ ርዕይ በማቅረቡ ረገድ ስኬታማ አልነበሩም፡፡ በታላላቅ መሪዎቻችን ተጋድሎ ዙሪያ ብቻ የተቀነበበ አስተምህሮት፤ ውስብስቡን የሕዝቦች መስተጋብር ሙሉ ስእልን ሊያሳይ አይችልም፡፡ የታሪክን ሁለንተናዊ ቁመናን ለመረዳት፣ የክስተቱን ዙሪያ ገባ መመርመር የሚያስችል ሥነ-ዘዴ መከተልን ይጠይቃል፡፡ ይህ ካልሆነ፤ ምንም ፍሬ አይኖረውም፡፡
ፕ/ር ተሻለ ጥበቡ እንደሚለው ከሆነ፤ ታሪክን የከተቡት የእውቀት ባለሟሎቻችን የተከተሉት ሥነ-ዘዴ፤ የሀገራችንን ሕዝቦች የዘመን አሻራን፣ በቅጡ መርምረን ወደፊት የምናማትርበትን አስተውሎት አላጎናጸፈንም፡፡
የዘመን ውጣ ውረዶችን ከመዘገብ ባለፈ፣ ትክክለኛውን መስተጋብራችንን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳያን ድርሳንን እስካሁን ለመመልከት አልታደልንም፤ ይላል፡፡ “A theoretically-framed social history of Ethiopia has not yet been written.” (በንድፈ ሐሳብ የተዋቀረ የኢትዮጵያ ታሪክ እስካሁን ተከትቦ አያውቅም፡፡)
በታሪክ ሰሪዎቹ ዙሪያ ብቻ የተገደበ ግንዛቤ፣ ፀረ-ምሁራዊ የልቦና-ውቅር ነው፡፡ ታሪክ የተከወነበት ሰፊው ማኅበረሰብ፤ ማኅበራዊ፣ ሥነ-ልቦናዊና ፖለቲካዊ ትሥሥርን ይፋ ማውጣት ካልተቻለ፤ የኋላው ገመናችንን ጓዳ ጓድጓዳ ማወቅ ይሳነናል:: ታሪክን ለታሪክ ሰሪዎች የምንተውበት፤ ትላንት ያጋጠሙንን ከፍ ዝቆች በሚገባ የምንፈትሽበት፤ የዛሬን ፈተና የምናልፋባቸውና ለነገ ስኬት የምንሰናዳባቸው፣ ግሩም ምሁራዊ ሥራዎችን ወይም ድርሳናትን፣ ከልሂቆቻችን ገና ብዙ እንጠብቃለን፡፡


Read 1897 times