Saturday, 24 August 2019 13:54

የፍሬዓለም “ላስብበት” መጽሐፍ ብዙ አሳሰበኝ!

Written by  ደ.በ
Rate this item
(0 votes)


            በኢትዮጵያዊ የሥዕል ሽፋን፣ “ላስብበት” በሚል ርዕስ የተዘጋጀችው መጽሐፍ፤ በወስጧ የያዘቻቸው ሀቆች፣ ፍልስፍናዎች፣ አተያዮችና ህልሞች፤ ሀገርን የመለወጥ አቅም ይኖራቸዋል ብሎ የሚገምት ሰው ያለ አይመስለኝም፡፡
ምናልባት ወይዘሮ ፍሬህይወት ሽባባውን ቀደም ባሉ የአቅም ግንባታ የህፃናት የምግብ መብት ተሟጋችነት የሚያውቃት ወይም “ተምሳሌት” በሚለው ታላላቅ የስኬታማ ሴቶች የህይወት ታሪክ ጥራዝ ታሪኳን ያነበበም፣ አሊያም በቴሌቪዥንና በሬዲዮ ንግግሯንና አስደናቂ ህልሟንና ተግባሯን ያልሰማ ሰው እንደዋዛ ሊያልፈው ይችላል፡፡ ..ግን በምንም ዐይነት፣ ማንም ሰው መጽሐፉን ካነበበ በኋላ አንዳች የታሪክ ቁፋሮ፣ የዘመን ልኬት፣ የመሪዎቻችንን መደንዘዝ… ፍተሻ ውስጥ ይገባል፡፡ የመንግስት መዋቅር ላይ የተንጠለጠሉ ድንዙዞች፣ ሞት የሚያዘፍናቸው ሰነፎች፤ ያገርን ህልም ባባቶች ወግ ጫንቃ ላይ እንጂ በህፃናት ህልም ላይ መተለም ያቃታቸው ከንቱዎች እንደሆኑ እናያለን፡፡
መጽሐፉ ገራሚ የሚሆንበት አንዱ ምክንያት ሀሳቦቹ ከልጆች ጥያቄዎች ላይ የተመዘዙ መሆናቸው ነው፡፡ ከልጆች ጥያቄ የተነሱት ግዙፍ ሀሳቦች፤ የሀገራችንና የክፍለ አህጉራችን መዘዞች ምንጭ ሆነው ይገኛሉ፡፡ ያንን አዳፋ ታሪክ እያበጀ፣ መቂያጥ ውስጥ እንዳሉ የማይረባ ፈትል፣ ከግራ ቀኝ የሚወረወረው የድህነት ቅብብላችን በጣም ፍንትው ብሎ እንዲታይ ያደርጋል፡፡
ለምሳሌ የመጀመሪያው ጥያቄ፤ ከደራሲዋ ሁለተኛ ልጅ የተነሳ ነው፡፡ ቤታቸው ውስጥ ለእንግዳ ክብር ሲባል የሚዘጋጅ ምግብ፣ የሚፀዳ ክፍል፣ የሚስተካከል ግቢ ለቤት ሰዎች ለምን እንደማይፈቀድ ያስተዋለችው ልጅ፤ “እግዚአብሔር እንግዳ ብቻ ነው የሚወደው?” ያለቻትን ጥያቄ ፍሬዓለም እያሰላሰለች ወደ ሀገር ታሳድገዋለች፡፡ ልጅዋም ሆነች ልጆች በጠየቋት ቁጥር “ለስብበት” ማለት የምትወደው ፍሬዓለም፤ የልጆችን ጥያቄ በቸልተኝነት መመለስ አትፈልግም፤ ምክንያቱም ለልጆች ያላት ቦታና ግምት፣ በማህበረሰባችን ከተለመደው በእጅጉ የተለየ ያለ ነው፡፡
የእንግዳን ጉዳይ ወደ ሀገር ከፍ ከማድረጓ በፊት በሳሎንና በኩሽና መካከል ያለውን ትነካካለች፡፡ ሳሎን ለእንግዳ ስለሆነ በከፍተኛ ጥንቃቄ ሲያዝ፣ ምግብ የሚዘጋጅበት ክፍል ግን የተርመጠመጠ ነው፡፡ ዋናውና ከጤናም ከህይወትም ጋር የተያያዘው የራስ ጉዳይ ግን ቸል ተብሏል፡፡ እንግዶች መጥተው መንገድ ሲዘጋ፣ ለእንግዶች ተብሎ ስራ ሲበላሽ ግድ የለም፡፡
ይህንኑ ሀሳብ በሀገራችን ያሉ ኤምባሲዎች፣ ለራሳቸው ዜጐች ካላቸው ክብር፣ ለእኛ ለእንግዳዎች ካላቸው ዝቅ ያለ ግምት ጋር ትሠፋዋለች፡፡ ቪዛ ለማስመታት ሲኬድ ያለውን ፍዳና እንግልት፣ የሰነድ ጥያቄ ብዛት ታሰላዋለች፡፡ ታዲያ ሰው በገዛ ሀገሩ ካልተከበረ፣ ክብሩ የት ይሁን? እያለች ነው፡፡ የኛ ቤት የእንግዳ ቤት፣ የኛ ሀገር የእንግዳ ሀገር ነው ይህ ደግሞ ሥር የሰደደ በሽታችን ነው፡፡ በዘመነ ምኒልክና ኃይለሥላሴ የፈረንጅ ሀገር ትምህርት ተምረው የመጡት ፊታውራሪ ተክለሃዋርያት ተክለማርያም የገጠማቸው ፈተና ይኸው ነበር:: ሀገር ገብተው የሀገር ባህል ልብስ ሊለብሱ ሲሉ፣ ዘመዶቻቸው “የፈረንጁን ልብስ ይንቁሀል” ነበር ያሏቸው፡፡ የፈረንጁን ልብስ ለብሰው ከበቅሏቸው ሳይወርዱ ሲገቡ፣ ክብሩ ሌላ ሆነ፡፡ እንዲያውም ሲገቡ በአክብሮት ሰላም ካሏቸው ታላላቅ መኳንንት አንዱ ካለፉ በኋላ፤ ማንነታቸውን ጠይቀው፤ “ውጭ ሀገር ተምረው የመጡ ኢትዮጵያዊ ናቸው፡፡” ሲባል እንደናቋቸው ጽፈውታል፡፡ እንግዳ እንጂ ያገር ልጅ የማያከብረው ልማድ የተወለደው ጐጆዋችን ውስጥ ነው፡፡
ሌላኛው ጥያቄ ባህርዳር በሚገኘው የፍሬዓለም ትምህርት ቤት፣ ከተማሪ የተነሳ ጥያቄው ነው:: (በነገራችን ላይ ፍሬዓለምና ቤተሰቦቿ የከፈቱት ትምህርት ቤት እጅግ ዘመናዊና በርካታ ተማሪዎችን ለውጤት ማብቃቱ በተደጋጋሚ የተመሰከረለት ነው፡፡)
የልጁ ጥያቄን በጽሑፍ እንዲህ አሥፍራዋለች፡-
“ሚስ ጥያቄ መጠየቅ እችላለሁ?” አለኝ፤ ሰውነቱ ፈርጠም ያለ፣ ጠይም ጠጉረ ሉጫ ነው፡፡
“እንዴ በሚገባ!” አልኩት፡፡
“ሚስ፤ ዲሞክራሲ ማለት ምን ማለት ነው?” አለኝ፡፡
ቀጥሎ ያስከተለው ጥያቄ ደግሞ፤ “ይኼ መንግሥት ዲሞክራሲያዊ ነው ወይስ አይደለም?” የሚል ነው፡፡
የራሷን ሃሳብ ልትጭንበት አልፈለገችም፤ ነገ እሱም በተራው በሌሎች ላይ ሃሳቡን እንዳይጭን ፈርታለች፡፡ መለስ ብላ ስትፈትሽ ግን ለ“ዲሞክራሲ” አቻ ትርጉም ያለው ቃል እንኳ የለንም፡፡ የአምስተኛ ክፍል የስነ ዜጋ መጽሐፍን ገለጠች፤ “ዴሞስ” ማለት በአንድ ሀገር የሚኖር ህዝብ ነው፡፡ “ክራቶስ” ደግሞ ሥልጣን ወይም አመራር ነው፡፡ ቃሉ ከግሪክ የተገኘ ነው፡፡ ዲሞክራሲ የሚለው ቃል፤ ስልጣን የህዝብ የሆነበት አስተዳደር ማለት ነው፡፡
ፍሬዓለም፤ ይህንን ሃሳብ አብላላችው “እቤት ውስጥ ያልተለማመድነውን ባህል አደባባይ ላይ መተግበር እንችላለን እንዴ?” አለች፡፡ “የቤተሰቡን የማሰብ ነፃነት፣ የመምረጥ ነፃነት፣ የህይወት አቅጣጫን የመወሰን ነፃነት የሚነፍግ ሰው፤ የመሪነት ቦታ ላይ ቢቀመጥ የህዝብን ነፃነት የሚያከብርበት ባህል አለው?” የሚስቱን መብት በቤት ውስጥ የማያከብር ሰው የሌሎችን ሰዎች መብት ያከብራል?”
ይህን ጉዳይ ለመለወጥ በተቋም ደረጃ ከሞከርን አያዋጣም ትላለች፡፡ መጀመያ ባህሉ መታከም አለበት፡፡ 1በአገራችን ፈውስ የሚያስፈልጋቸውን ጉዳዮች ለመፈወስ፣ ፈዋሾች አጥተን አይመስለኝም፡፡ ችግሩ ፈዋሾች፤ ፈዋሽ ሃሳቦቻቸውን የሚተገብሩበት ቦታ አለማግኘታቸው ይመስለኛል፡፡  ፈዋሾች ስራቸውን እንዲሰሩ የሚፈቅድ ባህልና አስተሳሰብ በሌለበት ፈውስ አይካሄድም፡፡” (ገጽ 4፡፡)
ለልጁ ብቻዋን መልስ እንዳትመልስለትና የሚመለከተውን ክፍል አብረው እንደሚያናግሩ የሄደችበትና ያንን ለማድረግ ያነሳሳት ምክንያት በእጅጉ የሚደነቅ ነው፡፡
“ለሚጠይቀው ጥያቄ ሁሉ መልስ እንደሌለኝ ማሳወቄ የዚህ ስልጠና ዋነኛው አካል አድርጌ የምቆጥረው ነው፡፡ እሱ አድጐ ትልቅ ቦታ ደርሶ ወይም የሀገር መሪ ሆኖ ለሁሉ ጥያቄ መልስ መስጠት አለብኝ ብሎ የሚያስብ ልጅ እንዲሆን በጭራሽ አልፈልግም፡፡” ትላለች፡፡ “ስለማያውቀው ነገር የሚተነትን ደፋር፣ እውነታዎችን የማይመዝን በግምትና በስሜት የሚነዳ እንዲሆን አልፈልግሁም::” (ገጽ 26፡፡)
ትልልቅ መሪዎች የሚፈጠሩት ከትምህርት ቤት እንደሆነ ታምናለች፡፡ በርግጥም ልክ ናት፡፡ ለምሳሌ በቅርብ ዓመታት ከነበሯት መሪዎች የተሻለ ክብርና ውጤታማነት ተጐናጽፈዋል ከሚባሉት የአሜሪካ መሪዎች አንዱ የሆኑት፣ ሮናልድ ሬገን፣ ትልቁ ችሎታቸው ይህ ነበር፡፡ እርሳቸው ሊሠሩት የሚገባውን ብቻ ይሠራሉ፤ ሌላውን ለሌሎች ያሳልፋሉ (Delegate) ያደርጋሉ፡፡ ሁሉ ላይ አይንጠላጠሉም፡፡ የደርግ ትልቁ ስህተት በካድሬ ሃምሳ አለቃ፣ የጀኔራል ጦርነትን ለመዋጋት መሞከር ነበር፡፡
አንዳንድ መምህራን ግን በቀላሉ ዴሞክራሲያዊ ለሆኑ ሀገራት አሜነካንን፣ በምሳሌነት ሲያቀርቡ፣ ዴሞክራሲያዊ ላልሆኑት ኢትዮጵያን ይጠቅሱ ነበር በማለት ትገልፃለች፡፡ ይህንን ግን አትቀበለውም:: ልጆቹ ራሳቸው የመመዘንና የመፈተሽ አቅም እንዳያገኙ ያደርጋል ትላለች፡፡ ነገም የራሳቸውን ሃሳብ በሌሎች ላይ ለመጫን የማይመለሱ እንዳይሆኑ ትሠጋለች፡፡
ደራሲዋ የዚህ ዓይነት ሥልጡን ሃሳቦችንና ድፍረቶችን አሜሪካ ሀገር ኮሌጅ ተማሪ በነበረችበት ጊዜ ያገኘችው ይመስለኛል፡፡ ያኔ ቤተሰብ ያደረገቻት አሜሪካዊ ጋዜጠኛ፣ ከሃገሯ ይዛ የሄደችውን የዝምተኝነትና ያለመጠየቅ አይነጥላ ገልጣላታለች የሚል እምነት አለኝ፡፡ ቀናነትና ርህራሄዋም ምናልባት ከቤተሰብና ከአደገችበት አካባቢ የወረሰች ይመስለኛል፡፡ መጽሐፉ ውስጥ የሚታየው ይኼ ነው፤ ለሁሉም እኩል ማዘን፣ በሌሎች ጫማ ቆሞ ማየት፡፡
ሌላው ግዙፍ ጥያቄ፣ የባህርዳሩ ተማሪ፣ መምህሩን የጠየቀው ነው፡፡ በዚህ ሰዓት የመጽሐፉ ደራሲ ክፍል ውስጥ ተቀምጣ እየታዘበች ነበር፡፡
“ቲቸር አባይ ነው ወይስ ኢትዮጵያ መጀመሪያ የተፈጠረ፣ ወይም የነበረ ማነው?” ብዙ ተማሪዎች ሳቁ፡፡ እርሷ ደነገጠች፡፡ “What a genius!” አልኩ - ትላለች፡፡
“ሁላችሁም በየቤታችሁ አንብባችሁ ወይም ሰው ጠይቃችሁ ኑ!” አልኩና መምህሩን ይዤው ወጣሁ::” (ገጽ 31፡፡)
ታናሽ እህቷ እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) ያዜመችውን ያስታወሰችው ይሄኔ ነበር!-
ገና ከጥንት አዳም ገና ከፍጥረት
የፈሰሰ ውሃ ፈልቆ ከገነት
አባይ… አባይ… አባይ… አባይ
የበረሃው ሲሳይ የበረሃው ሲሳይ
አባይ ወንዛወንዙ… ብዙ ነው መዘዙ፡”
ብዙ አሰበች፤ ወደ ብዙ የታሪክ መጻሕፍት ሄደች፡፡ ተማሪዎችም የአባይን ስዕል ስለው እንዲመጡ ነገረች፡፡ ሒትለር የጀርመንን ተማሪዎች ቁጭት ውስጥ ያስገባው በዚህ መንገድ ነበር፡፡ በአንደኛው የዓለም ጦርነት የተነጠቁትን የጀርመን ግዛቶች እንዲያሰሉ በሂሳብ ትምህርት ውስጥ በማካተት ነበር ጦርነቱን ያስፀነሱት፡፡
ፍሬዐለምም የአባይን ልብ ውስጣቸው ለመክተትና በጽኑ ለማሳሰብ ፈልጋለች፡፡ ግብጽን ከመሠረቷት ይልቅ ኢትዮጵያን የመሠረቷትን አደነቀችና ጥበበኞች ናቸው አለች፡፡ (ገጽ 32) “የአባይ ምንጭ ላይ ሀገር መመስረት በጣም ብልህነት ነው፡፡  ግብፆች የሚተዳደሩበት ውሃ 90% ከኢትዮጵያ የሚገኝ ነው:: ለሱዳኖችም ብቸኛ የውሃ ምንጫቸው ነው፡፡ ዐባይ የኢትዮጵያም ዐቢይ ጉዳይ ነበር” ትላለች፡፡ (ገጽ 34) “አፄ ኃይለሥላሴ፤ ገና አልጋ ወራሽ እያሉ፣ ንግስት ዘውዲቱ የኢትዮጵያ ንግስት በነበሩበት ጊዜ ከእንግሊዝ መንግስት ጋር ካደረጓቸው ውይይቶች ውስጥ  አንዱ የአባይ ጉዳይ እንደነበር ጠቅሰዋል:: በቀዳማዊ ኃይለሥላሴም ጊዜ የመገደብ ሃሳብ እንደነበር መጽሐፉ ይገልፃል፡፡ ኢትዮጵያና ግብጽ በአንድ መንግሥት ስር እንደነበሩም ትነግረናለች፡፡ የላይኞቹ (ኢትዮጵያ) አስገባሪ፣ የታችኞቹ (ግብጽ) ገባሪ ሆኑ፡፡ ተክለጻዲቅ መኩሪያን፣ የግሪኩ ፈላስፋ ሄሮዱትስ ፍሬዴሪክ ቲ.ቦልተንን ፣ ፕላንትና ፕላየንትን ትጠቅሳለች፡፡
የዛጉዌ ስርወ መንግስት፣ የሸዋው አምደጽዮንና ሌሎቹም ነገሥታት ዐባይን እንደ ማስፈራሪያ በመጠቀም የተለያዩ ጥቅሞቻቸውን ለማስከበር ሞክረዋል፡፡
ይህ ሁሉ ፖለቲካ የተወራው ከልጁ ጥያቄ በመነሳት ነው፡፡ የሀሳቡ መዝለቂያም ዛሬ ላለንበትና ለነገውም የሚጠቅሙ ትሩፋቶች የሚያስቀምጥ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ የቤት ሥራ ከተሰጣቸው ተማሪዎች አብዛኛዎቹም፣ ዐባይን በጋራ መጠቀም ዘላቂ መፍትሔ እንደሆነ ተስማምተዋል፡፡
“ህግ አስፈላጊ ነው ብዬ አላምንም” የሚል ሌላ ተማሪም፣ ወይዘሮ ፍሬዐለም ቢሮ ብቅ ብሎ ሞግቷታል፡፡ ይህ ጥያቄ ደግሞ ወደ ጠለቀ ምርምርና ፍተሻ ወስዷታል፡፡
ልጁ “የደንብ ልብሱን አልለብስም!” በማለት ነው ያመፀው፡፡
“ከልብሱ ጋር ነው ችግርህ?” በመገረም ጠየቅሁት፡፡
“አይ አይደለም፡፡ ከሕጉ ጋር ነው ችግሬ፡፡ እኔ ሕግ ለሰው ልጆች ያስፈልጋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ሕግ የሰው ልጆች ነፃነትን ይነፍጋል፡፡ ሰዎች የሚፈልጉት አይነት ሕይወት በነፃነት እንዲኖሩ ተፈጥሮ የሰጣቸው መብት ነው፡፡ ሕግ ለምን ያስፈልጋል?” ሲል ጠየቀ፤ ቁጣ በተቀላቀለበት ድምፀት፡፡
“ስለዚህ አንተ የሰው ልጆች ሕግ አያስፈልጋቸውም እያልክ ነው?” አልኩት፡፡
“አዎ፡፡ እሱ ብቻ አይደም፤ ሕግ እንኳ ቢያስፈልግ እኛ ተስማምተን ህግ ማውጣት ሲኖርብን፣ እንዴት ባረጀና ባፈጀ ሕግ እንተዳደራለን? በአጠቃላይ ግን ሕግ ጨቋኝ ነው፡፡ ስለዚህ ሕግ አያስፈልግም የሚል አቋም ነው ያለኝ፡፡”
“ድፍረቱ አስደሰተኝ፡፡ በራስ መተማመኑ አስገረመኝ፡፡” ትላለች ፍሬዓለም፡፡ ግን ሌሎች መምህራን ቢገጥሙትስ? “ይህ ልጅ ጥጋበኛ፣ ደፋር፣ ባለጌ ያሳደገው ነው፤ ሌሎችን እንዳያበላሽ ይወገድ! ወይም ማስጠንቀቂያ ሊሰጠው ይገባል፡፡” ማለታቸው አይቀርም ነበር ብላለች፡፡  
አሜካዊው የኮንኮርድ ፈላስፋና ደራሲ፣ በዚህ ቁጭት ነበር የራሱን ትምህርት ቤት የከፈተው፡፡ በዚያ ዘመን እንኳ (በ1841) ገደማ ተማሪዎች እርሱ ትምህርት ቤት አይገረፉም፡፡ ከቅጥር ግቢው ውጭ ወጥተው ከተፈጥሮ ጋር ይተዋወቃሉ፡፡ ሀርቫርድ በመረቅም ሀርቫርድን አይወድደውም፤ ህግ ልማድ፣ የተለመዱ ነገሮች ይሽከረከሩባታል፡፡ “One man is important the crawd is not” በመባልም ይታወቃል፡፡ እንደ ባህርዳሩ ተማሪም፤ “A man has a right to disobey” ይል ነበር፡፡ ልዩነቱ ትልቅ ሀገር መፈጠርና ደሀ ሀገር መፈጠራቸው ነው፡፡
ገጽ 44 ላይ ፍሬዓለም ከትራፊክ ጋር የገጠመችው ግብግብና ትግል፤ እኛ ሀገር ህግ፣ ስሙ ብቻ እንጂ በሰዎች ፍቃድ የሚጠመዘዝ እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡ የሰው ልብ ከህጉ ጋር መቀየር አለመቻሉ ይቆጫታል፡፡ (ገጽ 45) የሕጉ እሳቤ፤ ሰፊ ትንታኔና ገጠመኞች የተካተቱበት ጥልቅ አካሄድ ነው፡፡
በአፍ መፍቻ ቋንቋ መማር በሚለው ሃሳብ የተነሳ፣ በትምህርት ቤቷ፣ ከባለሥልጣናት ጋር የገጠማት ሙግት፣ ብዙ ገራሚና አስተማሪ ነገሮች ይገኙበታል፡፡ ለምሳሌ “Digestive system” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል” “ስርዓተ እንሸርሸሪት” በሚል ተተርጉሞ፣ ተማሪዎችን ግራ አጋብቷል ትላለች፡፡ ይህ ሀረግ በሆድ ውስጥ ምግብን የመፍጨትና የመቀላቀል ስርዓትን የሚገልጽ ነው:: እንዲህ ስትልም ትሞግታለች “በአማርኛ ሆዴ ውስጥ የምግቡ እንሽርሽሪት አልሰራ ብሎ ወይም አልንሸራሸር ብሎ ሲባል ሰምቼ አላውቅም፡፡ ምግብ አልፈጭ ብሎ ነው የምንለው፡፡ ታዲያ “የምግብ መፍጫ ስርዓት” ብንለው፣ ለተማሪዎች ስሜት አይሰጥም ነበር?” በማለት ችግሮቹን ነቅሳ ታሳያለች::
መጽሐፉ ውስጥ እንደምናየው ብዙ ሙግቶች፣ ብዙ ትግሎች አድርጋለች፡፡ በተለይ ባዶ የምሳ ዕቃ ይዞ በሚመጣው የትምህርት ቤቷ ተማሪ፣ እንባዋን ከማፍሰስ ባሻገር ልጆችን ለመታደግ ተነስታ “የኢትዮጵያ ስኩል ሚል ኢንሽየቲቭ” በማቋቋም በርካታ ልጆችን ከሞትና ከረሀብ ታድጋለች፡፡ “የሰቆጣው ስምምነት” በሚል ፕሮግራሟ፤ ብዙ ገበሬዎችንም ከድርቅ አደጋ፣ ከሞት ታድጋለች፡፡ በአሜሪካ ቆይታዋ በምትሠራበት ትልቅ ሬስቶራንት  ዝነኛው የቅርጫት ኳስ ተጫዋቹን ማይክል ጆርዳንን አግኝታው፣ ባለማወቋ ተገርመውባታል፤ ተናደውባታል፡፡
የፍሬዓለምን መጽሐፍ ያነበበ ሰው፤ የዚህች ዐይነት ታላቅ ሴት እንዴት ሀገርን ከሚለውጥ የሥልጣን እርከን ላይ አልተቀመጠችም እንዲል ይገደዳል፡፡ ይህቺ ጀግና ሴት፣ በተለያዩ ሀገራት ለተማረቻቸው ትምህርቶች፣ ምናልባትም የጥበብ ችቦ ከነደደበት ቤት ተወልዳ፣ በዚህ ቀና መንፈስ ከቢሮክራሲው ጋር ተፋልማ፣ ይህንን ያህል ከሰራችና ውጤት ካመጣች፣ በፍቃድዋ ሥር የሆነ፣ ዕቅድ አውጥታ የምትሠራበት ተቋም ቢሰጣት፣ የሀገራችንን አንድ መልክ መቀየሯ ይቀራል? በፍፁም! እዚህ ሀገር ስላለው ነገር ሁሌ ትዝ የሚለኝ፣ የዮሐንስ ገብረመድህን ግጥም አለ፡፡
ሁሉን በትክክል እንይ ከተባለ
በቦታው ላይ ማንም የለም
ያለቦታው ሁሉም አለ፡፡

Read 917 times