Sunday, 25 August 2019 00:00

ሌላ ሞት የማንሰማበት ዓመት!

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

 ከአሥራ ስምንት ቀናት በኋላ አዲሱ ዓመት 2012 ይገባል፡፡ በዘመናችን ሙሉ ስናደርግ እንደኖርነው ሁሉ፤ አዲሱ አመት ለዘመዶቻችን፣ ለጓደኞቻችን፣ ለሥራ ባልደረቦቻችን፣ በሰፊውም ለሀገርና ለወገን የደስታና የብልጽግና ዓመት እንዲሆን መልካም ምኞታችንን መግለፃችን አይቀርም፡፡
በ2011 አዲስ ዓመት መጀመሪያ ላይም የተለመደውን በጐ ምኞት አቅርበን ነበር፡፡ በጐ ምኞታችንን ሰዎችም እግዚአብሔርም የሰሙት ግን አይመስለኝም፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ዓመቱ የግጭት፣ የደም መፋሰስ፣ የመፈናቀል፣ የሞትና የስደት ዓመት ሆኖ አልፏል፡፡ ዘርን መሠረት ባደረጉ ግጭቶች፣ ዜጐች ለሞትና መፈናቀል ተዳርገዋል፡፡
መከራው እንደ ጐርፍ በሚፈስበት አካባቢ የተገኙ ሰዎች፤ መከራውን ከነሙሉ ክብደቱ ይሸከሙት እንጂ ከዚያ አካባቢ የራቁት፣ የእነሱም የሥጋ ዘመዶችና አብሮ አደጐች ሆኑ ወይም ዜናውን የሰሙ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ (እኔንም ጨምሮ) ሰላም ነበራቸው ማለት አይቻልም፡፡ ሁሉም እንዲህ ዓይነቱ ክፉ እጣ፣ እሱ በሚኖርበት አካባቢ ተፈጥሮ፣ እንደ ሌላው ወገኑ የሰላም ማጣት እንዳይገጥመው እየሠጋ ነው ዓመቱን በማጠናቀቅ ላይ ያለው፡፡
ስለ ሰላም ለመስበክ እናቶች ዘጠኙን ክልሎች አዳርሰው፣ ተንበርክከው ስለ ሰላም ቢማፀኑም፣ የሉሲ ቅሪት አካል፣ ከክልል ክልል ቢዞርም፣ የሚፈለገውን ሰላም ግን አላመጣም፡፡
ስደት መፈናቀልና፣ ሞት እንደ ማርያም ፅዋ ‹‹ማነህ ባለ ሳምንት›› እያሉ አገር ሲያዳርስ ነው የከረመው:: ከሌላው የበለጠ ተደጋጋሚ አደጋ የደረሰባቸው ደግሞ አማራና ቤንሻንጉል ክልሎች ናቸው፡፡ እዚህ ሰውን መግደል ጐመን ከመቀንጠስ እኩል ሊሆን ምን ቀረው ብሎ ለመጠየቅ ይዳዳል፡፡
ሰላም ከጠፋባቸው አካባቢዎች ውስጥ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ማለትም ዩኒቨርሲቲዎች ይገኙበታል፡፡ ዩኒቨርስቲዎች ከመላ አገሪቱ የተሰባሰቡ ልጆች የሚማሩባቸው ተቋማት ናቸው:: ከእያንዳንዱ ቤት የመጡ ልጆች ተገናኝተው፣ የሰዎች መከማቻ ኩሬ ወይም ባሕር ያደረጓቸው ተቋማት ናቸው፡፡ ኩሬ ወይም ባሕር ውስጥ የገባ ጠብታ ውኃ፣ እንኳን ሌላው ራሱን ፈልጐ ማግኘት በከበደው ነበር፡፡ እነሱ ዘንድ ግን ላለፈው ሃያ ሰባት ዓመታት በተዘራው፣ በበቀለውና በገነገነው ዘረኝነት የተነሳ እያንዳንዱ ተማሪ፣ ራሱንም ሌላውንም የሚያውቀው፣ የሚተዋወቀው በሰውነቱ ሳይሆን በዘሩ ነው፡፡
በየዩኒቨርስቲው ያሉ የገዥ ፓርቲዎች መዋቅሮች የሚያቅፉት የየራሳቸውን ዘር ነው፡፡ ስብሰባ ቢጠሩና ቢቀመጡ፣ ቢወያዩ… በዘራቸው ተጠርተውና ተጠራርተው ነው፡፡ መማሪያ ክፍል ውስጥ ብቻ አይደለም፤ አንድ መኝታ ክፍል ውስጥ የተለያዩ የብሔረሰብ ልጆች ቢያድሩ፣ ይኸ ግንኙነታቸው በመካከላቸው የሚቆየው ለሊቱ እስኪነጋ ወይም ክፍለ ጊዜው እስኪያልቅ ነው፡፡ ከዚያ ሁሉም በየቀፎው ይገባል፡፡ ስለዚህም ነው አንድ ችግር በተፈጠረ ቁጥር፣ በቅጽበት ወደ ዘር ግጭት የሚለወጠው፤ ሕይወት የሚቀጠፈው፡፡
በዩኒቨርሲቲ ግቢ የተማሪዎች ሕይወት መቀጠፍ ከጀመረ ቆይቷል፡፡ 2011 ዓ.ም ከሌላው ጊዜ በዛ ብሎ መታየቱ ግልጽ ነው፡፡ በትምህርት ተቋማቱ ግቢ የሚፈስ ደም፣ አንድ ገበያ ቦታ ድንገት በተቀሰቀሰ ጠብ ከሚፈስ ደም ጋር እኩል አይደለም - ለእኔ:: ሞቱ ሞት፣ የሚጠፋው የሰው ሕይወት ሕይወት ቢሆንም፣ ይኸኛው በብዙ መንገድ የከፋ ነው:: በገበያ ላይ የተነሳው ጠብ ምክንያቱ ይታወቃል:: ገዳይም ሟችም ይታወቃሉ፡፡ በገበያ ቦታ ጠብ የገጠመው ሰው፤ ጓደኛው ወንድሙ ወይም ዘመዱ ተከትሎት ጠቡ ውስጥ ይገባ እንደሆን እንጂ ‹‹የእከሌ ዘር የሆንክ ና፤ ተከተለኝ›› ብሎ ጠብ አይጀምርም፤ አያባብስም፤ ጉዳትም አያደርስም፡፡ እሱና አጋሮቹ ብቻ እንደገቡበት ይወጡታል፡፡ ተለይተው ስለሚታወቁም በወንጀሉ ይጠየቁበታል፡፡
በዚህኛው ግን እንደዚያ አይደለም፡፡ የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በአንድ ወቅት እንደገለጡት፤ ወንጀሉን የፈፀሙት የአንድ ብሔር ሰዎች በመሆናቸው አሳልፈው መስጠት አይፈልጉም:: ወንጀለኛው ይሁነኝ ተብሎ ይደበቃል:: በአደባባይ አይታይም፡፡  የሕግ ተጠያቂ እንዳይሆን ይደረጋል:: ድርጊት ሲደጋገም ልማድ ይሆናል እንዲሉ አበው፤  የአንድን ተማሪ ግድያ ጉዳይ፣ ‹‹ምን ደረሰ?›› ብሎ ማንም ሲጠይቅ የማይታይበት ደረጃ ላይ ተደርሷል:: ወንጀልን የመከላከል፣ አድኖ ወንጀለኛን ለፍርድ የማቅረብ ኃላፊነት ያለበት የየአካባቢው ፖሊስም፤ “ውሾን ያነሳ ውሾ ይሁን” የሚል መርህ ለመከተሉ፣ ከተግባሩ በላይ ምስክር መቁጠር አያስፈልግም፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ፍትህ የሚፈልጉ፣ እንባቸው ሊታበሰላቸው የሚገባ የሟች ተማሪዎች እናትና አባቶች፣ እህትና ወንድሞች ወዘተ… አሉ፡፡ እነሱ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ በመሆናቸው፣ በዘራቸው የተነሳ በሌሉበትና ባልፈጸሙት ጥፋት እየተቀጡ ነው፡፡ ተስፋ አድርገው ልጆቻቸውን ሲጠብቁ የነበሩ ወላጆች፤ ተስፋቸው ሲረግፍ፤ “በሆነው ነገር ሁሉ እናዝናለን፤ ለቤተሰባቸው መጽናናትን እንመኛለን፡፡ ድርጊቱን አጥብቀን እናወግዛለን” ከሚል መግለጫ በላይ ምንም ነገር ሲደረግ አይታይም፡፡ የእነሱ ልጆች ሞት፤ የሞት መጨረሻ እንኳ ስለመሆኑ መተማመኛ የሚሰጥ የመንግሥት አካል ወይም ሌላ ወገን አልተገኘም፡፡
እነሆ የ2012 ዓ.ም የዩኒቨርስቲ መግቢያ ውጤት ይፋ ሆኗል፡፡ ምደባው ይቀጥላል፡፡
ከ100ሺህ በላይ አዲስ ተማሪዎች በየዩኒቨርስቲው ይመደባሉ። ነባሮችን ጨምሮ ዩኒቨርስቲዎች ከ400ሺህ በማያንሱ ተማሪዎች ይጥለቀለቃሉ:: መንግሥት አዲሶችም ሆኑ ነባር ተማሪዎች፣ እንዲሁም ወላጆቻቸው ውል እንደሚገቡ ገልጿል:: ውሉ የትምህርት ተቋሙን ንብረት ከመጠበቅ፣ ከመንከባከብ ጀምሮ ሌላውን ኃላፊነት መወጣትን እንደሚያጠቃልል ተገልጿል፡፡ መጀመር ጥሩ ነው፡፡ ይሄ ግን በዘር እያሰበ በቡድን እየተንቀሳቀሰ ያለውን ኃይል መግታት ወይም መቆጣጠር ይችላል? ስለ ተፈፃሚነቱስ ማረጋገጫው ምንድን ነው? ከሁሉም በላይ ለሰው አካልና ሕይወት ምን ያህል ዋጋ ሰጥቷል? ብሎ መጠየቅ ግድ ነው፡፡
ግንቦት 16 ቀን 2011 ዓ.ም ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተማሪ ሰዐረ አብርሃ ትግሬ በመሆኑ  ተገደለ፡፡ ሰኔ 1/2011 ዓ.ም አክሱም የኒቨርሲቲ ውስጥ ተማሪ ዮሐንስ መርሻ አማራ በመሆኑ ተገደለ፡፡ ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ትምህርት አቋርጦ ተመልሶ የገባ፤ የመንፈስ ጭንቀት ነበረበት የተባለ ተማሪ፤ ራሱን ከፎቅ ወርውሮ ሕይወቱን አጠፋ፡፡ በእኔ ሞት ማንም መጠየቅ የለበትም በሏል ቢባልም፣ ጉዳዩ የዘር አጀንዳ ተሰጥቶት፣ ሁለት ተማሪዎች በዘራቸው የተነሳ ተገደሉ፡፡
የነዚህን ቤተሰቦች ጉዳት መረዳት የሚቻለው እያንዳንዱ ሰው እራሱን በእነሱ ቦታ አስቀምጦ ነገሩን ማየት ከፈቀደ ብቻ ነው፡፡ ያን ጊዜ ችግሩ አጥንቱ ድረስ ዘልቆ ሊሰማው ይችላል፡፡
አሁንም መጭው ዓመት ሌላ ሞት የማንስማበት ዓመት እንዲሆን በጥብቅ ሊታሰብበት ይገባል እላለሁ፡፡
መርዶ በቃን!!!!      

Read 1888 times