Saturday, 24 August 2019 13:42

ጋዜጠኞች በፀረ ሽብር ሕጉ እንዳይከሰሱ ሲፒጄ ጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 ለዘገባ በፍ/ቤት ግቢ ውስጥ ሲንቀሳቀስ ታስሮ በሽብር መጠርጠሩ የተገለፀው የኢትዮጲስ ጋዜጣ አዘጋጅ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስር እንዲለቀቅ የጠየቀው ሲፒጄ፤ መንግስት ጋዜጠኞችን ሰበብ እየፈለገ በፀረ ሽብር ሕግ እየከሰሰ መሆኑ ለአገሪቱ የፕሬስ ነፃነት አደጋን የደቀነ ስጋት ነው ብሏል፡፡
አለማቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ ሲፒጄ ከትናንት በስቲያ ባወጣው ሪፖርቱ፤ በፍ/ቤት ግቢ ውስጥ ለሕግ ባለሙያው ቃለ ምልልስ ካደረገ በኋላ ለእስር የተዳረገው የኢትዮጲስ ጋዜጣ አዘጋጅ ምስጋናው ጌታቸው ከታሰረ በኋላ፣ በፀረ ሽብር ሕጉ መሠረት መጠርጠሩን ጠበቃው መግለፁን አስታውቋል፡፡
ጋዜጠኛው ሐምሌ 28 ቀን 2011 ዓ.ም በፍ/ቤት ከባለስልጣናት ግድያና መፈንቅለ መንግስት ሙከራ ጋር በተገናኘ ጉዳያቸውን እየተከታተሉ የሚገኙትን ግለሰቦች የችሎት ጉዳይ ለመከታተል በተገኘበት የተጠርጣሪዎቹን ጠበቃ ሄኖክ አክሊሉን በፍ/ቤት ግቢ ውስጥ ቃለ ምልልስ ማድረጉንና ይህን ማድረግም በሕግ ክልከል አለመሆኑን የኢትዮጲስ ጋዜጣ ባለቤት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ለሲፒጄ አስረድቷል፡፡
ቃለ ምልልሱን አድርጎ ካጠናቀቀ በኋላ ፖሊስ ጋዜጠኛውንና አብሮት የነበረውን የባልደራስ ም/ቤት አባሉን አዳም ወጂራ ማሰሩን ሲፒጄ አስታውቋል፡፡ በጉዳዩ ላይ የጠቅላይ አቅቤ ሕግ የሕዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ዝናቡ ቱኑ ለሲፒጄ መልስ መስጠታቸውን የጠቆሙ ዘገባው፤ ጋዜጠኛ ምስጋናውና አዳም በባለስልጣናቱ ግድያና መፈንቅለ መንግስት ማቀነባበሩ እጃቸው እንዳለበት ለመጠርጠር የሚያበቃ በቂ ምክንያት አለን ማለታቸውን ሲፒጄ አስታውቋል፡፡
በሌላ በኩል የፌዴራል ፖሊስ ቃል አቀባይ ጄላን አብዲ በበኩላቸው፤ ጋዜጠኛ ምስጋናው በመነጽሩ ላይ ባለ ካሜራ ሳይፈቀድለት በፍ/ቤት ግቢ ውስጥ ቀረፃ በማድረጉ ተጠርጥሮ መታሰሩን ለሲፒጄ አስረድተዋል፡፡ መንግስት ጋዜጠኛውን ለማሰር በቂ ምክንያት የለውም በአስቸኳይ ሊፈታው ይገባል ብሏል - ሲፒጄ፡፡  
ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተገናኘ ጋዜጠኛ ምስጋናውን ጨምሮ ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ፣ የአስራት ቴሌቪዥን ጋዜጠኞች በሪሁን አዳነና ጌታቸው አምባቸው ታስረው በፀረ ሽብር ሕጉ መጠርጠራቸው ለአገሪቱ የነፃ ፕሬስ ማበብና ሀሳብን በነፃነት መግለጽ መብቶች የአደጋ ምልክት ነው ብሏል - ተቋሙ፡፡
መንግስት የታሰሩ ጋዜጠኞችን ጉዳያቸውን አይቶ እንዲፈታ፣ የፀረ ሽብር ሕጉን ጋዜጠኞች ላይ መጠቀሙን እንዲያቆምና ለጋዜጠኞች ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብቶች ጉዳይ መንግስት በሪፎርሙ ውስጥ ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጥና ተገቢውን ጥበቃ እንዲያደርግላቸው ሲፒጄ ጠይቋል፡፡

Read 5653 times