Print this page
Saturday, 24 August 2019 13:40

የዎላይታ የኢኮኖሚ መዋቅር ወደ ኢንዱስትሪ እንዲለወጥ ተጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

 የዎላይታ የክልልነት ጥያቄ አፋጣኝ ሕገ መንግስታዊ ምላሽ እንዲሰጠው እንዲሁም የዎላይታ የኢኮኖሚ መዋቅር ወደ ኢንዱስትሪ የሚለወጥበት አማራጭ እንዲፈተሽ የዎላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ጠየቀ፡፡
ግንባሩ ለጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በጻፈው ባለ 4 ገጽ ደብዳቤው፤ የዎላይታ ሕዝብ በክልል የመደራጀት ጥያቄ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ አፋጣኝ ሕገ መንግስታዊ ምላሽ ያሻዋል ብሏል፡፡
ዎላይታ በክልል ደረጃ መደራጀቱ ሊያስገኛቸው የሚችላቸውን አገራዊና አካባቢያዊ ጥቅሞችንም ሰፊ ማብራሪያ አቅርቧል በደብዳቤው፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም በዎላይታ ሕዝብ መሀል ተገኝተው ችግኝ መትከላቸውና የዎላይታን ሕዝብ ጥያቄ መስማታቸው ታላቅ አክብሮት የሚሰጠው ነው ያለው ግንባሩ፤ ‹‹ቀኑም በታሪካዊ ቀንነት እየታወሰ ይኖራል›› ብሏል፡፡
በእለቱም ጠ/ሚኒስትሩ የሰጧቸው ምላሾች ለዎላይታ ሕዝብ ያላቸውን ክብር የሚያሳይና በእጅጉ ተስፋ የሚሰጡ ናቸው ያለው ግንባሩ፤ ይህ ተስፋ ሕገ መንግስታዊ በሆነ መልኩ ምላሽ አግኝቶ፣ የዎላይታ የክልልነት ጥያቄ እንዲረጋገጥ ጠ/ሚኒስትሩ እገዛ እንዲያደርጉ ተማፅኗል፡፡
በአሁኑ ወቅት የዎላይታ ሕዝብ ለግብርና የሚሆን በቂ ግብዓት የለውም፤ በፍጥነት እያደገ ለሄደው የሕዝቡ ቁጥርም የሚበቃ የእርሻ መሬት ባለመኖሩ ወጣቶች ቀያቸውን ጥለው ለመሰደድ እየተገደዱ ነው››  ብሏል ግንባሩ፡፡
በዚህም የዎላይታ ሕዝብ ኑሮ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ በመሆኑ አስቸኳይ አማራጭ መፍትሄ ሊፈለግለት እንደሚገባም ግንባሩ በጻፈው ደብዳቤሰ ጠይቋል፡፡
‹‹የዎላይታ የኢኮኖሚ መዋቅር በአስቸኳይ ወደ ኢንዱስትሪ መቀየርም የቅንጦት ሳይሆን የነፍስ አድን ጥያቄ ሆኖ ተገኝቷል ያለው ግንባሩ፤ ለዚህ ሀሳብ ተግባራዊነት የሚያበቁ ምቹ ሁኔታዎች አሉ›› ሲል በደብዳቤው በዝርዝር አመልክቷል፡፡
ይህን ተግባራዊ ለማድረግና ሕዝቡን ከከፋ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉስቁልና ለማላቀቅ የዎላይታ ክልል ሆኖ መደራጀቱ አስፈላጊ ነው ያለው ግንባሩ፤ ለዚህ አፋጣኝ ሕገ መንግስታዊ ምላሽ እንዲሰጥ ጠይቋል - የራሱን የእድገት እቅድ አውጥቶ፣ በጀት መድቦና ስትራቴጂ ነድፎ የዎላይታን ሕዝብ ማልማት እንደሚፈልግ በመግለጽ፡፡

Read 6100 times