Saturday, 24 August 2019 13:35

‹‹የእነ አቶ ልደቱን እንቅስቃሴ በሕግ እናስቆማለን›› - ዶ/ር ጫኔ ከበደ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

‹‹ኢዜማን ከሰን ንብረታችንን እናስመልሳለን››- እነ አቶ ልደቱ አያሌው


              ኢዴፓ ይገባናል የሚለው የእነ አቶ ልደቱ አያሌው የአመራር ቡድኑ፤ በቀጣይ የፓርቲውን ንብረቶች ለማስመለስ ኢዜማን በሕግ እንደሚከስ ያስታወቀ ሲሆን የቀድሞ አመራሮች በበኩላቸው፤ ‹‹የግለሰቦቹን›› እንቅስቃሴ በሕግ እናስቆማለን ብለዋል፡፡
በኢዴፓ ብሄራዊ ም/ቤት ላይ የተጣለው እገዳ በምርጫ ቦርድ ተነስቶልናል ያለው የአቶ ልደቱ አያሌው ቡድን፣ የእገዳውን መነሳት ተከትሎ፣ አስቸኳይ ስብሰባ አድርጎ ውሳኔ ማሳለፉን አስታውቋል፡፡
በቀድሞ የፓርቲው አመራሮች (ማለትም ኢዜማን በተቀላቀሉት) ዶ/ር ጫኔና ሌሎች አመራሮች ምትክ አቶ አዳነ ታደሰን ፕሬዚዳንት፣ ወ/ት ጽጌ ጥበቡን ምክትል ፕሬዚዳንት አድርጎ ብሄራዊ ም/ቤቱ መርጧል ያለው የእነ አቶ ልደቱ ቡድን፣ በጥቂት ወራት ውስጥም የፓርቲውን ጠቅላላ ጉባኤ ለመጥራት መወሰናቸውን አስታውቀዋል፡፡
በዚህ ጉባኤ አዘጋጅነትም አቶ ልደቱ አያሌው፣ አቶ ሄኖክ ሄደቶ፣ አቶ ተስፋዬ መንበሩ፣ አቶ ግዛቸው አንማውና፣ አቶ አንድአርጋቸው አንዷለም መመረጣቸውን አመራሮቹ በጋዜጣዊ መግለጫቸው ጠቁመዋል፡፡
‹‹በምርጫ ቦርድ ተጥሎብን የነበረው እገዳ ተነስቶልናል›› ያሉት እነ አቶ ልደቱ፤ ከኢዴፓ አፈንግጠው የወጡ አራት ግለሰቦች የፓርቲውን ጽ/ቤቶች በባንክ የተቀመጠ ገንዘብ (416 ሺህ ብር) እንዲሁም መዛግብትና ማህተም ያለአግባብ ኢዜማ እንዲጠቀምባቸው አድርገዋል ብለዋል፡፡
ኢዜማ እነዚህን ንብረቶች ያለምንም ሕጋዊ መሰረት እየተጠቀመ ይገኛል ያሉት እነ አቶ ልደቱ፤ ኢዜማ አራቱ ግለሰቦች የማጭበርበር ድርጊት መፈጸማቸውን ተገንዝቦ፣ ንብረቶቹን እንዲመልስ እንጠይቃለን፤ የማያስረክበን ከሆነም በኢዜማ ላይ ክስ መስርተን፣ በሕግ ንብረታችንን ለማስመለስ እንገደዳለን ብለዋል፡፡
የእነ አቶ ልደቱ አካሄድ ፍጹም ሕገወጥ የግለሰቦች ሁከት መሆኑን የሚገልፁት የኢዴፓ የቀድሞ ሊቀመንበር ዶ/ር ጫኔ ከበደ በበኩላቸው፤ የኢዴፓ ሕጋዊ አመራሮች የነበርነው እኛ ነን፤ ይህም በምርጫ ቦርድና በፍ/ቤት የተረጋገጠ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
በፓርቲው ይገባናል የፍ/ቤት ክርክር እነ አቶ ልደቱ ተ    ሸንፈው ጽ/ቤት፣ ማህተምና የፓርቲውን ንብረቶች ለኛ እንዲያስረክቡ ተደርገዋል ያሉት ዶ/ር ጫኔ፤ በዚህ ውሳኔ መሰረት እነ አቶ ልደቱ ሕጋዊ ያልሆኑ አካላት ናቸው፤ የሚረከቡንም ሆነ በክስ የሚያስመልሱት ንብረት የለም ብለዋል፡፡
“የኢዴፓ የመጨረሻው ወሳኝ ጠቅላላ ጉባኤ ነው” ያሉት ዶ/ር ጫኔ፤ ይህ የጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ በግለሰቦች ሊሻር አይችልም ብለዋል፡፡
ግለሰቦቹ ያለአግባብ ኢዴፓንና ስሙን እየተጠቀሙበት በመሆኑም እያንዳንዳቸውን በግለሰብ ደረጃ በፍ/ቤት ለመክሰስ እየተዘጋጁ መሆኑን ዶ/ር ጫኔ ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል:: “የግለሰቦቹን እንቅስቃሴ በሕግ እናስቆማለን፤  ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ለእነ አቶ ልደቱ በሰጠው ምላሽ ከዚህ በፊት የተጣለ እገዳም ሆነ የሚነሳ እገዳ የለም ማለቱ ትክክል ነው” ብለዋል - ዶ/ር ጫኔ፡፡
እነ አቶ ልደቱ ምርጫ ቦርድ እገዳውን አንስቶልናል ማለታቸውም ማደናገሪያ ነው፤ ኢዴፓ እንደ ፓርቲ አልታገደም ነበር ብለዋል፡፡
ኢዴፓ ከሌሎች ጋር ተዋህዶ ኢዜማን የመሰረተበትን ሂደት የሚያስረዱ ሰነዶች ለምርጫ ቦርድ አቅርበንለታል፤ ምላሹንም እየጠበቅን ነው ብለዋል ዶ/ር ጫኔ፡፡
እነ አቶ ልደቱ በበኩላቸው፤ “ኢዴፓ ተመልሶልናል በቀጣይ ንብረታችንን እናስመልሳለን፣ ጠቅላላ ጉባኤም እናደርጋለን፣ ቀጣዩ ምርጫ መራዘም አለበት የሚል አቋም ቢኖረንም፣ የግድ ምርጫው የሚካሄድ ከሆነ በአዲስ አበባ ብቻ ተወዳድረን ለማሸነፍ እንሰራለን” ሲሉ በመግለጫቸው አመልክተዋል፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፤ ወትሮም ቢሆን የተጣለ እገዳ ስለሌለ የሚነሳ እገዳ የለም” የሚል ምላሽ ሰጥቷል፡፡

Read 1854 times