Saturday, 24 August 2019 13:36

አዲሱ የትምህርት ፖሊሲ ከ2013 ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(24 votes)

  በአጠቃላይ በአገሪቱ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ጥናት መሰረት የተዘጋጀው አዲስ የትምህርት ፖሊሲ በ2013 ዓ.ም ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል፡፡ የአገሪቱን የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ለማዘጋጀት በተደረገው ጥናት፣ ከተለያዩ ምሁራንና ሀሳብ አመንጪዎች በአጠቃላይ 357 ያህል ምክረ ሀሳቦች ቀርበው እንደነበር የገለፀው የትምህርት ሚኒስቴር፤ ከእነዚህ መካከል ሶስቱ አዋጆችንና ሕገ መንግስትን የሚቃረኑ በመሆናቸው ተቀባይነት አላገኙም ተብሏል፡፡
ተቀባይነት ያላገኙት ምክረ ሀሳቦችም ጥራት ያላቸው የግል ትምህርት ቤቶችን ለማስፋፋት ለባለሀብቶች መሬት በነፃ መስጠት፣ መምህራን ጡረታ ከወጡ በኋላ ሙሉ ደመወዛቸው እንዲከፈላቸው የሚሉት ውድቅ ከተደረጉ ምክረ ሀሳቦች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በአዲሱ የትምህርት ፖሊሲ መሰረት፤ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት እስከ 6ኛ ክፍል ይሰጣል፣ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ደግሞ ከ7-8ኛ ያለው ይሆናል፡፡ 6ኛ እና 8ኛ ክፍል ደግሞ ክልላዊና አገር አቀፍ የተማሪዎች ብቃት መመዘኛ ብሄራዊ ፈተና ይሰጣል ተብሏል፡፡ በአዲሱ የትምህርት ፖሊሲ መሰረት፤ ከ1993 ዓ.ም ጀምሮ ሲሰጥ የነበረው የ10ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና፣ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ይቀራል፡፡  
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል የሚሰጥ ሲሆን 12ኛ ክፍል ላይ ብሄራዊ ፈተና የሚሰጥ ይሆናል፡፡ 12ኛ ክፍል የሚሰጠው ብሄራዊ ፈተና ወደ ዩኒቨርሲቲና ወደ ቴክኒክና ሙያ የሚገቡ ተማሪዎችን መለያ ይሆናል ተብሏል፡፡ የዩኒቨርሲቲ ትምህርትም ዝቅተኛው 3 አመት መሆኑ ቀርቶ 4 ሆኗል፡፡
የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ደግሞ ከደረጃ 1 እስከ ደረጃ 8 ወይም ሶስተኛ ዲግሪ ደረጃ ድረስ እንዲሰጥ ተወስኗል - በአዲሱ የትምህርት ስርዓት መሰረት አዲስ የመምህራን ድልድልም መዘጋጀቱን የትምህርት ሚኒስቴር ያስታወቀ ሲሆን በዚህም ለ1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው፣ ሁለተኛ ደረጃ ሁለተኛ ዲግሪ ያላቸው እንዲሁም ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሁለተኛ ዲግሪና ከዚያ በላይ ያላቸው መምህራን ይመደባሉ ተብሏል፡፡
የትምህርት ፖሊሲው በዋናነት በስነ ምግባር፣ በመልካም እሴትና በብቃት የታነጸ ዜጋን ለማፍራት የሚያስችል ነው የተባለ ሲሆን የትምህርት ሥርዓቱ የአገሪቱን አንድነት የሚያስቀጥልና አገር በቀል እውቀቶችን መሰረት ባደረገ መልኩ የተዘጋጀ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

Read 17019 times