Saturday, 24 August 2019 13:32

ከ50-300 ሚ. ብር እዳ በተጠየቁ ቻይናውያን ጉዳይ ጠ/ሚሩ ጣልቃ እንዲገቡ ተጠየቀ

Written by  ሰላም ገረመው
Rate this item
(1 Vote)

 በኢትዮጵያ በተለያዩ ኢንቨስትመንቶች የተሠማሩ ቻይናዊያን ግብር ባለመክፈልና ሀሰተኛ ደረሰኝ ከመጠቀም ጋር በተገናኘ የገቢዎች ሚኒስቴር እንዲከፍሉ የወሰነባቸውን ከፍተኛ ዕዳ በተመለከተ ጠ/ሚኒስትሩ አጣርተው መፍትሔ እንዲያበጁ የቻይና መንግስት በደብዳቤ ጠየቀ፡፡ በኮንስትራክሽን፣ በኤሌክትሮኒክስ ምርትና በተለያዩ ኢንቨስትመንቶች ተሠማርተው የሚገኙት ቻይናውያን በተለያዩ ጊዜያት ለገቢዎች መክፈል ያለባቸውን ግብር ባለመክፈልና ሃሰተኛ ደረሰኝ በመጠቀም በሚል ከ50 ሚሊዮን እስከ 300 ሚሊዮን ብር ወለድና መቀጮን ጨምሮ እንዲከፍሉ መጠየቃቸውን ምንጮች ገልፀዋል:: ከገንዘብ ክፍያውም በተጨማሪ ጉዳዩ በወንጀል የሚያስቀጣ ነው ተብሏል፡፡
ቻይናውያኑ የሚያንቀሳቅሷቸው ድርጅቶች እንዲከፍሉ የተጠየቁት ገንዘብ ከፍተኛ መሆኑን የጠቀሱት ምንጮቻችን፤ አብዛኛዎቹ የሀሰተኛ ደረሰኝ የተባሉት ሕጋዊ ንግድ ፍቃድ አውጥተው ከሚሰሩ ተቋማት ግብይት የተፈፀመባቸው መሆኑን ገልጸው፤ “እንዴት ሀሰተኛ ደረሰኝ ሊሰጡን ይችላሉ ብለን እንጠረጥራለን” በማለት ቻይናውያኑ በደብዳቤ ለገቢዎች ቅሬታ ማቅረባቸውን ይናገራሉ፡፡
ቻይናውያኑ ጉዳያቸው በድጋሚ እንዲታይላቸው በተደጋጋሚ ለገቢዎች ሚኒስቴር በደብዳቤ ቢጠይቁም ምላሽ እንዳልተሰጣቸው በመግለጽ፤ የሀገራቸው መንግስት በጉዳያቸው ጣልቃ እንዲገባ በመጠየቃቸው የቻይና መንግስት ለጠ/ሚኒስትሩ ደብዳቤ መፃፉን ምንጮች ለአዲስ አድማስ ጠቁመዋል፡፡
የቻይና መንግስት ዜጐቹ በተሠማሩበት የኢንቨስትመንት ስራ ምክንያት ያለ አግባብ የተደረገባቸው ጫና ካለ ጠ/ሚኒስትሩ ጉዳዩን እንዲመረምሩትና ትብብር እንዲደረግላቸው በደብዳቤ መጠየቁን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
የገቢዎች ሚኒስቴር አደረኩት ባለው ማጣራት፣ በሀሰተኛ ደረሰኝ መገልገልና ግብርን ለመንግስት ባለመክፈል እንዲሁም ጉቦ መስጠት በሚል በጠረጠራቸው 17 ቻይናውያን ላይ ክስ መመስረቱ ተገልጿል፡፡ የገቢዎች ሚኒስትር ወ/ሮ አዳነች አበቤ፤ በግብር አለመክፈልና በሀሰተኛ ደረሰኝ መገልገል የተጠረጠሩ ባለሀብቶች፣ የተጠየቁትን ገንዘብ ከከፈሉ የወንጀል ክሱ እንደሚቀር መግለፃቸው ይታወሳል፡፡

Read 1340 times