Saturday, 09 June 2012 11:24

የክሊፕ ደረጃን በእጥፍ ያሳደገ “ጥቁር ሰው”

Written by  ሰላም ገረመው
Rate this item
(0 votes)

400 ተዋንያን የተሳተፉበት ክሊፕ 480ሺ ብር ፈጅቷል

“ይድረስ ለወዳጄ፡- እንደምን ሰንብተሃል እኛ ባለንበት በእግዚአብሄር ቸርነት ደህና ነን፤ መቼም ወቅት ፈቅዶ ለብዙ ትውልዶች ያህል ተራርቀን ብንኖርም ያገሬ ታሪክ የጀግኖች ታሪክ መቼም አይዘነጋም ብዬም አልነበር… እናም ይሄውልህ በእናንተው ዘመን ደግሞ ብላቴናው ቴዎድሮስ ካሳሁን “ጥቁር ሰው” ብሎ ታሪካችንን ብድግ አደረገዋ!

እንግዲህ ምን ትላለህ? ከሆነልህማ የፊታችን ማክሰኞ ከአመሻሹ 12 ሰዓት ላይ ከቤተመንግሥታችን ዝቅ ብሎ ከሚገኘው ሂልተን ውቴል ቤት ብቅ በልና ጠበል ፀዲቅ ቅመስ፤ ስናወጋ እናመሻለን

አደራ እንዳትቀር

ያልመጣህ እንደሆነ ግን ማርያምን እቀየምሃለሁ፡፡

ዳግማዊ አጤ ምኒልክ ግንቦት 28/2004 ዓ.ም”

ከላይ የቀረበው ፅሁፍ የቴዲ አፍሮን “ጥቁር ሰው” የቪዲዮ ክሊፕ ለመመረቅ የተጠራው እንግዳ ሁሉ የያዘው የመግቢያ ካርድ ላይ የሰፈረ መልዕክት ሲሆን ካርዱ በብራና መልክ የተዘጋጀ ነው፡፡ ጥሪ የደረሳቸው ከ800 የማያንሱ ታዳሚዎች ባለፈው ማክሰኞ ከምሽቱ 12 ሰዓት ግድም ላይ ሂልተን ሆቴል መግቢያ ላይ የተኮለኮሉት እቺን ያማረች ካርድ በእጃቸው ይዘው ነበር፡፡

የፍተሻው ቦታ ላይ “ኢታ ፖል ሴኩሪቲ” የሚል ልብስ የለበሱና ባጅ ያንጠለጠሉ ጋርዶች ቆመው ሲያስተናግዱ የነበረ ቢሆንም የፍተሻዋ ማለፊያ አንዲት በመሆኗ ግርግር መፈጠሩ አልቀረም፡፡ እገባለሁ አትገባም የሚለው ውዝግብም ታዳሚውን አስከፍቷል፡፡ ብዙዎችን ያስገረመው በአልበሙ ምርቃት ላይ የሚጠበቀውን ያህል አርቲስቶችና ድምፃውያን አለመገኘታቸው ነበር፡፡ ምን ተፈጠረ ያሰኛል፡፡ የእለቱን ፕሮግራም መጀመር ያበሰሩት ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሠሠ ሲሆኑ ምሽቱን በሙሉ በሳቅ እያዋዙ በመድረክ መሪነት ዘልቀዋል፡፡ እሳቸው በመድረክ መሪነት የዘለቁትን ያህል የቴዲ አልበም ስፖንሰር ሜታ አቦ ቢራ የምሽቱ ስፖንሰር ሆኖ ነበር ያመሰው - ሜታ ቢራ ለታዳሚው በማስተናገድ፡፡2 ሰዓት ላይ ታዳሚው እራት እንዲበላ ተጋበዘ (በጥሪው ካርድ ላይ ዳግማዊ ምኒሊክ ጠበል ፃዲቅ ያሉት ማለት ነው) አርቲስት ስለሺ ደምሴ (ጋሽ አበራ ሞላ) ሁለት አጃቢዎቹን አስከትሎ ክራሩን ይዞ መድረክ ላይ የወጣው 2፡25 ላይ ነበር፡፡

አርቲስቱ የዛሬ ሃያ አመት በአውሮፕላን  ወደ ካይሮ ሲያቀና በ27 ሺህ ከፍታ ጫማ ላይ ሆኖ ያየውን አባይን “አባቱ ደጀን እናቱ ጣና የኢትዮጵያ ልጆች መጡ እንደገና፤ የአፍሪካ ልጆች መጡ እንደገና” የሚል ግጥምና ዜማ ደርሶለት፣ በክራር አጅቦ ታዳሚውን አዝናንቷል፡፡ የሚኒሊክን የአድዋ ጦርነት አዋጅ ያነበበው አርቲስት ተፈሪ አለሙ፤ በባህላዊ አለባበስ ሚኒሊክን መስሎ ነበር ብቅ ያለው፡፡ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን በ1964 ዓ.ም ”ዋ አድዋ” በሚል ርእስ የፃፈውን ግጥም፤ አርቲስት አበበ ባልቻ ለታዳሚው አቅርቦታል - በመነባንብ፡፡

ከ30 ደቂቃ ዝምታ በኋላ የለጠቀው ፕሮግራም ቴዲ አፍሮ እስካሁን ስለ ሰራቸው ስራዎች በቪዲዮ የተቀረፀ የራሱ አስተያየት ነበር፡፡

“የሙዚቃ ፍላጐቴ ከቤተሰቦቼ የወረስኩት ሲሆን በልጅነቴ ህብረትርኢት ላይ እነ ጥላሁን ሲዘፍኑ ተመስጬ ነበር የማየው፡፡

አቦጊዳ የመጀመሪያ ካሴቴ በመሆኑና ልጅነቴን የሚያስታውሰኝ በመሆኑ በጣም እወደዋለሁ፡፡ ለኦሎምፒክ የዘፈንኩት ትልቅ ትውስታ አለኝ፡፡ ድል የተገኘበትና ከስሜት የተሠራ ስራ በመሆኑ ነው፤ “ቦብማርሌ” የሚለውን ሙዚቃ የሰራሁት ቦብ ኢትዮጵያን ሲያስተዋውቅ ከማንም በላይ በመሆኑ ነው፤ የተቀደሰች እና በሃይማኖት መቻቻል የበዛባት እንደሆነች በመግለጽ ከነ ሀይሌና አበበ ቢቂላ ባልተናነሰ ባንዲራዋን ለአለም ያስተዋወቀ ነው፡፡

“ጃ ያስተሠርያል” ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ካለፈው የተሻለ ነገር ተምረን በፍቅር ሁሉን ትተን ማስተማርና መቻቻል እንዳለብን ለማሳየት ያቀነቀንኩት ነው፤ አዲስ አመትን በተመለከተ እያንዳንዱ የራሱ የሆነ የዘመን ቀመር አለው፡፡ … ሁሉም አመት የራሱ የሆነ ተስፋ ይዞ የሚጓዝ ነው፤ ከዛ ስሜት ተነስቼ የሠራሁት ነው፡፡

“እስር ቤት ሁሉንም ነገር አስተምሮኛል፤ በህይወት የማሳልፈው ለማስተማርና ለጥሩ ነገር በመሆኑ ይዞ ሊመጣ የሚችለውን ነገር በፀጋ መቀበል ነው፡፡ ስለዚህ በቆየሁባቸው ጊዜያት ጥሩ ጊዜ አሳልፌያለሁ” በማለት የወህኒ ቤት ቆይታውን ሳይቀር የገለፀው ቴዲ አፍሮ፤ በመጨረሻ ስለመጨረሻው አልበሙ ተናግሯል - “ጥቁር ሰው የተሰኘው አልበም ደግሞ ዳግማዊ ምኒሊክ ከጣሊያን ጋር ተዋግተው ያሳዩትን ጀግንነት የሚያንፀባርቅ ነው፡፡ ለሚቀጥለው ትውልድ ትልቅ ቁምነገር ነው፡፡ ትልቅ ድል ከመሆኑ ባሻገር ለሌሎች አፍሪካ አገሮች ነፃ መውጣት አስተዋጽኦ አለው” በማለት፡፡

3፡10 ላይ ሁሉም በጉጉት ሲጠብቀው የቆየው “ጥቁር ሰው” ክሊፕ ተከፈተ፡፡

በሳቢሳ ፊልም ፕሮዳክሽን የተሠራው “ጥቁር ሰው” የዘፈን ክሊፕ የሚጀምረው አርቲስቱ ከመሬት የዘገነውን አፈር ሲበትን በማሳየት ነው፡፡ አርቲስት ሳሙኤል ተስፋዬ፤ አፄ ምኒሊክን ሆኖ ሲሠራ መነን ሙላቱ ደግሞ እቴጌ ጣይቱን በመወከል ተጫውታለች፡፡ የተዋንያኖቹን የሜካፕ ስራ ለመስራት 43ሺ ብር እንደፈጀ ተገልጿል፡፡ የሜካፕ ባለሙያው ተስፋዬ፤ የቴዲ አፍሮን ልብስ ዲዛይን ያደረገ ሲሆን ልብሱ የኢትዮጵያን ጐፈር ለባሾችና የግብፅ ፈርኦን  ለባሾችን በማጣመር ዲዛይን መደረጉን እና በልብስ ሰፊ አብርሃም ታከለ መሠፋቱን ገልፆ፤  የልብሱ ስምም ቴዲ አፍሮ መባሉን ተናግሯል፡፡   አብዛኞቹ ታዳሚዎች የተደመሙበት ይሄ ባለ ጥቁርና ነጭ ቀለም ክሊፕ፤ በፊልም እንጂ በዘፈን ክሊፕ በዚህ ደረጃ ተሠርቶ እንደማያውቅ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ለዚህም ይመስላል ለ6 ደቂቃ የታየው ክሊፕ ሲጠናቀቅ ታዳሚዎች አድናቆታቸውን በፉጨትና በጭብጨባ የገለፁት፡፡ ሁለት ወር የፈጀው ክሊፑ፤ 400 ተዋንያንን ያሳተፈ ሲሆን 480 ሺህ ብር እንደወጣበት ተነግሯል፡፡ በሲኤምሲ አካባቢ ከሚገኝ ኮረብታማ ቦታ ላይ የተቀረፀውን ክሊፕ ሙሉ ወጪ የሸፈነው አዲካ መሆኑን አቶ አሸናፊ ዘለቀ የአዲካ ኮሙኒኬሽን ኤቨንት ማኔጅንግ ዳይሬክተር ገልፀዋል፡፡ በስራው ሂደት የክሊፑ ወጪ በየጊዜው እየበዛ እንደሄደ የጠቆሙት አቶ አሸናፊ፤ ወጪውን የተቀበሉት ስራው አጥጋቢና ማራኪ እየሆነ በመምጣቱ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ቴዲ አፍሮም ለታዳሚው ባደረገው ንግግር ላይ ይሄንኑ ሃሳብ አንፀባርቆአል፡፡ በመጨረሻም በጣልያንና በኢትዮጵያ መካከል የተደረገውን ጦርነት የሚያስታውስ ሽለላና ፉከራ የቀረበ ሲሆን፤ ምኒሊክና እቴጌ ጣይቱን ሆነው የተወኑት እንዲሁም አጃቢዎቻቸው የድል ብስራት እያሰሙ በመግባት ትርኢቱ ተጠናቋል፡፡ በእንግድነት የተጋበዙት የባልቻ አባ ነፍሶና የፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ቤተሰቦች ቴዲ አፍሮን “የታሪክ ሊቅ” እና “ጀግና ብላቴና” በማለት ያደነቁት ሲሆን የራስ ተፈሪ ሀ/ስላሴ አራተኛ የልጅ ልጅ እንደሆነ የተናገሩት ግለሰብ፤ ለአርቲስቱ ያላቸውን አድናቆት ገልፀውታል፡፡

ቴዲ አፍሮ በምሽቱ ፕሮግራም “አመለ ሰናይ” እና “ሳሳሁልሽ” የሚሉ ዘፈኖቹን በመድረክ ላይ እንደሚጫወት በሚዲያ እንደተነገረ ቢታወቅም፤ “ዳግማዊ ምኒሊክ” የሚለውን ዜማ ከታዳሚው ጋር ከማዜም በቀር አንድም ዘፈን ሳይዘፍን ቀርቷል፡፡ የቴዲ ማናጀር ዘካሪያስ ምክንያቱን ሲያስረዳ፤ ድልና ጀግንነት የተበሰረበት ምሽት በመሆኑ ሌሎች ዘፈኖች መዝፈኑ ድብልቅልቅ ያለ ስሜት እንዳይፈጥር በሚል ነው ብሏል፡፡  የምሽቱ የክሊፕ ምርቃት ፕሮግራም የተቋጨው ለቴዲ አፍሮ በተበረከቱ ስጦታዎችና ሽልማቶች ነበር፡፡ አርቲስቱ ከጀግኖች ቤተሰብና ከእናቱ ስጦታዎች ሲበረከትለት፤ አጭር የአበሻ ቀሚስ የለበሰችው እጮኛው አምለሰትም ለመጀመሪያ ጊዜ በመድረኩ ላይ ታይታለች፡፡

======================

ስለ ፕሮግራሙ ማን ምን አለ?

“እኔ ካሴቱ ገና ከመውጣቱ በፊትም ሰምቼዋለሁ፡ አልበሙ ምንም የሚወጣለት አይደለም፡፡ ጥበብ ማለት መጀመሪያ ሰው የተደሰተበት ሳይሆን የሰራው ሰውዬ የተደሰተበት ማለት ነው፤ ባይደሰትበት ባይገባው አይሠራውም ነበር፡፡ ስለዚህ ካሴት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ አስቴር አወቀ ሃያ አልበም ቢኖራት አንድ ወይም አምስት ዘፈን ሊወደድ ይችላል፡፡ ቴዲ ያላመነበትን አልበም ትቶ ያመነበትን የሰራበትን ጊዜ እናስታውሳለን፡፡ በ1993 ዓ.ም “ጉድ ሠራሽኝ” የሚለው ዘፈን ላይ አወያይም እኔ ነበርኩ፡፡ ለዳዊት መለሰ ነበር የተሠጠው፤ ያንን አልበም አልቀበልም ብሎ ነበር፡፡ አሁን ይሄንን ተቀብያለሁ ብሎ ነው የሠራው፡ ብዙ ከበሰለ በኋላ የፃፋቸውን ነገሮች ስንሰማ የበሰሉ ናቸው፡፡ ብዙ ነገር መፍጠር የሚፈልግ ጐበዝ ዘፋኝ ነው፡፡

የዲቪዲው ምርቃት ላይ ሙሉ በሙሉ አዲስ ነገር ነው የታየው፤ ማንም ያላደረገው ነው፡፡ ሰው መዝፈኑን ነው የሚፈልገው፤ እኛ ደግሞ ቁምነገር ፈልገን ነው የመጣነው፡ የታዳሚው ብዛት ለእኔ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ሆኖም መግቢያው አካባቢ ትንሽ ችግር ስለነበር እኔም በጓሮ በር ነው የገባሁት፡፡ ሰዎች ትኬት ይዘው የመከልከል ሁኔታ ነበር፤ ሆኖም ክሊፑን ሳይ አርበኛው አባቴ ነው ትዝ ያለኝ፡ ያልተሄደበት አካሄድ ነበር፡፡ እንደ ሌላው ተመልካች መዝፈኑን እጠብቅ ነበር፡፡ ሆኖም በሙያው ውስጥ ስላለሁ ለእኔ ችግር የለውም፡፡ ብዙ ሰዎች ግን ቅር መሰኘታቸውን አይቻለሁ፡፡”

 

====================

“ስለ ካሴቱና ስለ ፕሮግራሙ የምሰጠው አስተያየት ባይኖረኝም ክሊፑ በጣም አሪፍ ነው፤ የሠሩት ልጆች መመስገን አለባቸው፡፡”

“አልበሙ በጣም ደስ ይላል፡፡ ቅርበቴ ከስነ ጽሑፉ ጋር ስለሆነ ደስ የሚሉ ገለፃዎች አይቼበታለሁ፡፡ አንዳንድ የቃላት አገባቦች ላይ ጥያቄ ያላቸው አሉ፤ ግን ጥሩው ነገር ይበዛል፡፡ ብዙ ጊዜ ቢባልም እኔም ያነሳሁት ሃሳብ ነበር፡፡ “ጥቁር ሰው” የሚለው ዘፈን ላይ “ባልቻ አባቱ ነፍሶ” የሚለው ትክክለኛ አገላለጽ አይደለም፤ “ነፍሶ” የባልቻ አባት ሳይሆን የባልቻ ፈረስ ነው፡፡ ሌላው የፀጋዬ ገ/መድህን ግጥም የገባበት ቦታ ትክክለኛ ነው ብዬ አላስብም፡፡ ቴዲ የዘፈነው “ሁሉም ቀላል ነው፤ ሁሉም ይለወጣል” እያለ ሲሆን የፀጋዬ ደግሞ (ፊውቸሪንጉ) “ፈራን ሁሉንም ፈራን” የሚል በመሆኑ ሁለቱ ተቃራኒ ነገሮች ናቸው፡፡ ከዛ በስተቀር ግን “ከምችለው በላይ” የሚለው አይነት አገላለፅ ያለበት ደስ የሚሉ ዘፈኖች አሉት፡፡ ስለ ክሊፑ ምርቃት በሁለት ጐኑ እናየዋለን፡፡ ፕሮግራሙን ያዘጋጁት ሠዎች ሠውን እንዴት አስገቡ፤ ፕሮግራም ያለ ሠአት መጀመር የተለመደ ቢሆንም የሔድንበት አላማ “ጥቁር ሠው” የሚለውን ክሊፕ ለመመረቅ ነው፡፡ ክሊፑ በጣም የሚገርም ነው፤ የገመትኩትም ነበር፡፡ አድቬንቸር ፊልም ለመስራት ገንዘብ ካልገደበን በስተቀር እንደሚቻል ያሳየና ከፍተኛ ድካም እንደተደከመበት ማንም አይቶ የሚፈርደው ነገር ነው፡፡ በጣም ነው የተደሠትኩት፤ ክሊፕ ብቻ ሳይሆን ፊልም ነው፡፡ ሆኖም ይህንን የመሠለ ስራ ተሠርቶ ባለሙያዎቹ መመስገን ነበረባቸው፤ ቴዲ ራሱ እርስ በርስ ባንሠራው ይሔንን የመሠለ ስራ ለመስራት አንችልም ነበር የሚል ሀሳብ አንስቶ ነበር፡፡ ሌላው መግቢያው አካባቢ የነበረው ግርግር ይከብዳል፡፡ ህዝቡ የሚጠብቀው የነበረውን ዘፈን አለመዝፈኑ ብዙዎችን አሳዝኗል፤ ግን ቴዲን በሌላ ኮንሠርት ሊያገኙት ይችላሉ፤ ሆኖም የሠሩት ሠዎች መመስገንና መሸለም ነበረባቸው፡፡ አበባም ቢሆን ሊሸለሙ ይገባ ነበር፡፡” አርቲስት ደረጄ ፍቅሬ፤ የ“ስርየት” ፊልም ደራሲ

 

=======================

አርቲስት ታምሩ ብርሃኔ

“አዲሱን ከቴዲ የቀድሞ ካሴቶች ጋር አነፃፅሬው አላውቅም፤ ከጥንካሬው ጋር እንጂ፡፡ ማንኛውም ሠው እስር ቤትን የሚያህል ትልቅ ማህበራዊ ችግር ደርሶበት ተመልሶ ወደ ፈጠራ ሲገባ ትንሽ አስቸጋሪ ነገሮች ይገጥሙታል፡፡ ቴዲ ግን እንደገና ይሔንን መስራቱ በራሱ ትልቅ ነው፡፡ ነጮቹ ቢሆኑ ይሔኔ ስንት ሳይካትሪስት ይዘው ነው፡፡ ስለካሴቱ ለማውራት ሠፊ ጊዜ ያስፈልጋል፡፡ የምመኘውና እዚህ ካሴት ላይ ጠብቄ ያጣሁት ነገር ቢኖር እነ ቴዎድሮስ ታደሠ እንደዘፈኑት አይነት “እምዬ ኢትዮጵያ” አይነት  ዜማ ነው፡፡ ባለፈው ስለ አፄ ሀ/ስላሴ ዘፍኗል፡፡ አሁን ስለ አፄ ሚኒሊክ ዘፈነ፡፡ በሚቀጥለው ስለ አፄ ቴድሮስ እንደሚዘፍን እጠብቃለሁ፡፡ ሌላው ባለፈው “ገና እወድሻለሁ” ብሏል፤ አሁን ደግሞ “ብወድሽ ብወድሽ አትሠለችኝም” የሚል ነገር አለ፡፡ ስለዚህ ተያያዥነት አለው፡፡ የራሱ የፈጠራ ስራ ነው፡፡ አንድ አልበም መቶ ሀምሳ ሺህ ብር በሚሸጥበት ዘመን ቴዲ ለ6 ደቂቃ ክሊፕ 480ሺህ ብር ማውጣቱ ሠውን ማክበሩ ነው፤ ለየት ያለ ነገር ማስቀመጥ ነው፤ ደረጃውን የጠበቀ ሥራም ነው፤ የትኛውም አለም አቀፍ ሚዲያ ላይ ቢተላለፍ ያኮራል፤ ለአንድ ዘፈን ነበር ያመሸነው፤ እንዲህ የሚነቀንቁ ታሪካዊ ክሊፖች ሲሠሩ ደስ ይላል፡፡”

 

 

Read 4036 times Last modified on Saturday, 09 June 2012 11:34