Saturday, 17 August 2019 14:16

ወንድም ዤሮ

Written by  በሊና ጎበና ስሜ linagobena@gmail.com
Rate this item
(2 votes)

                          (እንክርዳድ ወ ስንዴ )
                
            ‹‹በህይወት ኖሬ ይህን የጥበብ ነጻነት ዘመን በማየቴ ዕድለኛ ነኝ!››
- ተ/ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሠሠ
አልፎ አልፎ ጥምን የሚያረካ የጥበብ ውጤት ያጋጥማል፡፡ ውስጥን ለሚጎተጉት ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ፡፡ ጥያቄው የሁላችንም መሆን ሲጀምር ችላ ብለነው ስር እየሰደደ ቆይቶ ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ መግለጫ በወጣበት ጊዜ ነበር በውጪ ሀገር የምንኖር አማኞች ተሰባስበን በይፋ የተነጋገርንበት፡፡ከዚያ በፊት (ሆነም በኋላ) እያንዳንዱን ጋጠ ወጥ የነቢይ ተብዬዎች ተግባር ከማጣጣል ያለፈ ያደረግነው የለም፡፡አሁንም ድረስ:: ይህንኑ የቤተ ክርስቲያናት ህብረት በነቢያት ተብዬዎች ላይ ያወጣውን መግለጫ ተከትሎ ደግሞ ጉዳዩን ለውይይት አደባባይ ይዛ የወጣችው የሰሎሜ ታደሰን ዝግጅት ወዳጆቼ ጋብዘውኝ አየሁ:: “እንዴት እንዲህ ሲሆን ዝም አላችሁ?” አለቻቸው የኔ ቢጤ አማኞች እንግዶቿን በሰሎሜ ሾው ዝግጅቷ ላይ ፊት ፊት አቅርባ፡፡ተባረኪ፡፡እነርሱም ሽንጣቸውን ገትረው  ‹‹ሰዎቹ በእኛ ሽፋን የሚኖሩ ሀሳይ መሲህ ናቸው፡፡›› አሉና ደመደሙ፡፡ እና ማን ሀይ ይበላቸው? ነው ቁም ነገሩ! ከፕሮግራሙ በፊትም ሆነ በኋላ የነቢያት ተብዬዎቹን ጉዳይ ዘላቂ መፍትኄ አልታየም፡፡ ዛሬም በየጉባኤውና ፑልፒቱ ላይ በተአብዮ ይንጎማለላሉና፡፡የእውነት በቴአትሩማ ብሽቅ! አድርጋኛለች ስዬ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ መሀል አደባባይ  ‹‹ነቢይ ነኝ!›› የሚል ገጸ ባህሪ ግዘፍ ነስቶ መታየቱን ሰማሁ፡፡በአሜሪካን ሀገር የኢትዮጵያዊያን ስራዎችን በማሳተም ከሚተጋው ብርቱ ሰው ከኤልያስ ወንድሙ ገጽ ነበር በቅድሚያ  መረጃውን ያገኘሁት:: በሰኔ ወር  ለሦስት ተከታታይ እሁዶች ብጠይቅ የለም አሉኝ፡፡ ከወር በኋላ ትርዒቱ ከክፍለ ሀገር ጉዞው ተመልሷል አሉኝና እሁድን ጠብቄ ከጓደኛዬ ስዬ ጋር ተያይዘን ገባን፡፡ተውኔቱ ከሁለት አመት በፊት በአ.አ.ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ጥበባት ተማሪዎች ተሰርቶ መቅረቡንና ቆይቶ ወደ አ.አ ቴአትርና ባህል አዳራሽ መምጣቱንም ሰምቻለሁ፡፡ኦስሎ ማኪያቶ ጠጣ ብቻ ትርጉሙም በሶፍትመ ሀርድም ኮፒ አለህ በግማሽ ሰአት፡፡ረዳት ፕሮፌሰር ነቢዩ ባዬ የሙዚቃዊ ድራማ አዘጋጅነት ድንቅ ብቃቱን ያሳየበትን ይህን በአለም ኖቤል ሎሬት ናይጄሪያዊው አንጋፋ ደራሲ ዎሌ ሶይንካ የተጻፈውን ተውኔት እንግሊዝኛውንም ከሌሎቹ  ስራዎቹ ጋር አንብቤው ነበር፡፡ እናም ከተለመዱት ትርጉም ስራ ወጣ ያለብኝን  አፍሪካዊ ተውኔት ስታደም፤ ባቀራረቡ ምን ሊመስል እንደሚችል፡ የቱ ተቆርጦ የቱ ተቀጥሎ በምን መልኩ ቀርቦ ይሆን? የሚለውና ጋሽ ደበበ እሸቱ በድራማተርጅና የመክፈቻ ወቅት ተጋባዥ መሪ ተዋናይነት እገዛ ያከለበትን መድረክ ማየት ጓጉቼ ተቁነጠነጥኩ፡፡ ከጊቢው ውጪ የተሰቀለው ፖስተር ላይ የተጻፈው የ15ኛው ክ/ዘመን ጥቅስ ነውና ካነበብኩት ወጥ ትርጉም ያለፈ  ነቀሳ እና ወሽመጥ ሊኖረው ይችላል ብዬ እንድገምት አደረገኝ:: ከመሪ ተዋናዩ አንጋፋው ከያኒ ደበበ እሸቱ ምስል ስር፡ በዎሌ ሶይንካ ትርጉም ስራ ፖስተር ላይ፡ በአፄ ይስሀቅ ዘመን የኖሩትን የኢትዮጵያዊውን አባ እስጢፋን አባባል በማንበቤ ነው፡ ‹‹ጽኑ ነቢይ ሲነሣ እንደዚሁ ጽኑ ንጉሥ ያስነሣል›› ይላል በጉልህ፡፡እውነት ነው በእርግጥ፡፡ ቀሺም ነቢይ (ካለ) ሲነሳስ? ያለው ማነበረ? ተውኔቱ ቀላል ያሽሟጥጣልንዴ! ቴአትር ከሰሩስ እንዲህ ነው ፡፡
አዘጋጁ ነቢዩ ባዬ ከአ.አ የኒቨርሲቲ የቴአትር ጥበባት መምህርነቱና የሙዚቃና ስዕል ትምህርት ቤቶችም ኃላፊነት አገልግሎቱ በኋላ በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ መሾሙን ተከትሎ የሳንሱር ህግ ስለ መቅረቱ : ይህም ተውኔት በነፃነት ለእይታ መብቃቱ የዚያ አሻራ መሆኑ በሰፊው ይወራል:: ዶሮ ማነቂያ አርፍድ ብቻ፡፡እሰይ! ደግ! ይበል! መሰል ስራዎችን ያብዛልን! ውቤ በረሀ ቃለ ተውኔት በአፕሬቲቭ ያስተማረን ተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሠሠም ትርኢቱ በተመረቀ እለት ‹‹በህይወት ኖሬ ይህን የጥበብ ነጻነት ዘመን በማየቴ ዕድለኛ ነኝ!›› ማለታቸው፡፡ታዋቂ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ዜናውን  ማሰራጨታቸው፡፡ ለአመታት ድር ያደራበት ቤተ ተውኔትም ከእንቅልፉ እንዲያንሰራራ ተውኔቱ ትንሳኤ መሆኑ፡፡ እውነት ነው የልጅነት መዋያችን ያ ሞልቶ የማውቀው ክበብ ያዛጋል፡፡ አዳራሹ አርጅቷል፡፡ወንበሮቹ ተገነጣጥለዋል፡፡ባህል አዳራሹ ያ ከቤተሰቦቼ ጋር ኦቴሎን እና ቴዎድሮስን ስናይ የነበረው ግርማው እና ድባቡ ከስሟል፡፡ያም ሆኖ የአንጋፋው አዘጋጅ አባተ መኩሪያ የዝግጅት መንፈስ በልጁ ነቢዩ ባዬ በኩል በመድረኩ ላይ ከመገማሸር አልታገደም፡፡ተርጓሚውና መሪ ተዋናዩ  ፈለቀም ገና በልጅነቱ የትወና ክህሎቱን ሀ ብሎ ያሟሸው በዚሁ መድረክ ላይ - በባሴ ሀብቴ ተተርጉሞ በስዩም ተፈራ በተዘጋጀው የዊልያም ሼክስፒር ሮሜዮና ዡሊየት ተውኔት እንደ ነበረና  ‹እንደ አያቴ ቤት ነው የማየው›› ሲል በአርሂቡ የቴሌቪዝን ቃለ መጠይቁ አይቸዋለሁ፡፡እኔም ራሴ በልጅነቴ ነቢይ መኮንን ተርጉሞት ማንያዘዋል እንደሻው ባዘጋጀው የእንግሊዛዊው ዊልያም ሼክስፒር ጁሊየስ ቄሳር ተውኔት ውስጥ ከክበባችን አባላት ጋር በአጃቢ ሕብረ ዘማሪነት የመካፈል እድል ነበረኝ፡፡
የመጨረሻው ደወል ተሰምቶ መብራት ሙሉ ለሙሉ ሲጠፋ ድምፁን በደንብ በማውቀው አርቲስት ከ”እንኳን ደህና መጣችሁ” ሰላምታ ጋር  ተውኔቱ ከ55 አመታት በፊት የተጻፈ መሆኑን:: ሞባይል ስልካችንን እንድናጠፋ ተጠየቅን፡፡ በትርኢቱ መሀል የበጠበጠን የስልክ ጥሪ የለም ማለት ግን አይደለም፡፡55 አመት ይገርማል መቸም፡፡በ34ኛው ክ/ዘመን ጥምቀት ገና ከኢየሩሳሌምና ሰማርያ ከተሞች ሳይወጣ በጃንደረባው በኩል ያውም በሐዋርያው ፊልጶስ የተጠመቅን ጥንታዊያን ህዝቦች፡ አፍሪቃዊያን ሀገራት ከቅኝ ግዛት ነጻ ሲወጡና ክርስትና ግራ ሲያጋባቸው የጻፉትን ነው የተዋስነው፡፡ እናም ጭራሽ ጉዳዩ በእኛ ብሶ ቁጭ ያለብን! ልበልን... ለማንኛውም አሁን ወደ ትርኢቱ...
ጸጥታ ባረበበበት ጨለማ አዳራሽ ውስጥ፡ ማዕበል የሚያላጋው ውኃ ድምጽ በሙዚቃ ተቀነባብሮ  ይጀምራል፤ እሱን ተከትሎ ሙሉ  ተውኔቱን በሚያጅበው፡ ቅኝት በገባው ባለሙያ ልብ የሚሰውር የአፍሪካ ከበሮ ምት ቀስ እያለ ሲነሳ፤ ከዚያም በስስ ብርሃን በዘንባባ ያጌጠ የባህር ዳርቻ ምስል ፊት ለፊት ገጭ ሲል፡ በቀጥታ ተውኔቱ ወደተጻፈበት የምዕራብ አፍሪቃ መንደር ባህር ዳርቻ አንሳፍፎ ይወስዳል፡፡ እንደ ዶሮ እየተግተለተሉ ገብተው ቁጢጥ የሚሉትና በዶሮ ክንፍና ጩኸት ትርኢቱን በሚከፍቱት በአፍሪቃዊ አልባሳት የተንቆጠቆጡ ህብረ ዘማሪያን ዝማሬ መሀል፤ ከፍ ባለ ወንበር ላይ የተቀመጠው በደማቅ አልባሳት የተዋበው ሰው ይመጣና ፊት ለፊት አይኑን በጨው አጥቦ ቆሞ ‹‹ነቢይ ነኝ!›› ይላል፡፡ ለነቢይነቱ የሚሰጠው ማረጋገጫ ግን ተመልካቹን በሳቅ ያፈነዳው ይጀምራል፡፡ የተውኔቱ ዘውግ ሳታየር ኮሜዲ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ከቆይታ በኋላ የሚፋጠጠው አዛውንት ነቢይ ደግሞ እንዴት አድርጎ የአምልኮ ስፍራውን እንደነጨቀው ያረዳናል፡፡እባብ ለእባብ፡፡ አቶ ዤሮ ግን ምን ግዱ፤ መንፈስ  ‹‹በጸሎት ጠይቄው የጌታ ድምጽ ወደኔ መጥቶ ነቢይነትንና ቢዝነስን ሚክስ አድርገው ብሎ አዝዞኛል›› ይለናል ፍጥጥ ብሎ፡፡እኔ ሀሜተኛ ነቢይ አይደለሁም እንጂ ብዙ እምናገረው ነበረኝ ብቻ ይቅር እያለ፡ግን ደሞ ሲሰሙዋቸው ክው! እሚያደርጉ በዙሪያችን እምንታዘባቸውንና እንዳላየ የምናልፋቸውን ነውሮቻችንን ‹‹የአዳር ጸሎት አገልግሎትን እና ባሎች ፊልድ ሲወጡ ብቅ እሚሉ አጽናኝ ነቢያት ነን ባዮችን...››ወዘተ. እየነቀሰና በዚቅ እያዋዛ ይዘረግፍልናልም፡፡
ሁለተኛው ገቢር አዲስ የመኖሪያ መንደር ይሆናል፡፡ ጓዛቸውን ጠግርረው በጫኑባት በአንዲት ብስክሌት የተፈናጠጡ ባልና ሚስቶች ገብተው ያበደ ጭቅጭቃቸውን ያሳዩናል፡፡ ሚስትየዋ (ድንቅ የትወና ክህሎቷን ያሳየችን) ባሏን ንቃ!ባንን! እያለች ነው  እምትወተውተው፡፡ ‹‹በከተማዋ መስተዳድር ቢሮ የመንግስት ተላላኪዎች ኃላፊ ሹመኛ¡!›› - እንደው ለመሆኑ፡ አሁን ይኼንን ነው ስራ ብለህ እምትጠራውስ?¡ ካንተ ጋር የተማሩ እኩያ አብሮ አደጎችህ ዛሬ ሚኒስቴር ሆነዋል፡ የሚነዷቸው ሽንጠ ረዣዥም መኪኖቻቸው ብትል!!›› እያለች ቀላል ታበግነዋለች?!
....አቤት የባሏ ትእግስት! ድንቅ አድርጎ ተጫውቶታል፡፡ ከጭቅጭቋ አምልጦ ሲወጣ፤ ዱቤዋን ልትጠይቀው የመጣችው ነቢይ ብቅ ብሎ የባለ እዳነቱን ቅሌት ይከናነባል፡፡ በፍርሀት ከመንገዱ ተመልሶ ወደ ወጣበት ቤቱ ኩም ብሎ ይገባል፡፡ጠብ ያለሽ በዳቦ እምትለው ሚስት መንገደኛ አሳ ነጋዲት ጠርታ የጭቅጭቅ ሱሷን ልትወጣ ትነዘንዛታለች:: ነጋዴዋ ከልብ የማይጠፋ ዜማዋን በየንግግሮቿ መሀል እያስገባች ስታወራ ፤ ተመልካቹም ዜማዋን ተውሶ ያንጎራጉራል፡፡የወንድም ቹሜ ሚስት በነጋዴዋ ንዴት ውስጥ ሳለች ነው ነቢዩ በመስኮት እሚያመልጣት:: በዚህ እርር ድብን ባለችበት ቅጽበት ደግሞ ታምቡረኛው ምጽዋት ጥየቃ ሲገባ ብስጭቷ ሰማይ ሊነካ ይደርሳል ፡፡ እንዲህም ትላለች...
‹‹ኧረ ምንድነው ጉዱ! አገሩን ሁሉ እንዴት ያለ ቅጣምባሩ የጠፋበት መተራመስ እየዋጠው ነው በሉ?! ነቢይ ነኝ ባዩ ወሽካታ ሌባ እዳ ወስዶ እማይከፍል ቋጣሪ ተበዳሪ!  ነጋዴዋ አሣዋን ሳይሆን ዓይኗን በጨው ያጠበች የወጣላት አጭበርባሪ! እና ይኸው አሁን ደግሞ ማን ይመጣል፡ ጸጉሩን ቅጫም ሁለመናውን ተባይ የወረሰው መድረሻ ቢስ የትም ዘዋሪ፡ የገማ የጠፍር ከበሮውን እየደበደበ ትኋኑን ላዬ ላይ ሊያራግፍ የሚቅለሰለስ ተጠዋሪ! ይኼ ችጋራም ድሀ የኔ ቢጤ ለማኝም ሆነ ፡ ያ ነቢይ ተብዬም ሁላቸው ፡ ወደዛች የከረፋ አሣ ነጋዴ እናታቸው ፡ ተጠራርተው ቢሰባሰቡና ስለኑሯቸው፡ አንድ ላይ ቢማከሩ ነው የሚበጃቸው!!›› በ ለ ው!
በመጀመሪያው የባህር ዳርቻ ገቢር ላይ የሚካሄደውን የሦስተኛውን ትዕይንት እጅግ የሚሰቀጥጥ የአምልኮ ጉባኤ ለመግለጽ ትንሽ ይከብዳል፡፡እንባ እንባ ይላል፡፡ በተጠና ስልት የሚውረገረጉት አጃቢ ተዋንያን (ሕብረ ዘማሪያኑ) ዝማሬ እና ውዝዋዜያቸው እፁብ ድንቅ ነው ውበታቸው፡፡ ነቢይ ዤሮ በጉባኤው ላይ ምኞታቸው ከመንፈሳዊ ድኅነት ይልቅ  ለቁሳዊ ተስፋ እንዲሆን  ለራሱ እንዲመቹ አድርጎ ስለሚነዳቸው ምስኪን ተከታዮቹ በንቀት ከሚናገረው ‹‹የበግ መንጋዎቼ ሁሉ እርካታን ያጡ መሆናቸውን አውቃለሁ ምክንያቱም እርካታ ማጣቱንም የማድላቸው እኔ ስለሆንኩ! የትንቢት ቃል አውጥቼ ‹‹ፎገርኳቸው››! ጌታ አናገረኝ ፡ ከጌታ ጋር ተገናኝተን አወራን›› እያለ የሚቀበጣጥረው  አንጀት ያሳርራል፡፡በተለይ እንደኔ ላለ አማኝ መቋቋም ይከብደዋል፡፡አብራኝ የገባችው ጓደኛዬ ስዬም ተናድዳ  ደጋግማ አቋርጠን እንድንወጣ ጠይቃኛለች፡፡ባንጻሩ ስለ መሰል ነቢይ ተብዬዎቹ የሚዘላብደውን መስማት ደሞ ያጓጓል:: እና መጨረስ ፈለግን፡፡ እውነትም በትዕይንቱ መጨረሻ ላይ አዛውንቱ ነቢይ (ጋሽ ደበበ መተካቱ ለተመልካች  ቢገለጥ ጥሩ ነው እላለሁ) እና አዛውንቱ ነቢይ ተመልሶ መጥቶ ስለ ዤሮ አይነት ነቢይ ነን ባዮችና እውነተኛ የእግዚአብሔር አገልጋዮች እያብጠረጠረ ደፋሩን ነቢይ ነኝ ባይ ሲሞግተው ልቤ ረካ፡፡ዤሮ በትዕቢት ተመልቶ ‹‹የዚህ ዘመን ነቢይ ነኝ ብል ማን ይከለክለኛል እ!›› ሲል አዛውንቱ እንዲህ ይለዋል . . .
‹‹እሱስ ልክ ነህ ፤ ከልካይ መጥፋቱ አይደል ጉዱ! ቢሆንም ‹‹እንክርዳዱን ስትለቅሙ ስንዴውን ከእርሱ ጋር እንዳትነቅሉት አይሆንም - እስከ መከር ጊዜ አብረው ይደጉ›› ለሚለው ቃሉ በመገዛት ስንታዘብ ብንቆይ፡ ‹‹እንክርዳዱን አስቀድማችሁ ልቀሙ በእሳትም ለማቃጠል በየነዶው እሰሩ፥ ስንዴውን ግን በጎተራዬ ክተቱ›› ይላልናም ቃሉ ፤ ባንተ ክፋት የንፁኃኑ የእግዚአብሔር አገልጋዮች መታመን ሲጎድፍ ያንገበግበኛል!!!”
በዚህ የሁለት ዘመን ማንነቶች ውስጥ ብዙ ትርጉም መኖሩን እናውቀዋለን አይደል?! ለወንጌሉ በቆሰሉ እና ወንጌሉን በሚያቆስሉ ልበል ይሆን?! በሁለቱ ምልልስ መሀል ነው የአባ እስጢፋን ፖስተር ላይ ያነበብኩትን ንግግር የሰማሁት፡፡ እናም ያቺ የትዕይንቱ መዝጊያ ቅጥያ ትዕይንት ወሽመጥ መሆኗን ልብ አልኩ፡፡አባ እስጢፋ በኢትዮጵያ ከ500 አመታት በፊት ተነስተው የነበሩትንና ምናልባትም ከማርቲን ሉተር 30? አመታትን ቀድመው ተቃውሞ ማሰማት የቻሉት (ፕሮቴስት ያደረጉት) የደቂቀ እስጢፋኖስ እንቅስቃሴ መስራች ነበሩ፡፡አዘጋጆቹ ተውኔቱን ከግብ ለማድረስ ያበጁት ይሆናል፡፡ ነው፡ ኤልሳቤጥ መላኩ እንደ ጋሽ ደቢሾ ሞግታ አፃፅፋለች rewrite አሉ፡፡ ተረት ሰፈር አምሽ ብቻ፡፡እናም አይጎረብጥም፡፡እንዲያውመ መኖሩ ይጠቅማል፡፡ለማለዘብ፡፡ለማስረዳት ይረዳል እኔ እንዳየሁት፡፡ወፍ እንደ አገሩ ይጮሀል፡፡ሕብረ ዘማሪያኑም ተከትለው - ‹‹ነቢይ ዤሮ ዤሮ ዥሮ - ዜሮ ዜሮ! ›› እያሉ በነቢይ ነኝ ባዩ ላይ ክፉኛ ያሳለቁበታል፡፡
ቀጣዩ አራተኛ ትዕይንት የባልና ሚስቱ ታሪክ ከነቢይ ነን ባዩ መሰሪነት ጋር የተሰናሰለበት መንገድ ድንቅ ነው፡፡ ተውኔቱን ዘርዝሬ እንዳልጨርስባችሁ  ልዝለለው፡፡
የመዝጊያው ትዕይንት የሚያመጣልን አዲስ ገጸ ባህሪ ሚኒስትር ለመሆን የቃተተ አንድ የፓርላማ አባልን ነው፡፡ ነቢዩ በደካማ ጎኑ በኮልታፋነቱ አጥምዶ ሲያንበረክከው እናያለን፡፡ ባለስልጣኑ ቀልቡን ከተቀማ በኋላ በምኞት ይነሆልላል፡፡እንዲህም ይላል .....‹‹ነቢይዬ ይህንን ኮልታፋ ምላሴን እንደ ቶር በሰላ ምላስ ሲከይልልኝ ሀገሌን በንግግል ሰት ለት አድልጌ አስተዳድላለሁ!›› በ - ለ - ው...!!!
በትርኢቱ መሀል አዳራሹ ውስጥ እንደየሁኔታው እኔን ራሴንም ጨምሮ ለምሳሌ የጠበል መጠመቅ ትዕይንት ሲታይ  ያንዱ ኃይማኖት፤ በልሳን መናገር ሲታይ ደግሞ የሌላው ኃይማኖት (ስዬ) ተከታዮች ሲስቁ ማስተዋል ይቻላል፡፡አንዱ ባንዱ ሲስቅ ነው ነገሩ፡፡በበኩሌ እውነታው  ግን “ነቢይ ዤሮ’ ቴአትር እከሌ ከእገሌ ሳይል ሁላችንም ራሳችንን  እንድናይበት የቀረበ የአስመሳይነታችን hypocrisy ጭምብል የሚገለጥበት የጥበብ ውጤት ነው፡፡ደራሲው እንደሚለው የጭፍን እምነትና ጭፍን አማኞች Blind belief and believers አርእስተ ጉዳይ ላይ ነው እሚያጠነጥነው፡፡ ይህን ወቅታዊ ጭብጥ ያዘለ፡ የመጀመሪያው ጥቁር የሥነ ጽሁፍ ኖቤል ተሸላሚ የሆነውን ታላቅ ደራሲ ስራ ከተጸፈ 55 አመት በኋላ የተረጎመልንን፡ ያዘጋጀልንን እንዲሁም በሀገራችን መድረክ ያቀረበልንን የአአ ቴአትርና ባህል አዳራሸን ባጠቃላይ በስራው ለተሳተፉት ሁሉ የከበረ ምስጋና ማቅረብ ግድ ይለናል፡፡ ውለታችሁን ጥበብ ትክፈላችሁ፡፡ተባረኩ፡፡  
‹‹እሺ ታዲያ ቅድም ‘ሰሎሜ በፕሮግራሟ ላይ ያቀረበቻቸው’ ያልሽኝ እንግዶች -  “ነቢያት ነን ባዮቹ እኛን (ስንዴ)ይመስላሉ እንጂ እውነተኛ አይደሉም “ብለዋል አልሺኝ፤  እና ታዲያ ሌሎቻችሁስ? እንክርዳዶቹን አምናችሁ ተቀብላችሁ ነው ወይስ እነሱን መስላችሁ ተመስላላችሁ ዝምታችሁ?....አለችኝ ጓደኛዬ ስዬ ከግቢው ሳንወጣ፡፡ ጸጥ አልኩ፡፡ጸጥ እረጭ!ምንም መልስ የለኝማ፡፡ዝም ብቻ እንጂ፡፡አንድ ቀን እመለስበት ይሆናል፡፡ ከዚያ በፊት ሌሎች ትርኢቱን ያዩ የሚሉትን ባውቅ መልካም ነው፡፡ በበኩሌ ግን ለዛሬ ከተውኔቱ መካከል የነቢይ ዤሮን አንዲት ንግግር ጠቅሼ ልሰናበት . .
‹‹ እነዚህ እውነተኛ አገልጋዮች እያሉ ሰው እንዴት ተረጋግቶ የቸርች ቢዝነስ ለመስራት ይቻለዋል?! ›› ሕብረ ዘማሪያኑ እየተቀባበሉ ያዜማሉ ‹‹እንክርዳድ እንክርዳድ!
 ስንዴ! ስንዴ!
ወየው ጉዴ!!!
በሳቅ እያንፈራፈረ የሚያዝናናው ተውኔት በሀሳብ ሙግቶች ልቦና እና  ዘመናችንን  ያጠይቃል...
ወንጌሉ ‹‹በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን›› ነበር የሚል፡፡ባንፃሩ ቁልቁል ወደ ባርነት መንደርደሩን ተያይዘንዋል፡፡ኢትዮጵያዊያን በነጻነት የኖርን ሉአላዊ ሀገር ነን እያልን በከንቱ ስንደገግ፤ ወይ ራሳችንን አልሆንን፤ ወይ ከቅኝ ግዛት ለመላቀቅ ብርታት እንደተጎናፀፉት አፍሪቃዊያን አልሆንን፤ መሀል ላይ የዋለልን ህዝቦች አይደለንምን?!...
“እንኪያስ ምንድርነው?” ይላል የካህኑ ልጅ የዎሌ ሾይንካ ምናበ ዘረ ኢዮሮብዐም - ዤሮ . . .

Read 662 times