Saturday, 17 August 2019 14:09

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(0 votes)

 “እግዜር የበደለው “ራሱን” ነው፡፡ “ነፃ ማውጣት” የፈለገውም ራሱን ነው፡፡ “አምሳያዬ” ብሎ የፈጠረው ሰው፤ እንዳሰበው አልሆነለትም፡፡ ሰው ቢሆን “እግዜር ይቅር በለኝ” ይላል፤ ዳኝነት የሱ በመሆኑ:: ሰው የሚበድለው፣ የሚጐዳው የገዛ ወንድሙን ነው፡፡ ሌላውን ሰው፡፡ እግዜርንማ የት ያገኘዋል?”
         
          ገዳዩ ባልታወቀው ባሏ ሞት፣ “እጇ አለበት” እያሉ ያወሩባታል፤ ሴትየዋን፡፡ አንድ ቀን ይቺ ምስኪን ወደ ውጭ ለመውጣት የግቢውን በር ስትከፍት፣ ከሞተ አንድ ዓመት ያለፈው፣ የምትወደው ባሏ፤ ከመንገዱ ባሻገር ቆሞ የተመለከተች መሰላት:: ያውም የምትወደውን ካፖርትና ባርኔጣ አድርጐ::  በድንጋጤ አማትባ ወደ ኋላዋ ደነበረችና በሩን ጠረቀመችው፡፡ ነፍሷ ስትመለስ ያየችውን ለማረጋገጥ በቀዳዳ አጮለቀች:: ማንም የለም፡፡ ራሷን ተጠራጥራ ለወዳጆችዋ ብትናገር አላመኗትም፡፡ ልብሱ ቁምሳጥኑ ውስጥ አለመኖሩን ብታሳያቸውም “በጀ” አላሏትም፡፡
ከጥቂት ወራት በኋላ አንድ የገበያ ማዕከል ውስጥ ከባለቤቷ ጋር በሩቁ ዓይን ለዓይን ተገጣጠሙ፡፡ ራሷን መቆጣጠር አልቻለችም፡፡ ወዳጆቿ “ቅዠት ነው፤ ፀበል ተጠመቂ” አሏትና እንደተባለችው አደረገች፡፡ ሰውየው ግን አልቀረም፡፡ ብቻዋን በምትሆንበት ጊዜ፣ የግቢውን በር ከፍቶ ይታያትና ይሰወራል፡፡ ወይም በመኝታዋ መስኮት በኩል ውልብ ይላል፡፡ አንዳንዴ መኪናዋን ካቆመችበት ለመሄድ ስታስነሳ፣ መንገድ ሲያቋርጥ ታየውና፤ “ኡ ኡ” ትላለች፡፡ ማንም አልተረዳትም፡፡ እንደውም “ስራዋ ነው እንዲህ እሚያቃዣት” ማለት ተለመደ፡፡
አንድ ቀን በቤቷ ስልክ ደውሎ መጠነ ብዙ ገንዘብ፣ ከቆዳ ጃኬቱና ከከረባት ጋር መቃብሩ ቦታ እንድታመጣለት ቀጠራት፡፡ ለሚመለከታቸው ተናገረች፡፡ “አይዞሽ ሂጂ፤ እኛ ተደብቀን እናያለን” አሏት፡፡ ጤነኛ መሆን አለመሆኗን የሚያረጋግጡበት አጋጣሚ ተከሰተላቸው፡፡ ወደ ቤቷ ስትመለስ፤ “አንቺ ከሃዲ! ለምንድነው ለሰዎች የምትናገሪው? እነ እገሌ ተደብቀው ሲመለከቱ እንደነበር አይቻለሁ፤ የጠየኩሽን እዚሁ ቤቴ በረንዳ ላይ አስቀምጪልኝ፡፡ በሚመቸኝ ሰዓት መጥቼ እወስደዋለሁ” የሚል ወረቀት በሯ ላይ አገኘች:: ፈራች፤ ተንቀጠቀጠች፤አማራጭ የላትም:: የታዘዘችውን አስቀምጣለት፣ ጓደኛዋን አብራት እንድታድር አደረገች፡፡ ስትጨነቅና ስታዳምጥ ሌሊቱ ነጋ፡፡ ምንም የሰማችው፣ “ኮሽ” ያለ ነገር አልነበረም፡፡ ውሾቹም አልጮሁም፡፡ በረንዳው ላይ ያስቀመጠችው ዕቃ ግን ተወስዷል፡፡ ተመሳሳይ ነገር ተደጋገመ፡፡ ሴትየዋ ታመመች፡፡
መታመሟ ተነግሮት ሊጠይቃት ለመጣው፣ “መጽሐፍ ያሳበደው፣ ባለ አቢሾው” እየተባለ ለሚወራበት፣ ውጭ አገር ለሚኖረው፣ የወንድሟ ጓደኛ ግን እንቆቅልሹን ለመፍታት “ደቂቃ” አልፈጀበትም፡፡ እንዴት??
***
ወዳጄ፡- የእግዜር “ሲቪ” ሲነበብ፣ “ሰውን በመፍጠሬ ተፀፀትኩ” የሚል ይገኝበታል፡፡ አጥፍቻለሁ፤ ተሳስቻለሁ፤መሆን ያልነበረበትን፣ መደረግ የማይገባውን በማድረጌ ቅር ብሎኛል ማለቱ ነው፡፡ ነቢያቱንም፣ መልዕክተኞቹንም፣ ህዝቡንም ባንድ ቋት ነው ያጨቃቸው፡፡ “ከዝንጀሮ ቆንጆ…” እንደሚባለው ሆኖበት ወይም “ለሃጥአን የመጣ ለፃድቃን፣ ከኑግ የተገኘሽ ሰሊጥ አብረሽ ተወቀጭ” በማለት አስቦም ሊሆን ይችላል፡፡ ቁም ነገሩ ስህተቱን ማመኑና “ሲቪው” ላይ እንዲጠቀስ መፍቀዱ ነው፡፡ “ልክ ነው ተሳስተሃል” የሚለው ማንም የለማ፡፡
እግዜር የበደለው “ራሱን” ነው፡፡ “ነፃ ማውጣት” የፈለገውም ራሱን ነው፡፡ “አምሳያዬ” ብሎ የፈጠረው ሰው፤ እንዳሰበው አልሆነለትም፡፡ ሰው ቢሆን “እግዜር ይቅር በለኝ” ይላል፤ ዳኝነት የሱ በመሆኑ:: ሰው የሚበድለው፣ የሚጐዳው የገዛ ወንድሙን ነው:: ሌላውን ሰው፡፡ እግዜርንማ የት ያገኘዋል? “እግዜር ማለት እኔ ነኝ፤ እግዜር የእያንዳንዱ ሰው ህሊና ነው” ብለው ከሚያስቡ በስተቀር፡፡ እንደነዚህ ዓይነት ዐዋቂዎች ሲሳሳቱና ሲፀፀቱ ይቅርታ የሚጠይቁት ልብና አእምሮአቸውን ነው፡፡ እንዲህ ሲሆን ሰውና አማልክት፣ ፈጣሪና ፍጡር ይዋሃዳሉ፡፡ እዚህ ጋ ሌላውን መበደል ራስን መጉዳት ከሆነ፣ ሌላውን ማገዝም ራስን መጥቀም ይሆናል---በግልባጩ:: ስህተቶቻችን አንዱ በህይወት የመኖር ገጽታችን በመሆናቸው ለስራም፣ ለጓደኝነትም፣ ለህዝብ አገልጋይነትም፣ ለቤተሰባዊ ኑሮም “ሙሉ በኩልኬ” ለመሆን፣ ሲቪያችን ላይ ካልተጠቀሱ፣ እኛነታችን ሙሉ አይሆንም የሚል ነው፡፡
ወዳጄ፡- ነገስታትም ይሁኑ ፖለቲከኞች፣ ሳይንቲስቶችም ይሁኑ ጥበበኞችና አርቲስቶች፣ በታሪክና በኑሮ መንገድ ላይ በተሳፈሩበት አጋጣሚ ያገኙትን ዕድል፣ ስልጣንና አጋጣሚ፣ በነበራቸው ወይ ባላቸው ዐቅምና ችሎታ፣ ኃላፊነታቸውን የተወጡ መሆን አለመሆናቸውን፣ ትርፍና ኪሳራቸውን ስናሰላ፣ የነበሩበትን ጊዜና ወቅት፣ እኛም እነሱ በነበሩበት ቦታ ብንሆን ምን ልናደርግ እንደምንችል ከግምት ውስጥ ካላስገባን እንሳሳታለን:: ያለአግባብ እናሞግሳቸዋለን ወይም ነውራቸውን እናጐላለን፡፡ ደግነቱ ህይወት ያለ ማቋረጥ የሚፈስ ወንዝ መሆኑ ነው፡፡ “የነበረ ጊዜ”፣ የያኔዎቹ “እነሱና” ያለነው እኛ፤ “አሁን” ላይ የለንም፡፡ ውሃ እየጋለበ፣ ውሃ እየተተካ ነው፡፡ ሻጋታው አስተሳሰባችን ግን በደንብ ታጥቦ አልፀዳም፡፡ ጨለማ ጐን  የሌለው ሰው አንድም የለም፡፡ እግዜር ሰውን በመፍጠሬ ተሳሳትኩ ብሎ አንድ ላይ የደቆሰን ለዚህ ነው፡፡ ስለዚህ ወዳጄ፡- እግዜር እንዳደረገው፣ የኛም “ሲቪ” ላይ ስህተቶቻችን ቢጠቀሱ ምን ይመስልሃል፡፡
ጨለማና ብርሃን ደብለው በውስጤ
ሲበራ ሲጨልም በሚውለው ቀኔ
በበጐም በክፉ “ሰው” ሆኛለሁ እኔ
ዕድሜ ሆኖ ያልፋል - ትርጉምና ፍቺው
                  በኑሮ ሚለካ
የቅርብ ሩቅ ሆኖ፣ እያለ ያጣሁት
              በጄ ነበር ለካ!!
ራሴ ለራሴ የዘረፍኩት ቅኔ
ሚስጢሩ ሲገለጥ አንድ እኔን መሆኔ!
--ይልሃል ገጣሚው፡፡
***
ወደ ጨዋታችን እንመለስ፡- በውጭ አገር የሚኖረው ወንድሟ፣ አዲስ አበባ ለሚኖረው ጓደኛው ስልክ በመደወል፣ እህቱ የደረሰባትን ነገር በዝርዝር በማስረዳት፣ ሄዶ እንዲጠይቃት “አደራ” ይለዋል፡፡  ጓደኛውም ሴትየዋን አግኝቶ እያጫወታት ስለ ባለቤቷ፣ ስለ ራሷና ስለሆነው ሁሉ አንዳንድ ጥያቄዎችን ከጠየቃት በኋላ ግቢውን ተዘዋውሮ ተመለከተ፡፡ ስለ ተከራዮቿ ማንነት የምታውቀውን ዝርዝር ሁኔታዎች ነገረችው፡፡ አጅሬ እንቆቅልሹን ለመፍታት አፍታም አልፈጀበትም፡፡ ከዚያ በፊት ግን የአንደኛውን ተከራይ “ፕሮፋይል” ለማየት ወደ ሰውየው መስሪያ ቤትና ኮምፒውተር ቤት ጐራ ማለቱ አልቀረም፡፡ ሲመለስ ባሏ እሷን ከማግባቱ በፊት ከሰራተኛው ወልዶ የካደው ልጅ እንደነበረው፣ መልክና ቁመናው ከአባቱ ጋር እንደሚመሳሰል፣ ካለፈው አንድ ዓመት ከሁለት ወራት ጀምሮ አባቱን ለመበቀል፣ እዚህ ግቢ ተከራይቶ እንደሚኖር፣ የባሏን ልብሶች የሰረቀው እሱ መሆኑን፣ ሜክአፕ በመጠቀም ዕድሜውን ከፍ ለማድረግና ፍፁም “አባቱን” ለመምሰል እንደሚችል --- ወንጀለኛው እዚህ ግቢ እንደሚኖር፣ የጥርጣሬው መሰረት ያደረገው ደግሞ ሲወጣና ሲገባ፣ ውሾቹ አለመጮሃቸው መሆኑን በማስረዳት--የተረፈው የፖሊስ ስራ መሆኑን ነገራት:: ሴትየዋ ዳነች፡፡
ለወንድሟ ደውላ ስትነግረው፡-
“እንደዚህ ነን እኛ!” አላት፡፡
“ካ! ካ! ካ! እናንተ እነማን ናችሁ?”
“አብሿሞቹ!!”
ወዳጄ፡- ለማንኛውም፣ ስህተቶችህን ሲቪህ ላይ መጥቀስ እንዳትረሳ፡፡
ሠላም!!


Read 1107 times