Saturday, 17 August 2019 12:52

የቡሄ ትዝታ

Written by  ደ. በ
Rate this item
(1 Vote)

የጅራፉን ጩኸት የቤተክርስቲያኑ ዐፀድ እያስተጋባ ሲመልስ መምህሩ፤ “ዝም ብሎ ጅራፍ ገምዶ ማስጮህ ብቻ ዋጋ የለውም፤ ትርጉሙን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡” ሲሉ ጓደኞቹም ተያዩ፡፡ ከውጭ ሆኖ የሚያንጣጣው ማን እንደሆነም ያውቁታል፡፡ በላቸው ነው:: ወደ ቤተክርስቲያን ሲገቡ፣ “አልገባም” ብሎ ተጨናንቆ ነው የቀረው፡፡ የጅራፍ ሱስ አለበት:: በተለይ መጋረፍ ይወድዳል፡፡ ይሄኔ ጓደኞቹ እስኪወጡለት እያዛጋ ይሆናል፡፡ እጁ ብቻ አይደለም ሱሰኛ፣ ነፍሱ ነው፡፡
መምሬ፤ “ጌታችን ታቦር ተራራ ሲወጣ፣ የወረደበት የክብር ደመና እንዲህ ቀላል አይደም፡፡ ታላቅ በዐል ነው፡፡ ያዕቆብ፣ ጴጥሮስና ዮሐንስ… የጌታችን ሃዋርያት…” ወደ ግቢው አጥር እየተጠጋ የመጣው ጩኸት ረበሻቸው:: ጅራፎቹ ብዙ ሆኑ፡፡ ከዚያ በኋላ መምሬ ሁለት ወጠምሾች አሥነሱና “እነዚህን ረባሾች አምጡልኝ” አሉ፡፡
ያሬድ የሚባለው ከሁሉም ተለቅ ያለው ተነሳ፡፡ ሴቶቹ ፍርሃት ፍርሃት አላቸው፡፡ በተለይ ሜሮን ዐይኗ እንባ አንጠለጠለ፤ በላቸውን እንደሚይዙት ጠርጥራ ልቧ ደረቷን ደበደበው፡፡
ውጭ ያለው ድምጽ ባንድ ጊዜ አባራ፡፡ የሩጫ ኮቴ ብቻ ይሰማል፡፡ እየተባረሩ ነው፡፡ ትንሽ ቆይቶ በላቸውና አንድ ጓደኛው ከነጅራፋቸው ብቅ አሉ፡፡ ሁሉም ብድግ ብድግ አሉ፡፡  
መምሬ ፊት ሲቀርቡ አንገታቸውን ደፉ፡፡ በላቸው እንባው እየፈሰሰ ነበር፡፡ ‹‹አልተመታህ… ምን ያስለቅስሃል!›› አሉት፡፡
“ያሬድ በድንጋይ ወርውሮ እግሬን መትቶኛል!” ብሎ ሱሪውን ጠቀለለና እግሩን አሳያቸው፡፡
“ማን ምታው አለህ?...በዐውዳመት ሰው ይመታል?!” ብለው በያዙት መቋሚያ አንድ ሁለቴ አቀመሱት፡፡
ሜሮን ደስ አላት፡፡ “የታባቱ” አለች፤ በልቧ፡፡ ደሞ ሥታስበው በዐውዳመት ሰው አይሰድብም፡፡
“ቅዱስ ባለወልድ ይቅር በለኝ! ተሳስቻለሁ” አለች በልቧ፡፡
ከበላቸው ጋር አይን ላይን ተጋጠሙ፡፡ እሱ በዕድሜ ከሷ ከፍ ይላል፡፡ ግን ፀባዩን ይሁን አለባበሱን ትወድደዋለች፡፡ ደሞ ጐበዝ ተማሪም ነው ይባላል፡፡ ለነገሩ ለጉብዝናው እርሷም አታንስም፡፡
“አንቺን ደግሞ ምን ያስለቅስሻል?!” አሉና መምሬ ድንገት አጠገቧ መጡ፡፡
የምትይዘው ጠፋት፡፡ ምን ትበል?
“አይ የነገሩኝ ነገር ትዝ ብሎኝ ነው!”
“ምኑ?”
“ጌታችን ከደቀመዛሙርቱ ጋር ወደ ተራራ የወጣው…”
“ይህ ምኑ ያስለቅሳል? ባይሆን የስቅለት ቀን ብታለቅሺ ነበር ጥሩ!”
“ተራራ ያስፈራል!”
“መስቀል አያስፈራም?”
“ቢያስፈራም ህይወት ይሰጣል ብዬ ነው፡፡”
“ይቺ ልጅ ያማታል እንዴ?” በመቋሚያ ቋ! አደረጓት፡፡ “ትምህርቱን አታዳምጡም ማለት ነው?!፡፡ ከጅራፍና ከትምህርት የቱ በልጦ ነው ልባችሁን የወሰደው?”
“አይ ጅራፍ በጣም ይጮሃል!”
“የኔስ ድምጽ አይሰማም?”
አቀርቅራ “ይሠማል” አለች፡፡
በላቸውንና ጓደኛውን፤ “ቁጭ ብላችሁ ትማራላችሁ ወይስ ትሄዳላችሁ?” ሲሉ ጠየቋቸው፡፡
“እሄዳለሁ!” አለ በላቸው፡፡
“የትልቅ ሰው ልጅ ሆነህ እንዲህ በተስኪያን መሸሽህ ይገርማል! በል ሂድ››
እየበረረ ወጣ፡፡
“ዛሬ ቀላል በዐል አይደለም፤ ኤልያስና ሙሴ በደመና ከሰማይ የተላኩበት አስደናቂ ቀን ነው:: ዝም ብሎ ጅራፍ ማጮህ ብቻ አይደለም፡፡ ሶስቱ ሃዋርያት ለጌታና ለነሙሴ ዳስ ሰርተው እዚያው መኖር የተመኙበት የክብር ቀን ነው፡፡ ይህንን ሳታውቁ ዐውዳመት አታክብሩ! ጭራሮ ለቅሞ መለኮን ብቻ ትርጉም የለውም!”
አሁንም ከውጭ ጅራፉ ተንጣጣ፡፡
“ፈጣሪ አልታረቅ ያለን ለዚህ ነው! ሀገራችን ጠብና ክርክር፤ ሞትና ጭንገፋ አልላቀቅ ብሏታል፡፡ ስምንተኛው ሺህ ነው!”
ሜሮን ስቅስቅ ብላ አለቀሰች፡፡ ስምንተኛው ሺህ ሲባል ትፈራለች፤ ያንቀጠቅጣታል፡፡
ጓደኞቿ ሁሉ ወደሷ አፈጠጡ፡፡
“ምን ያስለቅስሻል?”
“ስምንተኛው ሺህ… ፈራሁ!”
“አከከከከ…ፈርተሽ የት ልትሄጂ!? ሰማዩ የደም ጢስ ይለብሳል፡፡ እናት ልጆቼን ምን ላርጋቸው ብላ መካንነት ትመኛለች፡፡ ሰማይና ምድር ዋይ ዋይ ዋይ ይላሉ፡፡ መላዕክት በመለከት ድምጽ ሰደፋቸውን መዝዘው ይወርዳሉ፡፡ ያኔ ምን ትሆኚ!?”
ድንገት ከውጭ በከፍተኛ ድምጽ ብዙ ጅራፎች ሲንጣጡ፣ በድንጋጤ ልጆቹ ሁሉ ግር ብለው እግሬ አውጪኝ አሉ፡፡
ሜሮን ከዚያን ቀን በኋላ ቤተክርስቲያን ሄዳ አታውቅም፡፡ በኋላ አድጋ ሰዎች ለህፃናት የማይገባ ትምህርት መማሯን ሲነግሯት ነው ልቧ የተመለሰው፡፡ ዩኒቨርስቲ ገብታ የመጀመርያውን ቡሄ ስታከብር፣ በላቸው አጠገቧ ነበር፡፡ የዕድል ነገር ሆኖ እርሷ አንደኛ ዓመት ተማሪ ሳለች እርሱ አራተኛ ዓመት ደርሷል፡፡
ሰላምታ ሲለዋወጡ ኖረው፣ አንድ ቀን ሲገናኙ ያወሩት፣ ይህንን የቡሄ ትዝታ ነበር:: ያኔ ግን መምሬ አልነበሩም፣ ሁለቱም አዘኑ፡፡ ትዝታቸው ሞቀ፡፡
በተለያየ ጊዜ እየተገናኙ ሲገባበዙና ሲጨዋወቱ፣ በላቸው ቀልቧን ሰልቦታል፡፡ ሁሉ ነገሩ ይመቻታል፡፡ ሰው ያከብራል፣ ምክንያት ይቀበላል፡፡ ይሁን እንጂ ልቧን የከፈለው ነገር አለ፡፡ የሚታገላት - ምክንያት ውስጧን አንቆታል፡፡
እስክታየው ትንሠፈሰፋለች፡፡ አብረው ሲሆኑ ትረካለች፡፡
በላቸው ነገሯ አልገባ ስላለው፣ አንዳንዴ የምታፈገፍግበትን ምክንያት ለማወቅ ሞከረ፤ ግን ልቧን አላነበበውም፤ ስሜቷን አልጨበጠውም:: አንድ ቀን ግን ከከተማ ውጭ ይዟት ሊሄድ ወሰነ፡፡ የማያስፈልጋቸው ነገር ሁሉ ሙሉ ነው፡፡ መኪና አለው፣ አባቱ የዘነጠ ቪላ ሰጥተውታል፡፡ በስሙ የባንክ አካውንት አለው፡፡ ይህንን ደግሞ የማትመኝ ሴት የለችም፡፡ ሜሮን ይህ ሁሉ እያለ፣ ስሜቷ መቀዛቀዙ ግራ አጋባው፡፡
ከአዲስ አበባ ሐዋሳ ድረስ ሲጓዙ፣ ብዙ ነገር አውርተዋል፡፡ ቢሆንም ሃሳቧ ሩቅ ነው፤ አይደረስበትም፡፡ በዚያ ላይ ገላዋን አታስነካም፤ ክብሯን አታስደፍርም፡፡
ነገሩ ሊገባው አልቻለም፡፡ ብዙ ነገሮችን አወጣ፣ አወረደ፡፡ መልስ የሌለው እንቆቅልሽ ሆነበት፡፡
“ከሀገር ውጭ ቃል የገባሽለት ሰው ይኖር ይሆን?”
“ማንም የለም!”
“እና አትወጂኝም?”
“እወድሃለሁ”
“ያልተቀበልሺው ምኔን ነው?”
“ጀርባህን?”
ደነገጠ፡፡
“አልገባኝም?”
“እኔና አንተ ባልና ሚስት መሆን አንችልም:: ከዚያ ውጭ ከልጅነቴ ጀምሮ ነው የምወድህ። በመምሬ ፊት ያለቀስኩት ላንተ አዝኜ ነበር…፡፡”
“ታዲያ አሁን ምን ነካሽ? መቸም በውበትሽ ተመክተሽ አይመስለኝም!”
“በፍፁም አንተስ ምን አነሰህ!?”
“እና ምንድነው?”
“ተራራ አልወድድም”
“የምን ተራራ!?”
“ቤተሰቦችህ ተራራ ናቸው፤ በጣም ሀብታም!! የኔ ቤተሰቦች ደግሞ የሸለቆ ያህል ሥር ያሉ ናቸው፡፡ ህመም ይሆንብኛል፡፡ መሳቀቁን አልችለውም፡፡ አንተ ቤተሰቦችህ ብቻ ሳይሆኑ አጐቶችህና አክስቶችህ ሳይቀሩ ቱጃሮች ናቸው:: እኔ እዚያ ውስጥ ገብቼ ምን ልሆን እንደምችል አስበው፤ ይልቅ እየወደድኩህ እኖራለሁ፡፡››
“አይደለም፤ ነው!”
“ይህማ እጅግ ከባድ ነው”
ይህ ቀን የተለያዩበት ቀን ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ዐመትም ሳይሞላ፣ በላቸው ሞተ ተባለ፡፡ ያኔ ህይወቷ ሁሉ ሞተ፡፡ አሁን ከብዙ ዓመት በኋላ፣ ቡሄ ላይ በላቸው ትዝ አላት፤ መምሬም ትዝ አሏት፡፡
ጅራፉ ትዝ አላት፡፡
“ምን ሆነሻል አንቺ… ቡሄ ላይ የሆነ በሽታ አለብሽ?” አላት ባለቤቷ፡፡
“በሽታ የለብኝም፤ ጤነኛ ነኝ”
“እና ምንድነው?”
“ፀፀት”
“የምን ፀፀት?”
“የሰው ፀፀት!”
ይልቅ ተነሽ… ችቦውን አቀብይኝ”
“አላቀብልህም፤ ችቦ ሳይ ልቤ ይቃጠላል፡፡ ብርሃኑ የነፍሴን ርቃን ይጋልባታል”
“ያምሻል ልበል?”
“በጣም ያምመኛል? ተራራ ጠልቼ ሸለቆ መግባቴ!”
መኪናውን አስነስቶ፣ ወደ ሆስፒታል በረረ፡፡
“ደስ ይበልህ! የኔ ህመም ትዝታ ነው!?”
“ታዲያ ትዝታን አግቢያ!”
“ታዲያስ! ባሌ ማን መሠለህ? የቡሄ ትዝታ ነው!”

Read 2698 times