Saturday, 09 June 2012 11:12

የሁለተኛው ባል በጐነት

Written by  አንድነት ግርማ
Rate this item
(0 votes)

እኔ አልወደውም፡፡ ስለምንም ግን አይደለም፡፡ ለሷ ለሚስቱ ስለሚያሳየው ባህሪ እንጂ፡፡ ከእኔጋማ ሰላምታም የለንም፡፡ እንደውም እሱ እስከመፈጠሬም ላያውቅ ይችላል፡፡ የኛን በረንዳ እና የነርሱን በረንዳ ከሚለየው ቀርከሃ ግርዶሽ አጮልቄ በሳሎናቸው መስኮት አይኖቼን አሻግሬ ሲመታት ደጋግሜ አይቼያለሁ፡፡ አሁንም ትንሽ ቆይተን አብረን ልናይ እንችላለን፡፡ አዎ ሲመታት፡፡ የተዘጋጀ ፊልም አለ ማለቴ ግን አይደለም፡፡ እንደውም መጣላችሁ፡፡ ከቀኑ 11፡30 ሆኗል አይደል? ከስራ መመለሱ ነው፡፡ የግቢያቸው የቆርቆሮ በር ሲንቃቃ ነው ያወቅሁት፡፡ ፈጠን ብዬ ከነበርኩበት በረንዳ ወደ ሳሎን ገባሁ፡፡ ሳሎን በር ላይ ተለጥፌ ትንሽ ቆየሁ፡፡ በኮቴው ድምፅ ወደ ቤት መግባቱን አረጋግጬ ወደ በረንዳ ወጣሁ፡፡ በእርግጥ በረንዳችንን የሚለየው ቀርከሃ ግርዶሽ ከአይኖቹ በበቂ ሁኔታ እንደሚሸፍነኝ አውቃለሁ፡፡ ግን ጥላው እራሱ ይከብደኛል፡፡ አሁን የሰማሁት ኮቴ እራሱ ቀፎኛል፡፡ ይህን ሰው እናንተ እራሳችሁ ለአንድ ሳምንት ያህል ብታዩት የኔን ስሜት በእርግጠኝነት ትጋሩታላችሁ፡፡ የሽንት ቤት ዝንብ ያህል ይቀፋችሁዋል - ስለ አካሉ ሳይሆን ስለምግባሩ መቆሸሽ፡፡

“ሂጂ አይንሽን ማየት አልፈልግም” ሲላት ሰማሁ፡፡ ሳጠራው ላይ ሄጄ ተለጠፍኩ፤ በቀዳዳዎቹ ለማየት እንዲመቸኝ ሆኜ፡፡
አይኗን ከሱ ላይ አንስታ መሬት ላይ አሳረፈችው፡፡ ተመልሳ በእርጋታ እይታዋን ከመሬት ላይ አንስታ በጨረፍታ እና በስስት አየችው፡፡ የሳሎናቸው በር እና መስኮት ክፍት ስለሆነ እያንዳንዱ ነገር ይታያል፡፡
“አይንሽ ይጥፋ” አላት፤ ከቃላቶቹ የበለጠ ጠጣር ጥላቻ ከሰውነቱ እየረጨባት፡፡ አጠፋችው፡፡ አይኗን ሙሉ ለሙሉ መሬት ላይ ተከለችው፡፡ መለስ ብላ ወጣች፡፡
ፈጠን ብዬ ወደ እኔ ሳሎን ገባሁ፡፡ ስድቡን አሊያም ዱላውን ሲያቆምላት በጓሮ በኩል ወደ እኔ ነው የምትመጣው፡፡ “እንዴት ነው ባለቤትሽ መጣ?...” እንዳላወቅሁ ሆኜ ጠየቅኋት፡፡ የኛን የሳሎን ግርግዳ ተሻግሮ እንዳይሄድ ድምፄን ቆጥቤ፡፡
“አዎ መጥቷል፡፡ ስራ ስለዋለ ልረብሸው አልፈለኩም” እንደተለመደው በአንድ ጐኗ አጋድላ ወገቧን ይዛለች፡፡
“ግን እንዴት ነው ይህን ያህል የምትሳሽለት?” በከፊል ከልቤ በመገረም፤ በከፊል ደግሞ ስላቅ ነበር፡፡
“እሱም እኮ እንዲሁ ነው፡፡ ይወደኛል፡፡ ይሳሳልኛል፡፡ በአይኑ ሙሉ እንኳን አያየኝም፡፡ የዋህነቱ እና ገራገርነቱ ይደንቀኛል”
እሷ እንዲህ ስትለኝ ደግሞ ለሱ ያለኝ ጥላቻ ሆዴ ውስጥ የበለጠ እየደደረ፤ የበለጠ ቅርፅ እየያዘ ሄደ፡፡
2
በነጋታው ደግሞ እንዲሁ ከስራ መመለሱን ከበር ውጭ ህፃናትን ሲቆጣ ድምፁን ሰምታ ከኛ ቤት በፍጥነት በመውጣት በጓሮ በኩል ወደ ቤቷ ገባች፡፡ ‘ቤት አላት’ እንበል እንጂ፡፡ ሁሉን ነገር አዘገጃጅታ ከተወሰኑ ደቂቃዎች በፊት ስለነበር ወደዚህ የመጣችው ገብቶ ማቀራረብ ብቻ ነበር የሚጠበቅባት፡፡
ምግብ አቀረበች፡፡ ከበላ በኋላ ማስታጠቢያ አምጥታ አስታጠበችው፡፡ እጁን ታጥቦ ሲጨርስ ግን በጥፊ አቃጠላት፡፡
“እንዴት ነው ባለቤትሽ” በቀርከሃ ተደግፌ እንዳላየሁ ሆኜ ስትመጣ ጠየቅኋት፡፡
“ሲተኛልኝ መጣሁ”
“ፊትሽ ምነው በውሃ ተጨማልቋል? ደግሞ ቀልቷል፡፡”
“ከመተኛቱ በፊት ሊስመኝ በእጆቹ ጭምቅ አድርጐ ይዞ ሊለቀኝ አልፈለገም፡፡ አቤት የእጆቹ ልስላሴ! ምናልባትም በጉንጮቼ አጥንት የመዳፉን ለስላሳ ስጋ ወግቼ ይሆናል፡፡ አይ የኔ ነገር” አለች፡፡ ከልቧ ነው፡፡
3
ግን ለምን? ለምን ትደብቀኛለች? እኔ ገመናዋን በየመንገዱ እንደማልነሰንሰው ታውቃለች፡፡ ታዲያ ምን አስደበቃት? ምናልባት ባለቤቷን እንዳልጠላባት ይሆን?... ተመሳጠረብኝ፡፡ አልወደድኩትም ሚስጥርነቱን፡፡ በተለይ እናንተን እንግዶቼን ጠርቼ ይሄ ነገር ሲገጥመኝ የበለጠ አናደደኝ (አንባቢ ተጋባዥ እንግዳ አይደል? ምናልባት ህይወትን ራሷን የሚጋበዝ) ጉዳዩን እናንተ መከታተል ከጀመራችሁ በኋላ ለሦስተኛ ቀን መጥታ አሁንም በተመሳሳይ መልኩ ቀጣጠፈች፡፡ ቅጥፈት ልበለው ወይስ ምን? ለምታወራው ነገር ምንም ስሜት እንደሌለኝ እንደውም የእስከዛሬው ቅርርባችን አፈር ላይ እንደወደቀ ሥጋ የቆሸሸ መሆኑን በሚገልፅ አኳሁዋን ተመለከትኳት፡፡ አቀረቀረች፡፡ ገብቷታል፡፡ የባሰ አፋጠጥኳት - በአስተያየቴ፡፡
ታከብረኛለች፡፡ እንኳን እኔን ይህንን ከሰውነቱ ይልቅ አውሬነቱ የጠናበትን ባል ተብዬ እንኳ ታከብራለች እኮ፡፡ ሁኔታዬ ያልተለመደ ሆነባት፡፡ ምላሽዋም እንግዳ ነበር፡፡
“ይኸውልሽ…” የግራ ጡቷን እና የቀኝ እግር ጭኗን በአንዴ ገልጣ፡፡ የተጋደመ እባብ የሚመስሉ ጠባሳዎች ጣምራ ጣምራ ሆነው ተዘርግተዋል፡፡
“የቀድሞ ባለቤቴ ነው የተለተለኝ” ብላኝ በሃሳብ ተለየች፡ የፊቷ ገፅታ ጥቁር ደመና የመሰለ ነገር ለበሰ፡፡ ፊቷን የጋረደውን ሃዘን ጨምቃ በአይኖቹዋ በኩል እያንጠባጠበች የጀመረችልኝን ቀጠለች፡፡
“ከቀድሞ ባሌ የተለያየንበት የመጨረሻ ምክንያት ግን ይሄ አይደለም፡፡ ያን ቀን ገበያ ለመሄድ ፍራንክ ጠይቄው ነበር፡፡ ሰጠኝ፡፡ ከገበያ ስመለስ በእጄ የያዝኩትን 50 ሳንቲም በሚንቀጠቀጡ እጆቼ ዘረጋሁለት፡፡
“ቀሪውስ?” ጠየቀኝ
የማስታውሰው ምላሼ መንቀጥቀጤን በእጥፍ ድርብ ማሳደጌ እንደነበር ነው፡፡ ከገበያ መመለስ የሚገባኝ አንድ ብር ነበር፡፡ ገበያው ጉልበቱ ጨምሮ ያልታሰበ 50 ሳንቲም ነጥቆኛል፡፡ በአምስት ሳንቲም፣ በአስር ሳንቲም ያልጨመረ ነገር አልነበረም፡፡  የዘረጋሁለትን የሚንቀጠቀጥ እጄን እየጐተተ ወደ አንድ ክፍል ይዞኝ ገባ፡፡ በሩን ከዘጋ በኋላ የሚያደርገውን በማጣት ተቁነጠነጠ፡፡ መጨረሻ ላይ፣
“አፍሽን ክፈቺ” አለኝ
አላመነታሁም፡፡ አፌን ከፈትኩ፡፡ ቢላዋ በክፍሉ ውስጥ እንደሌለ እርግጠኛ ነበርኩ፡፡ እሱ የሚወደው ቢላዋ ነው፡፡ ግን በጉሮሮዬ ቁልቁል ሲደንደረደር አወቅሁ፡፡ አስታውሳለሁ፡፡
አንድ ድፍን ሃያ አምስት ሳንቲም፣ አንድ አስር ሳንቲም አና ሦስት አምስት ሳንቲሞች ነበር የመለስኩት፡፡ ነገሩ ገብቶኝ ላቆማቸው ብሞክር የጉሮሮዬ አጥንት ሊሰበር ሆነ፡፡ ዘለቁ፡፡ ታዲያ… ታዲያ… እስከ አሁን…” እያለች ወገቧን በታማሚነት ያዘች፡፡ አዘውትራ ወገቧን ስትይዝ ለምዶባት ይመስለኝ ነበር፡፡ ገፅታዋን ጋርዶት የቆየው ጥቁር ደመና ሙሉ ለሙሉ ፈነዳ፡፡
እየተንፈቀፈቀች ትታኝ ሄደች፡፡ ተከተልኳት፤ ምክንያቱም ሁኔታዋ አላማረኝም፡፡ ከውስጥ የፈነዳው ብሶቷ እንደ ደራሽ ውሃ እያንከባለለ የትም እንዳይጥላት ፈራሁ፣ ሰጋሁ፡፡
ወደ ቤቷ ገባች፡፡ ‘ቤቷ’ ‘ቤታቸው’ ልንል ተስማምተን የለ? በእንጥፍጣፊ ደቂቃ ቃላችንን አናጥፍም፡፡ እኔ እቤታቸው ገብቼ አላውቅም፡፡ ያ አውሬ ያለበት ቤት ምን ተብሎ ይገባል፡፡
ግን እሷን ምን ላድርጋት? …አደገኛ የዱር እንስሶችን ለመጐብኘት እንደተዘጋጀ ሰው ጥንቃቄ ባልተለየው ሁኔታ ወደ ውስጥ ዘለቅሁ፡፡
በመጨረሻ አገኘሁዋት፡፡ የአሁን ባልዋ እግር ስር በበደለኝነት ተደፍታለች፡፡ “አንተ እኮ ሩህሩህ ነህ፡፡ አንተ እኮ ገራገር ነህ፡፡ ከአንተ ጋር ስኖር ሰውነቴ ከመጠበስ ዳነ፡፡ አንተ እኮ.. አንተ እኮ… አንተን ማስከፋት የለብኝም…” ከአፍዋ የሚወጡትን ቃላት በራሱ ቀለም ሊከትብ፣ ሊያፀና የፈለገ ይመስላል - እንባዋ፡፡

 

 

Read 2584 times Last modified on Saturday, 09 June 2012 11:25