Saturday, 17 August 2019 13:56

ጎግል ከአመቱ ምርጥ 100 ድረገጾች ቀዳሚ ሆኗል

Written by 
Rate this item
(0 votes)


          በ2019 የፈረንጆች አመት በተጠቃሚዎች ቁጥርና በብዛት በመጎብኘት ቀዳሚነትን ከያዙ የአለማችን ምርጥ 100 ድረገጾች መካከል ጎግል፣ የአንደኛነት ደረጃን መያዙን ቴክኒውስ ዘግቧል፡፡ ሲሚላርዌብ የተሰኘው አለማቀፍ ተቋም ሰሞኑን ባወጣው የአመቱ ምርጥ 100 ድረገጾች ሪፖርት መሰረት፤ ጎግል በአመቱ፣ በየወሩ፣ በአማካይ 60.49 ቢሊዮን ጊዜ ተጎብኝቷል፡፡
በየወሩ በአማካይ 24.31 ቢሊዮን ጊዜ እንደተጎበኘ የተነገረለት ዩቲዩብ በበኩሉ፤ በአመቱ የምርጥ ድረገጾች ዝርዝር ውስጥ የሁለተኛነት ደረጃን ሲይዝ፣ ፌስቡክ 19.98 ቢሊዮን ጊዜ ያህል በመጎብኘት በሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
ባኢዱ የተሰኘው የቻይና ድረገጽ 9.77 ቢሊዮን፣ ዊኪፔዲያ 4.69 ቢሊዮን፣ ትዊተር 3.92 ቢሊዮን፣ ያሁ 3.74 ቢሊዮን፣ ፓርንሃብ 3.36 ቢሊዮን፣ ኢንስታግራም 3.21 ቢሊዮን፣ ኤክስቪዲዮስ 3.19 ቢሊዮን ጊዜያት በመጎብኘት እንደ ቅደም ተከተላቸው፣ ከአራተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ የያዙ ድረገጾች መሆናቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
በዝርዝሩ ውስጥ የተካተቱት 100 ድረገጾች ባለፈው ሰኔ ወር ብቻ በድምሩ 206 ቢሊዮን ጊዜ ያህል መጎብኘታቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ በአመቱ የአለማችን ምርጥ 100 ድረገጾች ዝርዝር ውስጥ ለመካተት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ቢያንስ ለ350 ሚሊዮን ጊዜያት ያህል በተጠቃሚዎች መጎብኘት እንዳለበት መነገሩን ገልጧል፡፡
ከአመቱ የአለማችን 100 ምርጥ ድረገጾች መካከል 60 ያህሉ የአሜሪካ ኩባንያዎች መሆናቸውን የጠቆመው ዘገባው፤15ቱ የቻይና ኩባንያዎች መሆናቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡

Read 2227 times