Monday, 19 August 2019 00:00

ያልተቋጨው የሕወሓት የቤት ሥራ

Written by  ደረጀ ይመር
Rate this item
(1 Vote)


           ማስፈንጠሪያ
ከዚህ ቀደም በዚሁ ጋዜጣ ላይ በወጣው መጣጥፌ፣ ኢሕአዴግ ምን ያህል እንደታመመና ድርጅቱ በቅርጽም ሆነ በይዘት መለወጥ ካልቻለ፣ ዳፋው ለሀገራችን የከፋ እንደሚሆን፣ አጭር ምልከታዬን ማኖሬ የሚታወስ ነው፡፡ በመጣጥፉ፣ ሕወሓት ይዞት ሊመጣ የሚችለው ዱብዳ፣ በተገቢው መልኩ አልተብራራም ነበር፡፡ የዚህ ጽሑፍ ነጥብ ማጠንጠኛ፣ ይህንን ርዕስ ጉዳይ መዳሰስ ይሆናል፡፡
ወቅታዊው ሁኔታ
የሕወሓት ጉዳይ አሁንም ፈር አልያዘም፡፡ አትንኩኝ የሹም ዶሮ ሆኗል፡፡ በትግራይ ያለውን ይዞታ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያጠናከረ፣የሉአላዊ ሀገር ቅርጽን እየተላበሰ መጥቷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ፣አጋር ይሆናሉ የሚላቸውን ኃይሎችን በማካተት፣ በአዲስ አሰላለፍ ለመምጣት፣ በብርቱ እየተጣደፈ ነው፡፡ ድርጅቱ ምናልባትም፤ በየክልሉ ያቆጠቆጡትን ጠርዘኛ ኃይሎች፣ እንደ መደላደል በመጠቀም፣ ራሱን እንደ ንሥር አድሶ ብቅ ለማለት እያደባ ነው፡፡ ከእነዚህ ቡድኖች ጋር ስትራቴጂካዊ ጫጉላ ውስጥ ለመግባት እየዳዳው እንደሆነ፣ አንዳንድ ምልክቶችን ማስተዋል ከጀመርን ሰንብተናል፡፡ ሰሞኑን ጽንፈኛ ፖለቲከኞች ወደ መቀሌ እግር አብዝተዋል፡፡ አብዛኞቻችን ሕወሓት ካለው ድርጅታዊ ተፈጥሮ ተነስተን፣ ለሴራ ትንታኔ መልህቃችንን ለመጣል መዳዳታችን አይቀርም፡፡ በርግጥም፤ በዚያ አካባቢ አንድ መመለስ የሚገባው ኹነኛ ጥያቄ እንዳለ እሙን ነው፡፡ ፓርቲው በማካቬላዊ ስልት የቆረበ ስለሆን፤ አላማውን ለማሳካት ከየትኞችም ኃይል ጋር ግንባር ከመፍጠር ወደ ኋላ አይልም፡፡
ሕወሓት ምን እያሰበ ነው?
የሕወሓት ልሳን በሆነው ‹‹ትግራይ ኦንላይን›› ላይ፣ ዶ/ር መኮንን ሐጎስ በተባሉ የድርጅቱ ቀንደኛ ደጋፊ የሰፈረው ረጅም ሐተታ፣ ምናልባትም ቀጣዩን ስትራቴጂ በቁንጽሉም ቢሆን የሚያሳየን ይመስለኛል:: ፓርቲው፣ ሊጠገን ከማይችለውና ከተፍረከረከው ኢሕአዴግ ጋር፣ አብሮ ጊዜ ማጥፋት እንደሌለበት ጸሐፊው በሐተታቸው አንጸባርቀዋል፡፡ በፍጥነት መውጪያ መንገዱን ማፈላለግ ይኖርበታል፤ ይላሉ:: ‹‹TPLF must take immediate action.This is the right time to break the EPRDF trap by writing a formal letter of withdrawal to the chairman, Abiy Ahmed Ali, with a copy to the chairperson of the House of Federation, the Ethiopian Defence Forces, and other stakeholders as neccessary.”
‹‹ሕወሓት አፋጣኝ እርምጃን መውሰድ አለበት:: ከኢሕአዴግ ወጥመድ  ለማምለጥ፣ ከጥምረቱ መውጣቱን ይፋ የሚያደርግ ደብዳቤ፣ ለድርጅቱ ሊቀ መንበር ዐቢይ አሕመድ አሊ  ማስገባት፤ አስፈላጊ ከሆነ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ ለመከላከያ ሚኒስቴርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በግልባጭ እንዲያወቁት ማድረግ ይኖርበታል፡፡” ይላል፤ ሃተታው፡፡
በርግጥም፣ ይህን አይነት መንፈስ የተላበሰ፣ ይፋ የወጣ ኦፌሴላዊ አቋም እስካሁን ከድርጅቱ በቀጥታ መታዘብ ባንችልም፤ ከዚህ ቀደም ባለን ተሞክሮ፣ እንደ ‹‹ትግራይ ኦንላይን›› እና ‹‹አይጋ ፎረም›› ባሉ ድረገጾች፣ በአብዛኛው የሚንጸባረቁት ሐሳቦች፣ ድርጅቱ በዲጂታሉ ዓለም እንደ ዋንኛ የትግል ስልት የሚጠቀምባቸው ናቸው፡፡ ጸሐፊው፤ የኢሕአዴግ መፍረክረክ ለሕወሓት እንደ ትልቅ የምሥራች መወሰድ እንዳለበት ጨምረው ይገልጻሉ:: ‹‹TPLF has a huge opportunity now to create a brand new startegy for Ethiopian’s revolutionary democartic developmental state (RDDS) with the willing Nations, Nationalities, and Peoples of Ethiopia.“
“ሕወሓት፤ ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን በአጋርነት በማሰለፍ፣ የኢትዮጵያ አብዮታዊ ዴሞክራቲክ ልማታዊ መንግሥት (RDDS) የሚል አዲስ ስትራቴጂ በመፍጠር፣ በአዲስ አሰላለፍ ብቅ ለማለት የሚያስችል ትልቅ አጋጣሚ በእጁ ገብቷል፡፡”
የሀገራችንን ፖለቲካ በየጊዜው በመተንተን የሚታወቀው ሬኒ ሊፍሮኽ፣ በታዋቂው ‹‹ኦፕን ዴሞክራሲ›› ድረ-ገጽ ላይ ሕወሓትን አስመልክቶ በቅርቡ ያስነበበው መጣጥፍ፣ የመኮንን ሐሳብ በእጅጉ የሚያጠናክር ነው፡፡ ሊፍሮኽ እንደሚለው፤ ፓርቲው ለህልውናው ሲል፣ የትግራይን ሉአላዊነትን ተገን ማድረጉ የሚጠበቅ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ዓላማውን ለማሳካት ከሚረዱት መላዎች መካከል፣ የዘውግ ፌዴራሊዝሙን አስመልክቶ የያዘው የሞት ሽረት አቋም ነው፡፡ ለዚህም ተፈጻሚነት፣የፌዴራላዊውን አወቃቀር ህያውነት ለማስረገጥ እንደ ልሳን በሚጠቀምባቸው የሚዲያ አውታሮቹ ሳያሰልስ እየወተወተ ነው፡፡
‹‹TPLF has re-engaged nationally to lead the construction of the hard ethnic federalism pole in order to ensure its top priority፡ a strong autonomous Tigray. Its experience, organization and clarity of vision make it the only organization that can perform this task.Tigrian Websites have called for this decsive task.”  
ግርድፍ ትርጉሙ፤ “ሕወሓት ጠንካራና ሉኣላዊ የሆነችውን ትግራይ እውን ለማድረግ፤ አክራሪ የዘውግ ፌዴራሊዝም አቀንቃኞችን አቀናጅቶ ለመምራት ዳግም ሊነሳሳ ይችላል፡፡ ድርጅቱ በዚህ ረገድ ያለው የካበተ ልምድ፤ ይህንን አላማውን ለማሳካት እንደሚያስችለው ይታመናል:: የትግራዋያን ድረገጽ የጉዳዩን አስፈላጊነት ለወራት ሲወተውቱ ቆይተዋል፡፡” እንደ ማለት ነው፡፡
ሕወሓት የተደራጀ የብሔር ድርጅት ስለሆነ፤ ሌሎች አክራሪ የዘውግ-ብሔርተኞች እንደ መከታ ቢያዩት የሚገርም አይሆንም፡፡ በፖለቲካ አቋሙም ሆነ አደረጃጀት፣ ከእነዚህ ኃይሎች ጋር በአንድ ማህጸን ነው የተኛው፡፡ ልክ እንደ ጽንፈኛ የብሔር ድርጅቶች፣ በሕገ መንግሥቱና በፌዴራላዊው ሥርዓቱ አይደራደርም፡፡ ለዚህም ነው፣ድርጅቱ በደቡብ ክልል የሚነሱትን የክልልነት ጥያቄዎች፣ ከየትኛውም ኃይል በላቀ ደረጃ በጽኑ በመደገፍ፣ ለፖለቲካ ትርፍ ሲታትር የሚስተዋለው፡፡ በደቡብ ክልል የሚከፈተው የመርገም ሳጥን /ፓንዶራ ቦክስ/፤ ሀገሪቱን ወደ ሌላ ትርምስ ውስጥ ቢከታት ተጠቃሚ ሊሆን የሚችለው ይኸው ድርጅት ነው፡፡ በሚፈጠረው ቀውስ ምናልባትም፣ ሕወሓት መልሶ ወደ አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት እንዲያማትር ድፍረቱን የሚሰጠው ይሆናል፡፡ ስለዚህ በፌዴራል ሥርዓቱና በሕገ መንግሥቱ ዙሪያ ያለው አቋም በአለት መሠረት ላይ የቆመ ነው፡፡
ኦሮ-ማራ ላይ መዝመት
በቅርቡ ፌዴራል ሥርዓቱን አስመልክቶ፣ በመቀሌ በተዘጋጀው የውይይት መድረክ የተገኙት ፕሮፌሰር እዝቄል ጋቢሳ፤ “ኦሮ-ማራ ታክቲካል እንጂ ስትራቴጂክ አይደለም፤ ኦሮ-ማራ አምቦ ላይ ሞቷል:: “ማለታቸውን ተከትሎ የሕወሓት አክቲቪስቶች አቅላቸውን ስተው ሰንብተዋል፡፡ እውነት ግን የሁለቱ ታላላቅ ሕዝቦች ውህደት፣ በዘመንና በመሪዎች ችሮታ የሚወሰን ነውን?
ታሪክን በጥራዝ ነጠቅ እሳቤ ከቃረምነው፣የዚህ አይነቱ ሸውራራ ፕሮፓጋንዳ ሰላባ መሆናችን የማይቀር ነው፡፡ የሀገራችንን የታሪክ ጉልላት መለስ ብለን ስንመረምር፣ የአማራና የኦሮሞ ሕዝቦች፣ እንደ መዳፍ ጣት የማይነጣጠል ኅላዌን ያልተላበሱበትን አጋጣሚ ፈጽሞ ማግኘት አንችልም፡፡ ሕዳጣኑ ድርጅት፤ ሁለቱን ታላላቅ ሕዝቦች፣ በእሳትና ጭድ፤ በጨቋኝና በተጨቋኝ ፈርጅ በመመደብ፣ ጥቂት ዘመናትን በበላይነት ማዝገም ቢችልም፤ ማሳረጊያው  ሽንፈት ከመሆን አላመለጠም፡፡ “ጣና ኬኛ” እና “የኦሮሞ ደም ደሜ ነው” የሚሉት የዘውግ ዘለል አዲስ የልቦና ውቅሮች፤ ለተቀበረው የሸር ፖለቲካ ማርከሻ ሆነው አልፈዋል፡፡
የሕወሓት አክቲቪስቶች፣ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽእኖዋቸውን በመጠቀም፣ የኦሮ-ማራን ሕልፈት፣ በአልሞት ባይ ተጋዳይነት ሲለፍፉ እያስተዋልን ነው፡፡ ይህንን አጀንዳ ተቀብለው የሚያስተጋቡት ሌሎች የዘውጌ ብሔርተኞችም ጭምር መሆናቸውን ስንመለከት ደግሞ፣ የጉዳዩ ዙሪያ ጥምጥም በደንብ ይገባናል፡፡ እነዚህ ኃይሎች በግብር ቢለያዩም፣ በአላማ ከሕወሓት ጋር ኩታገጠም ናቸው፡፡ የተረኝነት የፖለቲካ ዝንባሌ እንጂ ለውጥ የለም፤ የሚለው ፕሮፓጋንዳ በሁሉም አክራሪ የዘውጌ-ብሔርተኞች ዘንድ የሚስተጋባ ነው፡፡ የአዴፓና የኦዴፓ ቁርቋሶን ለማባባስ፣ የጆሴፍ ጎብልስ፣ ‹‹ውሸት ሲደጋገም እውነታ ይሆናል›› የሚለው አስተምህሮት፤ ከልቦናቸው ያደረ ኃይሎች፤ ኦሮ-ማራን ሳይፈጥሩት፣ ሊገድሉት እየተንደረደሩ ነው:: ኦሮ-ማራ ትርክት የሁለቱን ሕዝቦች ትስስር ያደሰ እንጂ የፈጠረ አይደለም፡፡ ሁለቱ ሕዝቦች የተጋመዱበት እትብት፣ ከመሪዎች ዲስኩር፣ ከፖለቲከኞች ሴራ በላይ የረቀቀ ምስጢር አለው፡፡  
ትግራይን እንደ ሶማሌላንድ (የመጨረሻው ምላጭ)
ሕወሓት ከሌሎች የኢሕአዴግ እህት ድርጀቶች የተሻለ ቁመና በክልሉ ላይ እንዳለው ይታወቃል:: ለዚህም እንደ ምክንያት ከሚወሰዱት ነጥቦች መካከል አንዱ ሊሆን የሚችለው፣ አዴፓ እና ኦዴፓ ከሚያስተዳደሩት ክልልና ሕዝብ ጋር ለንጽጽር  የማይበቃ፣ ጠባብ መልክአ ምድር ውስጥ አገዛዙ ስላልነበረ ነው፡፡ በትግራይ ክልል፣ ይኽ ነው የሚባል ተጽእኖ ማሳረፍ የሚችል ሕዝባዊ ንቅናቄም ሆነ የፖለቲካ ድርጅት የለም፡፡ ያሉትም ቢሆን የፓርቲውን አቅም የሚፈትኑ አይደሉም፡፡
ሕወሓት ቀስ በቀስ ትግራይን፣ እንደ ሶማሌላንድ፣ የአለማአቀፉ ማኅበረሰብ እውቅና ያልሰጣት ሉአላዊ ሀገር እያደረጋት ነው፡፡ ባስ ሲል፣ ከዚህም ገፍቶ ሊሄድ ይችላል፡፡ ከማእከላዊ መንግሥት ጋር ያለው ቁርቋሶ አፋፍ ከደረሰ፣ የመጨረሻ ምላጩን ከመሳብ ወደ ኋላ አይልም፡፡ ይኸውም አንቀጽ 39ን ማወጅ ይሆናል፡፡ ሕገ መንግሥቱን ከማሻሻል ይልቅ አንቀጽ 39ን ማወጅ ቀላል ሥራ እንደሚጠይቅ ሰነዱን መመልከት በቂ ነው፡፡ ድርጅቱ ይህን ያህል እንኳን ድፍረት ቢያጣ፣ ያሻውን ሕግ እያወጣ የሚሽርባት፣ ጠንካራ የውስጥ ሉአላዊ ሥልጣን ያላትን ትግራይ፣ የሙጢኝ ብሎ መቀጠሉ አይቀርም፡፡
የግርጌ ማስታወሻ
የሕወሓት ጉዳይ ውሉ እንደጠፋ ነው:: ድርጅቱ የለውጡ አጋር ሊሆን የሚችልበት ሦስት አማራጮች ይኖራሉ፡፡ የመጀመሪያው፣ ልክ እንደ ቲም-ለማ ወይም ቲም-ገዱ፣ ከውስጥ ሰብሮ የሚወጣ ኃይል እስኪፈጠር መጠበቅ ፤ይኽ እንኳን ተስፍኝነት የተጫነው ምኞት ነው፡፡ ሌላው፣ ብዙ ዋጋ የሚያስከፍልና ሀገሪቱን ወዳልታወቀ ቀውስ ውስጥ የሚከታትን የኃይል አማራጭ መጠቀም ነው:: ሦስተኛው፣ የአስተዳደሩን አቅም የሚፈታተን፣ የኢኮኖሚ ማነቆዎችን በመፍጠር፣ ሕወሓት ተገድዶ፣ የለውጡን ካምፕ እንዲቀላቀል ማድረግ ይሆናል፡፡ በእነዚህ የመፍትሄ ማእቀፎች፣ ሕወሓትን የለውጡ ተጣማሪ ማድረግ ካልተቻለ፣ በሕወሓት ምትክ ከአጋር ፓርቲዎች መካከል ተራማጆቹን ብቻ በማካተት፣ የተጀመረውን የሽግግር ሂደት ስኬታማ በሆነ ሁኔታ ማስቀጠል ምርጫ የሌለው አማራጭ ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ከላይ በቀረበው ጽሁፍ ውስጥ የተንጸባረቀው ሃሳብ፣. ጸሃፊውን ብቻ እንደሚወክል እንገልጻለን፡፡


Read 7070 times