Saturday, 17 August 2019 13:41

እቴጌ መነን ሊበን - የዘመነ መሳፍንት “አፍሪካዊቷ ካተሪን”

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(3 votes)

 ብዙ ጊዜ የሚገርመኝ አንድ ጥያቄ አለ፡፡ ጥያቄው፤ “በሀገራችን ሴት የታሪክ ጸሐፊ ለምን የለም?” የሚል ነው፡፡ የዚህን ጥያቄ መልስ በተለይ ሴቶች ብትወያዩበት መልካም ነው፡፡ የሀገራችን ሴቶች ከጥንት ጀምሮ በሀገራችን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያላቸው ተሳትፎ የላቀ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ይህ የሀገራችን ሴቶች ታሪክ በአግባቡ አልተዘገበም፡፡ ቢዘገብም በወንዶች ታሪክ ውስጥ ጠቀስ ተደርጎ የሚታለፍ እንጂ ራሱን ችሎ እንዲጻፍ አልተደረገም፡፡ አቅም በፈቀደ ይህ የተዳፈነ ግማሽ ታሪካችንን ለማስታወስና የታሪክ ጸሐፊዎችን ለማነቃቃት በማሰብ ነው ይቺን ጽሁፍ ያዘጋጀሁት፡፡ ወደፊት “ዮዲት ጉዲት”ን ጨምሮ የሌሎች ሴቶችን ታሪክ አቀርባለሁ፡፡ የዛሬው መጣጥፌ በዘመነ መሳፍንት በነበረች አንዲት ኢትዮጵያዊት ታሪክ ዙሪያ የሚያጠነጥን እንዲሆን ፈቀድኩ፡፡ የማቀርብላችሁ ባለ ታሪክ እቴጌ መነን ሊበን አመዴ ትባላለች፡፡ እቴጌዪቱ በዘመነ መሳፍን የነበሩት የትንሹ ራስ አሊ እናት፣ የአፄ ዮሐንስ 3ኛ ባለቤት ነበረች፡፡
አንዳንድ ምሁራን አሁን ያለንበትን ዘመን ከዘመነ መሳፍንት ጋር ያመሳስሉታል፡፡ የሚያመሳስሉት በአሁኑ ወቅት ጠንካራ ማዕከላዊ መንግስት የለም ለማለት ነው:: በዚህ አልስማማም፡፡ ዘመነ መሳፍንት የሚባለው ከ1750ዎቹ እስከ 1850ዎቹ ዓ.ም ድረስ ያለው ጊዜ ነው በሚለው በርካታ የታሪክ ምሁራን ይስማማሉ፡፡ በዚህ ከ80 -100 ዓመታት ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግስት አልነበረም፡፡ በየአካባቢው ንጉሶች ነበሩ፡፡ የሁሉም የበላይ የሆነ፣ ሁሉንም ንጉሶች አስተባብሮ የሚመራ ንጉሰ ነገሥት ግን አልነበረም፡፡
መነን ሊበን አመዴ የተወለደቺው በደቡብ ወሎ ሲሆን፤ የታላቁ የወሎ ማመዶ ቤተሰብ ኢማም፣ የወረ ሂመኖው ባላባት የሊበን አመዴ ልጅ ናት፡፡ ከወረ-ሼህ ሙስሊም ቤተሰብ የተገኘች በመሆኗ የመጀመሪያ ስሟ “ሐሊማ” ሊበን ይባል ነበር፡፡መነን የመጀመሪያ ባሏ የሆነውን የየጁውን አሉላ ጉግሳን ማግባቷ ይነገራል፡፡ ራስ አሊ 2ኛን የወለደቺው ከመጀመሪያ ባሏ ከአሉላ ነው፡፡ አሊን ከወለደች በኋላ በየጁ የወረ-ሼህ መሪ ትእዛዝ አሉላን ፈታችና ወሌ የሚባል ሰው እንድታገባ ተደረገች፡፡ ክርስትና ተነስታ “መነን” ተባለች፡፡
አንዳንድ ጸሀፊዎች እቴጌ መነን “ኃይለኛ፣ ብርቱና ጨካኝ ሴት ነበረች” ይሏታል፡፡ “በሀገራችን ከእርሷ ጋር ይወዳደራሉ የሚባሉ ሴቶች ተፈጥረው ነበር ቢባል በጣም ጥቂት ናቸው” በማለትም ያክሉበታል፡፡ የእቴጌ መነንን ኃይለኛነት በተመለከተ ደራሲ አቤ ጉበኛ እንዲህ ይላል፤ “ወንድ ለመሆን የቀራቸው የወንድነት ምልክት ብቻ ነው” በማለት ይገልጻታል፡፡
የቅርብ ጊዜዎቹ ካልሆኑ በስተቀር ቀደምት ነገስታት በተለይ ደግሞ ንግስቶች፣ እቴጌዎችና ልእልቶች ከስማቸው በስተቀር ፎቶ ግራፋቸው በታሪክ ሰነዶች ላይ አይገኝም:: አርኖልድ ዲ. አባዲ የተባለ ፈረንሳዊ ጸሐፊ የመነንን ከፊል ገጽታ በጽሁፍ አስፍሯል፡፡ መነንን “ፀጉሯ በጥንቃቄ የተጠቀለለ ነው፡፡ በሻሽ የተሸፈነው ሰፊው ግንባሯ የምትሽኮረመም ያስመስላታል፡፡ የሚያንፀባርቁ ትልልቅ ውብ ዓይኖች አሏት፡፡ ብልህና ጣፋጭነቷን ይናገራሉ፡፡ ስትቆጣ ግን ውብ ገጽታዋ ይቀየራል፣ ደስ የማይለው የአፏ ገጽታ ጎልቶ ይወጣል” በማለት ገልጿታልአርኖልድ፡፡
የ13 ዓመት ዕድሜ የነበረው የመነን ልጅ አሊ አሉላ ስልጣነ መንበሩን የተረከበው ከአጎቱ ነው፡፡ አሊ ስልጣን እንደጨበጠ አባቱ አሉላ ሞተ፡፡ ስለሆነም አሊን በመንግስት ጉዳዮች ላይ ምክርና ድጋፍ የሚሰጥ ምክር ቤት ተቋቋመ፡፡ ይሁን እንጂ እናቱ ወ/ሮ መነን ሊበን “ምክርና ድጋፍ የሚሰጥ ምክር ቤት አያስፈልግም፡፡ የሞግዚትነት ኃላፊነቱ ለኔ ለእናቱ ሊሰጠኝ ይገባል” የሚል ሙግት አቀረበች፡፡ ከብዙ ንትርክና ጭቅጭቅ በኋላ ሞግዚትነቱን ራሷ ወሰደች፡፡
በዚህም መሰረት እቴጌ መነን ከምንትዋብ በኋላ በጎንደር ቤተ-መንግስት የአድራጊ ፈጣሪነት ሚናን ተቀዳጀች፡፡ በዚያ ወቅት በጎንደር ቤተ መንግስት ዙፋን ላይ በመውጣት ሂደት ላይ የነበሩት የየጁ ኦሮሞዎች ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ ከየጁ ኦሮሞዎች ውስጥ በጎንደር ቤተ መንግስት ንጉሰ ነገስት ሆኖ ዙፋን የጫነ ጠንካራ የመንግስት አስተዳደር አልነበረም፡፡ ይህንን የተገነዘበቺው መነን ምን ማድረግ እንዳለባት ማሰላሰል ጀመረች፡፡ ራሷን ብታነግስ በዚያ ዘመን በነበረው ወግ አጥባቂ ሁኔታ “የሴት ንጉስ”ሆና ተቀባይነት እንደማታገኝ ተረዳች፡፡ ብልኋ መነን አንድ ዘዴ አውጠነጠነች፡፡ ይኸውም ባሏን ንጉስ አድርጋ ከዚያ ራሷን ንግስት (እቴጌ) በማድረግ ቤተ መንግስቱን ለመቆጣጠር ቆርጣ ተነሳች፡፡ይህንን ለማድረግ በቅድሚያ በዚያ ወቅት ንጉስ የነበሩትን አፄ ሳህለ ድንግልን በመፈንቅለ መንግስት ከቤተ መንግስትአስወጥታ በርሳቸው ምትክ የአፄ ተክለ ጊዮርጊስ ልጅ የነበሩትን ባሏን“አፄ ዮሐንስ 3ኛ” አሰኝተታ እንዲነግስ አደገች፡፡ ከዚህ ንግስ በኋላ ወ/ሮ መነን መባሏ ቀርቶ እቴጌ መነን እየተባለች መጠራቷን ታሪከ ነገስት መዝግቦታል፡፡
የእቴጌ መነን እና የካሳ ኃይሉ ግብግብ
የመነን ግዛት በሆነው በቋራ አካባቢ ካሳ ኃይሉ ወ/ጊዮርጊስ (በኋላ አፄ ቴዎድሮስ) የተባለ ሰው ነበር፡፡ ካሳ አጎቱ ደጃች ክንፉ ጋር ነበር ያደገው፡፡ አጎቱ ሲሞቱ የደጃዝማች ቢተዋ ወታደር ሆነ፡፡ ደጃዝማች ቢተዋ ኃላፊነቱን በአግባቡ ባለመወጣቱ መነን ጠራችና አሰረቺው፡፡ የደጃዝማች ቢተዋ ጭፍራ የነበረው ካሳ ኃይሉ አምልጦ ወደ ቋራ ሄደና ሸፈተ… የካሳ ሽፍታነት እየገነነ ሲመጣ የእቴጌ መነን ግዛት ወደሆነው ወህኒ አምባ ሄዶ ዘረፋ ያካሂድ ጀመር… እቴጌ መነን ካሳን “ይሄ ሰው ክፉ ቆለኛ ነው” በማለት ደጋግማ ትናገር ነበር፡፡ የወህኒ አምባን መዘረፍ ስትሰማ ደግሞ በጣም ተናደደች… ካሳ ኃይሉ ተራ ሽፍታ ቢሆንም እቴጌ የካሳ አካሄድ አደገኛ መሆኑ ገብቷታል፡፡ አበው “ሳይርቅ በቅርቡ፣ ሳይደርቅ በርጥቡ” እንዲሉ ይህንን ሽፍታ በአጭሩ መቅጨት እንዳለባት ማውጠንጠን ጀመረች:: በመጨረሻም ካሳን የገባበት ገብቶ የሚይዝ ጦር ካሳ ይገኝበታል ወደተባለው ስፍራ ላከች… መነን የላከቺው ጦር የካሳን ጦር ተሰልፎ ባየ ጊዜ ሁኔታውን አመዛዝኖ ሳይዋጋ ተመለሰ፡፡
የጦሩ መመለስ እቴጌን ይበልጥ አበሳጫት፡፡ እናም ሌላ ዘዴ ማሰላሰል ጀመረች፡፡ እቴጌ መነን የካሳን መበርታትና የህዝቡን ከካሳ ጋር ማበር ባወቀች ጊዜ አንድ ሃሳብ መጣላት፡፡ ከጦርነት ይልቅ በወዳጅነት መያዙ የሚጠቅም መሆኑን በማመኗ ካሳ ጋር ታረቀች፡፡ እቴጌ ለጊዜው ከካሳ ጋር ብትታረቅም ካሳን ይበልጥ ማዘናጋት አስፈላጊ መሆኑን በማመኗ ለካሳ ተጨማሪ የወዳጅነት ተግባር ለመፈጸም አሰበች፡፡ በዚህም መሰረት ካሳ ቋራን በምስለኔነት እንዲያስተዳድር ሾመቺው፡፡
ካሳም የተሰጠውን ግዛት እስከ መተማ ድረስ በመሄድ ድንበር ተሻግረው የሚያስቸግሩትን ሽፍቶች ወግቶ በማሸነፍ በርካታ ምርኮ ሰበሰበ፡፡ እቴጌ መነን፤ ካሳ ከውጪ ወራሪዎች ጋር ያደረገውን ጦርነትና አሸንፎ የሰበሰበውን ምርኮ ስታይ ከካሳ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር እንዳለባት ተገነዘበች፡፡ በዚህም መሰረት ካሳ ጋር የፖለቲካ ጋብቻ መመስረት እንደሚገባ ወሰነች፡፡ ይሁን እንጂ ካሳ ባለ ትዳር በመሆኑ ይህንን ማድረግ አስቸጋሪ ነበር፡፡
ሲያስፈልግ ብልሃትን ሲያሻት ጉልበትን እንደተጨባጭ ሁኔታው እያፈራረቀች ትጠቀም የነበረቺው እቴጌ መነን ያሰበቺውን ከማድረግ የሚመልሳት ኃይል አልነበረምና ካሳ ሚስቱን ፈትቶ እሷ ያዘጋጀችለትን ሴት እንዲያገባ በማድረግ ቀንደኛ ጠላቷን በሰላምና በፍቅር ለማንበርከክ ወሰነች፡፡ እናም፤ “ሚስትህን ፍታና የኔን ልጅ አግባ” የሚል ትእዛዝ ቀመስ መልእክት ላከችበት፡፡ ካሳ ኃይሉም እቴጌ መነን የላከችበትን “ቀጭን ትእዛዝ” ተቀብሎ ሚስቱን ፈትቶ የራስ አሊን ልጅ፣ ተዋበች አሊን አገባ፡፡
ከጋብቻውና ከሹመቱ በኋላ ካሳ ከህዝብ የሰበሰውን ግብር ይዞ ወደ ጎንደር ቤተመንግስት ሄደና አስረክቦ እዚያው ከረመ፡፡ በመጨረሻም ወደ ግዛቱ ሊመለስ ሲል “ካሳ ምስለኔ ነው፡፡ ቋራ ግን የደጃዝማች አገር ነው፡፡ ከእሱ የበላይ ሆኖ የሚያስተዳድር አንድ ባለ ነጋሪት ደጃዝማች ይዞ መሄድ አለበትና ለካሳ ንገሩት” ብላ ላከችበት እቴጌ መነን፡፡የፖለቲካ ጋብቻና ትስስር ቢፈጠርም፣ ሹመት ቢሰጥም፣ ግብር ቢገብርም፣ የመነን እና የካሳ ኃይሉ ግንኙነት የሁለት ጉልበተኞች ቁርኝት ስለነበርና ሁለቱም የየራሳቸውን ፍላጎት ለማሳካት የሚመኙ በመሆኑ ወዳጅነታቸው ብዙም ርቀት መሄድ አልቻለም፡፡ካሳ በበላዩ አለቃ ይሾማል በመባሉ ተናደደ፡፡ ይሁን እንጂ ቅሬታ ቢያሳይ እቴጌ ወደ ዘብጥያ እንደምታወርደው ስለገባው እሺ ብሎ ሃሳቡን ከተቀበለ በኋላ ራሱ ቀጥታ ወደ ቤተ መንግስት እቴጌ ዘንድ በመሄድ “የበላይ ሆኖ የሚመለከት ሹም ስላደረጉልኝ አመሰግናለሁ፡፡ በዚህም ተደስቻለሁ፡፡ ለእኔም ቢሆን ታዛቢ ሆኖ ሁሉን ነገር የሚያይልኝ በማግኘቴ እቴጌን ከልብ አመሰግናለሁ” ብሎ እጅ ነሳ፡፡ ወደ አገሩም ሄደ…
ከካሳ ጋር የተደረገው የጋብቻ ትስስር የእኩያዎች ጋብቻ ባለመሆኑ እቴጌ መነን ካሳን ይንቁት ነበር፡፡ ሲፈልጉ ግዛቱ እየተቀነሰ፣ ሲያሻቸው ፍርዱ እየተገለበጠ በህዝብ ዘንድ የተናቀ እንዲሆን አድርገውት ያን ሁሉ ችሎ አሳለፈ:: በመጨረሻ ላይ ወደ ጠረፍ ሄዶ እንዲዋጋ አዘዘቺው እቴጌ፡፡ ይህንን ያደረገቺው በጦርነቱ እንዲሞት በማሰብ ነበር፡፡ ካሳ አላወላወለም፡፡ ምርጥ ወታደሮቹን ይዞ ወደ መተማ ሄደ:: እዚያ አካባቢ የነበረውን የድንበር ማስከበር ስራ ሰርቶ፣ ተዋግቶ፣ ድል አድርጎ ተመለሰ፡፡ ያገኘውን ምርኮ ከፊሉን ለእቴጌ መነን ይዞ ሄዶ አስረከበ፡፡
እቴጌ መነን በቀረበላት ስጦታ ብትደሰትም የካሳ በህይወት መመለስ አላስደሰታትም ነበር፡፡ ካሳ በጠረፍ አካባቢ በነበረ ውጊያ ቆስሎ ስለ ነበር ለቁስል መጠገኛየሚሆን ስንቅና ኮሶ ይዞት ስለበር ለዚያ የሚሆን ፍሪዳ እንዲልኩለት ለንጉሱ ለዮሐንስ 3ኛ፣ ለአማቱ ለራስ አሊና ለእቴጌ መነን ላከባቸው፡፡በዚሁ መሰረት እቴጌ መነን “አንድ ብልት ሥጋ፣ 30 እንጀራና አንድ ገንቦ ጠጅ ይላክለት” ብላ አዘዘች፡፡ ይህንን ትእዛዝ የሰሙ ሰዎች “ምነው እሜቴ የካሳን ጠባይ ሁላችንም እናውቀዋለን፡፡ ኩሩ ነው፡፡ ፍሪዳ አላጣን ምናለ ሲሆን አንድ ፍሪዳ ያለበለዚያ አንድ ሙክት ቢላክለት አይሻልም?” አሏት፡፡ እቴጌም “ለፍየል ጠባቂ ቆለኛ አንድ ብልት አንሶት ነው?” የሚል መልስ ሰጠች፡፡
እቴጌ “ለፍየል ጠባቂ ቆለኛ አንድ ብልት አንሶት ነው?” ማለቷን አንድ ወዳጁ ለካሣ ነገረው፡፡ ካሳ ግን የሆዱን በሆዱ አድርጎ ስጦታውን አመስግኖ ተቀበለ፡፡የካሳ ባለቤት ተዋበች አሊ ወደ ካሳ ዘንድ በመቅረብ “ሲሆን በቤተ መንግስቱ አዳራሽ ፍሪዳው ታርዶ፣ ማቶቱ በጠጅ ርሶ፤ ስጋው በመልከኛ፣ ጠጁ በገንቦኛ በተላከልን ነበር፡፡ እንደምን ብንናቅ ነው አንድ ብልት ስጋ የተላከልን? ጀግና ሰው እወዳለሁ፣ ፈሪ ወንድ ግን እንቃለሁ፡፡ ከፈሪ ሰው ጋር አብሬ መኖር አልፈልግም” አለቺው፡፡ ካሳ ከቀናት በኋላ እንደገና ሸፈተ…
እቴጌ መነን የካሳን መሸፈት እንደሰማች ካሳ ሳይደራጅና ኃይል ሳያበጅ ለመምታት አሰበች፡፡ እናም፤ ካሳ በሸፈተ በሳምንቱ ካሳን የሚመታ ጦር ላከች፡፡ ካሳም ጦሩን ሰበሰበና “… ጦርነት የምገጥምበት ጊዜው ተቃርቧል:: ሆኖም ግን እኔ የመለከትና የእምቢልታ ድምፅ ሳላሰማህ እንዳትንቀሳቀስ…” ብሎ ድንኳኑ ውስጥ ገብቶ ተኛ፡፡ካሳ ትንሽ እንዳሸለበ የእቴጌ ጦር መቃረቡን ያየቺው ባለቤቱ ተዋበች አሊ ወደ ካሳ ድንኳን ገብታ ቀሰቀሰቺውና “ጦሩ መጥቶልሃል፡፡ ተነስ ታጠቅ” አለቺው፡፡ ከዚህ ጊዜ በኋላ የካሳ የፈረስ ስም “አባ ታጠቅ” ተባለ፡፡ ካሳም ታጥቆ ወጣና “በለው እንግዲህ” ብሎ አዘዘ፡፡ ውጊያው ቀጠለ፡፡ የካሳ ጦር አሸነፈ፡፡ ብዙ ሰው ማረከ፡፡
እቴጌ መነን የተላከው ጦሯ ተሸንፎ መበታተኑን ስትሰማ እንደገና ሌላ ጦር ላከች፡፡ በዚህ ወቅት የካሳ ጦር ተጠናክሮ ስለነበር ይሄኛውንም የእቴጌን ጦር በቀላሉ አሸንፎ በታተነው፡፡ መነን በንዴት ጦፈች፡፡ ባለቤቷን አፄ ዮሐንስ 3ኛን አስከትላ፣ ራሷ የጦር መሪ ሆና 20 ሺህ የሚሆን ጦር ይዛ ጉዞ ጀመረች፡፡በጉዞ ላይ እያለቺም “ይሄ ቆለኛ! ፍዬል ጠባቂ! ወዴት ይሆን ያለው? … ይሄ ቆለኛ ወደ እናቱ ሆድ ተመልሶ እንዳይገባ እንኳ ያቺ ኮሶ ሻጭ እናቱ ሙታለች… ወዴት እንደሚገባ እናያለን!” እያለች እየፎከረች ሄደች፡፡ የካሳ ጦር ካለበት ስፍራ ስትደርስም የካሳ ሰራዊት ለጦርነት ተሰልፎ ጠበቃት፡፡ መነን የካሳን ጦር ተሰልፎ ስታይ “አያፍርም እኮ ይሄ ቆለኛ! ከእኔ ጋር ሊዋጋ ተሰልፏል!?” አለች በንቀትና በመገረም፡፡ የመነን የጦር ዝግጅትና ስድብ ካሳ ጆሮ ደርሷል፡፡ቋረኛው ካሳ በበኩሉ ወላጆቹን እያነሳች (የኮሶ ሻጭ ልጅ እያለች) ስትሰድበው በነበረቺው በእቴጌ መነን ቂም ይዞ “ቆይማ እኔ የመይሳው ልጅ ይህቺን ጎፍጣጣ ባልቴት ዋጋዋን ባልሰጣት እግዜር አልፈጠረኝም! ብቻ ትምጣና ትሞክረኝ…” እያለ የጦርነቱን መጀመር በፉከራ ይጠባበቅ ነበር፡፡
ከሽፍታው ካሳ ኃይሉ ጦር ይልቅ የእቴጌ መነን ጦር በብዛት ይበልጥ ነበር፡፡ ደንቢያ ሜዳ በመሆኑ አብዛኛው የእቴጌ ሰራዊት ፈረሰኛ ነው፡፡ ጋሻና ጦር ከያዘው እግረኛ ይልቅ ጠመንጃ የያዘው ቁጥሩ ብዙ ነው፡፡ ይህም የሚያሳየው እቴጌ መነን የምትመራውን ሰራዊት በትጥቅም፣ በስንቅም፣ በአደረጃጀትም አንድ ሰራዊት ሊያሟላው የሚገባውን ሁኔታ እንዲያሟላ ማድረጓን ሲሆን፤ከዚህም ዝግጅት መነን እንደ ጦር መሪ ሠራዊትን የማደራጀት አቅምና ችሎታ የነበራት መሆኑን ለመገንዘብ ይቻላል፡፡ … የእቴጌን ጦር እየተመመ መምጣት የተመለከተው ካሳ ኃይሉ ፍርሃት ፍርሃት ያለው ይመስላል:: እናም የጦር መሪዎቹን ወደ ድንኳኑ አስጠራና ምክክር ጀመሩ፡፡ “መቼም የዛሬው ውጊያችን ትንሽ ጠንከር ሳይል አይቀርም፡፡ የሚያዋጣንም ያው የድፍረት ሥራችን ነው... መጀመሪያ መሐል ገብተን ነፍስ ነፍስ ያለውን መጣል ነው… ተዚያ በኋላ አውራውን ሲያጣ ጀሌው ነፍሴ አውጭኝ ይላል… ቆይ! እኔ ካሳ ያቺን ወደል ባልቴት ራሴ ይዤ ባቄላ ባላስፈጫት…” አለ ካሳ፡፡ “እንግዲህ ተዚሁ ተሜዳው ላይ እንቆይ ማለት ነው” አሉ ቀኛዝማች እንግዳ በስጋት መንፈስ፡፡ “እዛዲያ ልንሸሽላት ኖሯል?!.. እንግዲህ ወደፊት እንጂ ወደኋላ ማለት የለም!” አለ ካሳ፡፡
የካሳ ጦር ሲመክር የእቴጌ ጦር እያስገመገመ መጣ… እቴጌ በፈረስ ላይ ሆና ሰራዊቷን ታበረታታለች፡፡ በቁጥርና በመሳሪያ ብልጫ ያለው የእቴጌ ጦር ያስፈራል፡፡ ከብዛት አንጻር የካሳን ሰራዊት አንድ በአንድ እጅ እጁን መያዝ ይቻለዋል፡፡ …ውጊያው ተጀመረ፡፡ እቴጌ ጦሯ መሐል ሆና ታዋጋለች፡፡ በርካታ ሴቶች በእቴጌ ዙሪያ ተሰልፈው እልልታና ሆታ እያሰሙ ባሎቻቸውን፣ ወንድሞቻቸውን፣ ሰራዊቱን፣… ያበረታታሉ፡፡ ለመሸሽ የሚያፈገፍገውን “ወዴት ልትሸሽ ኖሯል? በላ ና የእኔ ቀሚስ ውስጥ ግባና ተደበቅ!” እያሉ ይቀሰቅሳሉ… እንደ ተርብ እየተወረወሩ የተጎዳን ያክማሉ፣ የሞተን ያነሳሉ፡፡ የእቴጌ ጦር የካሳን ሰራዊት ምስቅልቅሉን አውጥቶ ገረፈው፡፡
ቀድሞም በውስጡ ፍርሃት የነበረውና ሁኔታውን ያስተዋለው የካሳ ጦር የጦር ስልት ቀየረ፡፡ አንድ በአንድ ከመግጠም ይልቅ በየግንባሩ ተከፋፍለው በእቴጌ ጦር ውስጥ በመግባት ይዋጉ ጀመር… እቴጌ ጦሯ መሐል በበቅሎ ሆና በጀግንነት ስታዋጋ አንድ የካሳ ወታደር እየተሹለከለከ ሄዶ ጭኗ ላይ በጦር ወግቶ ማረካት… የእቴጌ ባል ንጉሡ አፄ ዮሐንስ 3ኛም ምንም ሳይቆስሉ ተያዙ… የእቴጌና የንጉሡ መያዝ የእቴጌን ጦር ፈታው… የካሳ ጦር ያልተጠበቀ በለስ ቀናው፡፡ ካሳ ድል አደረገ፡፡ ምርኮኛዋ እቴጌ መነን በእስረኛነት ወደ ቋራ ተወሰደች…
ምርኮኛዋ እቴጌ መነን
ደራሲ አቤ ጉበኛ በጻፈው “አንድ ለእናቱ” የተሰኘ ታሪክ ቀመስ ልቦለድ ድርሰት ውስጥ አንዷ ገፀ ባህሪ እቴጌ መነን ሊበን ናት፡፡ ደራሲው ባቀረበው ምናባዊ ትረካ ደጃዝማች ካሳ ምርኮኛውን ንጉስ አፄ ዮሐንስ 3ኛን እና እቴጌ መነንን ራሱ ያስተናግድ ነበር፡፡ በዚሁ ጊዜ እቴጌን አየና “ጌታየ እርስዎ ይመገቡ፡፡ እቴጌ መቼም የእኔ ነገር አይሆናቸውም” ይላል፡፡
“ከዚህ በላይ ምን ታደርገኝ ኖሯል?” አለች እቴጌ፡፡
“እርስዎ ጦርዎን እየመሩ እዚህ ድረስ የመጡት ምን ሊያደርጉ ኖሯል?” አለ ካሳ፡፡
“እኛንስ ማረክኸነ ተዚህ ወዲያ ነገ ምን ልታደርግ ነው?” መልሳ ጠየቀች እቴጌ፡፡
“ግድ የለም ስለ ነገ፣ ነገ ያውቃል፡፡ ‘ለነገ አታስብ፣ ነገ ለራሷ ታውቃለችና’ ይላል ወንጌሉ፡፡ ዳሩ እርስዎ ቁራን ነው የሚያውቁት መሰል…” ይላል ካሳ እስላም መሆኗን በአሽሙር ሲናገር፡፡
“በል ተሳደብ… ጊዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል” በንዴትና በንቀት መለሰች እቴጌ፡፡
“እውነትዎን ነው እርስዎንስ ጊዜ ቢሰጥዎ አይደል በእነ እቴጌ ምንትዋብ ዙፋን ተቀምጠው እቴጌ የተባሉ…”
“ኧረ ለመሆኑ ነገ ምን ልትሆን ነው? ዛሬ ተሳደብ!...”
“ነገማ ልጅዎን አሊን አምጥቼ እጨምርልዎታለሁ”
“አሊን አንተ ልትማርከው?” ሳቀቺበት፡፡
“የልጅዎን መከራ ለማየት ምን አስቸኮለዎ?”
“በዳዊት ዙፋን ለመቀመጥ አስበህ ይሆናል እኮ!”
“ለዳዊት ዙፋን ከአሊ እኔ አልቀርብም ብለው ነው?” በማላገጥ መለሰ ካሳ፡፡
“ተው እግዜር ትቢት አይወድም”
“እዚህ ላይስ እውነት ተናገሩ… እርስዎንም እኔ እጅ ላይ የጣለዎ ትቢት ነው… ቆለኛ… ፍየል እረኛ … ሲሉኝ ነበር… ለመሆኑ ዙፋኑን የጠቀሱለት ዳዊት ስራው ምን እንደነበር ያውቃሉ?... በግ እረኛ ነበር፡፡ እንደኔ ቋራ ቢወለድ ኖሮ ግን ፍየል እረኛ ይሆን ነበር…”
“ለመሆኑ ልብህ ተዚያ ላይ ተንጠራርቶ ነው ያለው ማለት ነው?” አለች በንዴት፡፡
“አይ እቴጌ!... ሙተው ቢቀበሩም ተስድብ አይወርዱልኝም… ለነገሩ ንጉስ ከነ እቴጌው ማርኬአለሁ:: ምን ቀረኝ ብለው ነው… ጎንደር ያለው ግንብ ባዶ ነው… ዙፋኑን ራሴ ላይ ብደፋው ማን ይከለክለኛል”
“በጉልበት ልትነግስ?”
“ዱሮስ ጉልበት ያለው አይደል የሚነግስ…”
“ጉልበትህንስ ማን አየልህና…” አለች በንዴት…
“አሊን ሳይሆን እግዚአብሔርን ፈርቼ ነው የተውሁዎ እንጂ ኮሶ እንደጋትሁት ደጃዝማችዎ…” ካሳ ቁጣ ቁጣ አለው፡፡ እቴጌም በቁጣ ሳር እየነጨች ትጥል ጀመር… እያለ ይቀጥላል የአቤ ጉበኛ ድርሰት፡፡
ከላይ ለማሳየት እንደተሞከረው እቴጌ መነን ለሁለት አሰርት ዓመታት የሀገሪቱን ከፍተኛ ስልጣን በመያዝ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በበላይነት በመምራት የልጇን የራስ አሊንና የባለቤቷን የአፄ ዮሐንስ 3ኛን ስልጣን ተጋርታለች፡፡ እቴጌ መነን ከእርሷ በፊት እንደነበረቺው እንደ እቴጌ ምንትዋብ በሀገሪቱ ፖለቲካ ከፍ ያለ ሚና ነበራት፡፡
መነን የምታስተዳድረው ግዛት ነበራት፡፡ ራሷ የምትመራው ጦርም ነበራት፡፡ ጦሯን በመምራት የግብጽ ጦር ጋር ደጋግማ ተዋግታ በማሸነፍ ወታደራዊ አቅምና ችሎታዋን አሳይታለች፡፡ ደጃች ብሩ እና ደጃች ውቤ የተባሉ ታዋቂ የጎጃም ገዢዎች ጋር ተዋግታ አሸንፋለች:: በርካታ ሽፍታዎች ጋር ተዋግታ ግዛቷን አስከብራለች፡፡ በመጨረሻ ከደጃዝማች ካሳ ኃይሉ ጋር ባደረገቺው ጦርነት መጀመሪያ ላይ አሸንፋ ነበር፡፡ በታክቲክ ስህተትና ለካሳ በነበራት ንቀት ምክንያት ተሸንፋለች፡፡ የሚገርመው ነገር እቴጌ መነን በድርድር ከተፈታች በኋላ ከቋራ ወደ ጎንደር ከመሄዷ በፊት ተዋበችን ለማየት የምትፈልግ መሆን አለመሆኑን ካሳ ሲጠይቃት “አልፈልግም!... የሷ ኃላፊነት አንተን በተኛህበት ማነቅ ነው” የሚል ድፍረት የተሞላበት የጀግንነት መልስ ነበር የሰጠቺው፡፡  
መነን በአስተዳደራዊ ብቃቷም የተመሰገነች ነበረች:: በዚያ ወቅት በጎንደር ቤተክርስቲያን ውስጥ መከፋፈል ነበር፡፡ ያንን ችግር ለመፍታት በጎንደር ያለው ሀመረ ኖህ ቤተክርስቲያን ወደ ነበረበት እንዲመለስ አድርጋለች፡፡ ላሊበላ የሚለው የቤተክርስቲያኑ የቀድሞ ስም እንዲመለስ በማድረግ ሁለት መቅደሶችን አሰርታ አንዱን ለቅባት ልጅ አማኞች፣ ሌላኛውን ለፀጋ ልጅ አማኞች በመስጠት እኩልነትን ለማስፈን፣ አንድነትን ለመፍጠርና ሰላምን ለማረጋገጥ ጥረት አድርጋለች፡፡
እቴጌ መነን በስልጣን ዘመኗ በርካታ አውሮፓውያን እንግዶችን አነጋግራለች፡፡ የእቴጌ መነንን ብርታትና ጥንካሬ የተመለከቱና የተደነቁ አውሮፓውያንም በዚያ ወቅት በሩሲያ ከነበረቺው ታላቋና ኃይለኛዋ “ካተሪን” ጋር በማነጻጸር “አፍሪካዊቷ ካተሪን” ማለታቸው በታሪክ ሰነዶች ላይ ሰፍሮ ይገኛል፡፡
ጸሐፊውን በEmail: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡


Read 9058 times