Monday, 19 August 2019 00:00

“የማይሰበረው” ረቡዕ ምሽት ይመረቃል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

• አንጋፋና ወጣት ገጣሚያን ሥራቸውን ያቀርባሉ
        • ተወዳጁ ጃኖ ባንድ ሥነ ሥርዓቱን ያደምቀዋል


             በደራሲና ጋዜጠኛ አንተነህ ይግዛው የተጻፈውና በኢትዮጵያዊው ስራ ፈጣሪ፣ ኢኮኖሚስትና ፈር-ቀዳጅ ባለሃብት በአቶ ኤርሚያስ አመልጋ የሕይወት ታሪክና ስራዎች ዙሪያ የሚያጠነጥነው “የማይሰበረው - ኤርሚያስ አመልጋ” የተሰኘ የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ የፊታችን ረቡዕ በይፋ ይመረቃል፡፡
በዕለቱ ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ ከአትላስ ወረድ ብሎ ከአውሮፓ ህብረት ፊትለፊት ወደ ውስጥ ገባ ብሎ በሚገኘው ማግኖሊና ሆቴል በሚከናወነው የምረቃ ስነስርዓት ላይ ገጣሚ ነቢይ መኮንን፣ አበረ አዳሙ፣ ደምሰው መርሻ፣ ምልዕቲ ኪሮስ፣ ዋሲሁን በላይና ትዕግስት ማሞን ጨምሮ በርካታ አንጋፋና ወጣት ገጣሚያን ስራዎቻቸውን ለታዳሚዎች ያቀርባሉ፡፡
በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የሥነጽሁፍ መምህር የሆኑት ዶ/ር ገዛኸኝ ጸጋው በመጽሐፉ ዙሪያ አጭር ሙያዊ ዳሰሳ በሚያቀርቡበትና ጋዜጠኛ ደግአረገ ነቅዓጥበብ ከመጽሐፉ የተቀነጨበ ማራኪ አንቀጽ ለታዳሚዎች በትረካ በሚያስደምጥበት በዚህ የምረቃ ስነስርዓት ላይ፣ ባለታሪኩ አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የላኩት አጭር ደብዳቤም ለታዳሚዎች የሚቀርብ ሲሆን ተወዳጁ ጃኖ ባንድ ዝግጅቱን እንደሚያደምቀው ይጠበቃል፡፡
በሁለት ክፍሎች ተከፋፍሎ የቀረበውና 12 ዋና ዋና ምዕራፎች ያሉት “የማይሰበረው - ኤርሚያስ አመልጋ” የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ፤“ማረፊያ አንቀጾች” እና “ድህረ-ታሪክ” የሚሉ ተጨማሪ ንዑሳን ክፍሎችን ጨምሮ በ394 ገጾች የተቀነበበ ነው፡፡ ከሳምንታት በፊት ለገበያ የበቃው መጽሐፉ፤በአዲስ አበባና በሁሉም የክልል ዋና ዋና ከተሞች በሚገኙ መጽሐፍት መደብሮችና በአዟሪዎች እየተሸጠ ይገኛል፡፡
አጠቃላይ ዝግጅቱ ከስድስት አመታት በላይ ፈጅቶ የተጠናቀቀው የህይወት ታሪክ መጽሐፉ፤ከወላጆቻቸው የበስተጀርባ ታሪክ አንስቶ የአቶ ኤርሚያስ አመልጋን የልጅነት ሕይወት፣ የወጣትነት ዘመንና የትምህርት ቆይታ እንዲሁም ወደ አሜሪካ አቅንተው፣ ከዘበኝነትና የዩኒቨርሲቲ ተማሪነት እስከ ግዙፉ የአለማችን የፋይናንስ ማዕከል ዎልስትሪት የኢንቨስትመንት ባንኪንግ ስመ-ጥር ባለሙያነት ያለፉበትን ረጅም ጉዞ እንዲሁም፣ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው ለ20 አመታት የተጓዙበትን ስኬት፣ ውድቀት፣ ፈተናና ውዝግብ ያልተለየው የሕይወት ጎዳናም ይዳስሳል፡፡   
በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የታሸገ ውሃ “ሃይላንድ” ለገበያ በማቅረብ እንዲሁም “ዘመን ባንክ” እና “አክሰስ ሪል ስቴት”ን ጨምሮ ባቋቋሟቸው የተለያዩ ኩባንያዎች የሚታወቁት አወዛጋቢው ኢኮኖሚስት ኤርሚያስ አመልጋ፤ ከብረታ ብረት ኮርፖሬሽን የሙስና ክስ ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው፣ ከወራት በፊት በቁጥጥር ስር መዋላቸውና በአሁኑ ወቅትም በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ሆነው የፍርድ ሂደታቸውን በመከታተል ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡
ጸሃፊው፤ ደራሲና ጋዜጠኛ አንተነህ ይግዛው፣ ከዚህ ቀደም “መልስ አዳኝ” እና “ባቡሩ ሲመጣ” የተሰኙ የአጫጭር ልቦለድ ስብስብ መጽሐፍትን ለንባብ ያበቃ ሲሆን፣ ለ54 ተከታታይ ሳምንታት በፋና ኤፍ ኤም 98.1 የተላለፈውንና “ስውር መንገደኞች” የተሰኘውን ተከታታይ የሬዲዮ ድራማ በደራሲነትና በተዋናይነት ለአድማጭ ማብቃቱም ይታወሳል፡፡


Read 5516 times