Print this page
Saturday, 17 August 2019 13:31

ባላገሩ አስጎብኚ የቡሄን በዓል ለዘጠነኛ ጊዜ በጣይቱ ነገ ያከብራል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

 በየዓመቱ የቡሄን በዓል በድምቀት የሚያከብረው ባላገሩ አስጎብኚ ዘንድሮም ለዘጠነኛ ጊዜ ‹‹ቡሄን ለሰላም ለፍቅርና ለአንድነት›› በሚል መሪ ቃል ነገ እሁድ ነሐሴ 12 ቀን 2011 ዓ.ም ከቀኑ 9፡00 ጀምሮ በጣይቱ ሆቴል ግቢ ውስጥ በድምቀት ያከብራል፡፡
በእለቱ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ ወጣቶች፣ የጎዳና ተዳዳሪ ልጆች፣ አርቲስቶችና ታዳጊዎች በበዓሉ ላይ የሚታደሙ ሲሆን፣ መርሃ ግብሩ ከነገተ ኢየሱስ ገነተ ማርያም ቤተክርስያን በሚመጡ ዘማሪያንና ካህናት በውዳሴና በዝማሬ እንደሚጀመር ታውቋል፡፡ በመቀጠልም ስለቡሄና ስለደብረ ታቦር ቅኔ፣ በታዳጊ ወንዶች ትውፊቱን የጠበቀ የሆያ ሆየ ጫወታ፣ የሙልሙል መጋገርና መግመጥ ውድድር፣ እንዲሁም የጅራፍ ማጮህና ግርፊያ ውድድር እንደሚደረግ የባላአገሩ አስጎብኚ ድርጅት ባለቤት አቶ ተሾመ አየለ ገልጸዋል፡፡
በጅራፍ ማጮሁ ላይ ከታዳሚ ፍላጎት ያለው መሳተፍ የሚቻል ሲሆን የችቦ ማብራት ስነ ሥርዓትም ይካሄዳል፡፡
ከቡሄ በዓል አከባበሩ ጎን ለጎን የአፄ ምንሊክና የእቴጌ ጣይቱ የልደት በዓል ለዘጠነኛ ጊዜ የሚከበር ሲሆን፣ ጽምፃዊ አስራት ቦሰናና ዓለማየሁ ፋንታ ንጉሱንና እቴጌዋን በሽለላና በፉከራ ያወድሳሉ ስራቸውን ይዘክራሉም ተብሏል።
በውድድሩ አሸናፊ ለሆኑ በሽልማት መልክ የአንድ ቀን አንኮበርን የመጎብኘት ፕሮግራም የሚዘጋጅላቸው ሲሆን ይህም ኢትዮጵያዊያን አገራቸውን የመጎብኘት ልምድ እንዲያዳብሩ ይረዳል ተብሏል፡፡ የዕለቱን መድረክ ኮሜዲያን አሰፋ ተገኝ እንደሚመራውም ታውቋል፡፡

Read 783 times