Print this page
Saturday, 17 August 2019 13:06

ተቃዋሚዎች ለምርጫ በቂ ዝግጅት እያደረግን ነው አሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(14 votes)

 ከምርጫው በፊት በአገር አንድነት ላይ የጋራ መግባባት ያስፈልጋል ብለዋል

            ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለ2012 ምርጫ በቂ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን በመግለጽ፣ ከምርጫው በፊት የአገር አንድነትና የመተማመን መንፈስ፣ የህግና የሰላም ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት  እንዲፈጠር ጠይቀዋል፡፡
የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፤ ምርጫው በአዲሱ አመት ጊዜውን ጠብቆ እንዲካሄድ ከሳምንት በፊት ውሳኔውን የገለፀ ሲሆን፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በበኩላቸው፣ የመፎካከሪያ አማራጭ ሃሳቦች በማሰናዳት፣ አደረጃጀታቸውን በማጠናከር ለምርጫ በብቃት እየተዘጋጁ እንደሆነ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ ሰባት ድርጅቶች ተዋህደው የመሰረቱት ‹‹ህብር ኢትዮጵያ›› ፓርቲ፤ የአገሪቱን ሁኔታ ለምርጫ ምቹ ለማድረግ መንግስት የራሱን ኃላፊነት ከተወጣ፣ ምርጫው ጊዜውን ጠብቆ መካሄዱ  ጠቃሚ ነው ብሏል፡፡
አገሪቱ ካልተቸገረች እኛ ለምርጫው ዝግጁ ነን ብለዋል - የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ሀላፊ ኢ/ር ዘለቀ ረዲ፡፡ ቅድሚያ ተሰጥቶ አገሪቱን ለምርጫ ዝግጁ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ኢ/ር ዘለቀ ጠቅሰው፤ ነገር ግን  ኢሕአዴግ ወደ ምርጫው መግባት እችላለሁ የሚል ከሆነ፣ ለኛ የሚያስቸግረን ነገር የለም ብለዋል፡፡
ከሌላ ፓርቲ በተሻለ ሁኔታ ፓርቲያችን ከሞላ ጐደል በሁሉም የአገሪቱ አካባቢ በሰፊው እየተደራጀና እየተጠናከረ ነው ያሉት ኢ/ር ዘለቀ፣ በምርጫውም የምንወዳደረው ለማሸነፍ ነው ብለዋል፡፡
አብላጫ የፓርላማ ወንበር አሸንፈን መንግስት ለመሆን፣ አልያም ጥምር መንግስት ለመመስረት የሚያበቃ ወንበር ለማሸነፍ አስበናል፡፡ ዝግጅታችንም በዚያው ልክ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡  ህብር ኢትዮጵያ፣ በሶማሌ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች በስፋት እንደሚንቀሳቀስና ህብረብሔራዊነትን እንደሚያቀንቅን ገልፀዋል - ኃላፊው፡፡  
ከምርጫው በፊት የዜጎች በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት መረጋገጥ አለበት፣ አገሪቱ ሁሉም በጋራ የመሰረቷት የጋራ አገር መሆኗ ላይ መግባባት ያስፈልጋል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የመድረክ አባል የሆነው “አረና ትግራይ ለሉአላዊነትና ዴሞክራሲ” (አረና) በበኩሉ፣ ቀጣዩ ምርጫ ጊዜውን ጠብቆ የሚካሄድ ከሆነ፣ በአማራጭ በፖሊሲም ሆነ በአደረጃጀት በቂ ዝግጅት ስላደረግሁ አልቸገርም ብሏል፡፡
ነገር ግን፣ የፖለቲካ ነጻነት በትግራይ ገደብና ክልከላ የበዛበት በመሆኑ፤ ካልተሻሻለ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች አስቸጋሪ እንደሚሆን ተናግረዋል - የአረና ም/ሊቀመንበር አቶ ጎይቶም ፀጋዬ፡፡
በአብዛኛዎቹ የትግራይ ወረዳዎች የአረና መዋቅር ተዘርግቷል፤ በቀሪዎቹ ወረዳዎችም ከክልሉ መንግስት የሚደርስበትን ጫና ተቋቁሞ እየተደራጀ ነው በማለት የአረና ተወካይ ተናግረዋል፡፡
ኢህአዴግ ምርጫው ጊዜውን ጠብቆ እንዲካሄድ መወሰኑ ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን ከምርጫው በፊት የፖለቲካ ሃይሎች የጋራ ራዕይ የሚፈጥሩበትና አለመተማመን የሚቀርፉበት መንገድ መመቻቸት አለበት ብሏል - አረና፡፡ ለዚህም የብሄራዊ መግባባትና የእርቅ መድረክ እንዲዘጋጅ ይፈልጋል፡፡
ኢ/ር ይልቃል ጌትነት የሚመሩት “የኢትዮጵያውያን አገር አቀፍ ንቅናቄ”(ኢአን)፣
ከምርጫው በፊት ብሄራዊ መግባባትና እርቅ እንዲሁም የህገ መንግስት ማሻሻያ እንደሚፈልግ በመግለጽ፤ አለበለዚያ ኢትዮጵያ ምርጫ ለማካሄድ ዝግጁ አይደለችም ይላል፡፡
‹‹ፓርቲዎች የማይተማመኑበትና፣ የፖለቲካ ወንጀሎች የተበራከቱበት ችግር መፍትሔ ሳያገኝ፤ የጋራ ራዕይ ሳይኖር፣ በወደፊቷ ኢትዮጵያ ላይ የጋራ መግባባት ሳይፈጠር፣ ምርጫ ማካሄድ አገሪቱን ለበለጠ ቀውስ መዳረግ ነው›› ብለዋል ኢ/ር ይልቃል፡፡ እንዲያም ሆኖ ፓርቲያችን  በማንኛውም ጊዜ ምርጫ ቢካሄድ ለመወዳደር ዝግጁ ነው ያሉት ኢ/ር ይልቃል፤ ለምርጫ የሚሆን አውድ ሳይመቻች፣ በምንትስ ያህል ወረዳ እጩ አዘጋጅቻለሁ ብሎ በቁጥር መናገር አይቻልም ብለዋል፡፡
በአማራ ክልልና የክልሉ ተወላጆች ባሉበት መላ የኢትዮጵያ አካባቢዎች መዋቅር እየዘረጋሁ ነው ሲል የገለፀው “የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ” (ኢብን) በበኩሉ፣ ምርጫው በጊዜው መካሄዱ ተገቢ መሆኑንና እየተዘጋጀ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ንቅናቄው አማራጭ ፖሊሲዎችንና የምርጫ ስትራቴጂውን እንዳሰናዳ ጠቅሶ፣ ለምርጫው በተወዳዳሪነት፣ በምርጫ አስፈጻሚነትና በታዛቢነት የሚያገለግሉ አባላትን እየመለመለ መሆኑን ገልጿል፡፡
አስፈላጊ የተቋማት ሪፎርም የተሟሉ ባይሆንም፣ ከነ ችግሩም ቢሆን፣ ለምርጫው ጠንካራ ሆኖ ለመቅረብ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር አጋርነት ለመፍጠር እየተነጋገርኩ ነው ብሏል - ኢብን፡፡
በአገሪቱ ምርጫ ማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ በቅድሚያ እንዲፈጠር ሲያሳስብ የቆየው ኢዜማ በበኩሉ፤ ኢሕአዴግ ወደ ምርጫ ለመግባት ከወሰነ ወደ ምርጫው ለመግባት እንደማይቸገር አስታውቋል፡፡
ፓርቲው በመላ አገሪቱ በሚገኙ ከ400 መቶ በላይ የምርጫ ወረዳዎች ሰፊ አደረጃጀት ፈጥሮ፣ ፖሊሲ አዘጋጅቶ ምርጫውን እየተጠባበቀ መሆኑን የፓርቲው ም/ሊቀ መንበር ዶ/ር ጫኔ ደሳለኝ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
ከምርጫው በፊት፣ አንድ አገር እንዳለን ተገንዘበን፣ በአገር አንድነት ላይ ብሄራዊ መግባባት መፍጠር ይገባናል የሚል አቋም ያለው ኦፌኮ በበኩሉ፣ ምርጫው ወቅቱን ጠብቆ እንዲካሄድ ኢህአዴግ ያሳለፈው ውሳኔ ተገቢ ነው ብሏል፡፡ ኦፌኮ  በምርጫው ተሳታፊ የሚያደርገውን አስፈላጊ ዝግጅትም ከወዲሁ እያደረገ መሆኑን ሊቀ መንበሩ ፕ/ር መረራ ጉዲና አስገንዝበዋል፡፡


Read 8000 times