Saturday, 17 August 2019 12:57

በጳጉሜው የሰላም ፌስቲቫል የ7 አገራት መሪዎች ይገኛሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

 በመጪው ጳጉሜ 2 እና 3 በአዲስ አበባ በሚካሄደው የሰላም ፌስቲቫል ላይ የአምስት አገራት መሪዎች ይገኛሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሚና የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር እንደሚገኙበት ተገልጿል፡፡
የፕሮግራሙ አዘጋጅ ኮሚቴ አባላት ባለፈው ረቡዕና ሀሙስ በሩዋንዳ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሚ በአዲስ አበባ በሚከናወነው የሰላም ፌስቲቫል ላይ እንዲገኙ ላቀረበላቸው ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ መስጠታቸውን የኮሚቴው ሰብሳቢ ዲ/ን አይሸሽም ተካ ተናግረዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ በዚህ ፌስቲቫል ላይ በመገኘት አገራቸው አጋጥሟት የነበረውን የዘር ጭፍጨፋ መንስዔ፣ ክስተቱ በአገሪቱ የፈጠረውን ጉዳትና ከዚህ ችግር የወጡበትን መንገድ በሰፊው ያጋራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ለቀድሞ የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ዶ/ር መላቱ ተሾመ የቀረበላቸውን ግብዣ መቀበላቸውን ያረጋገጡት ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ፤ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ሕዝቤ ነው፣ ያለንን ተሞክሮ ለማካፈል ዝግጁ ነን›› ማለታቸው ታውቋል፡፡
በአዲስ አበባ በሚካሄደው የሰላም ፌስቲቫል ላይ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣኖችን ጨምሮ 5 መቶ ያህል ሰዎች ይሳተፋሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን በዋናነት በአገር አንድነት፣ በይቅርታና በሰላም ጉዳይ ሰፋፊ ጥናታዊ ጽሑፎች እንደሚቀርቡ፣ የኪነጥበብ ድግስም መርሃ ግብሩን እንደሚያጅበው ተገልጿል፡፡ በዚህ ፌስቲቫል ላይ ምሁራን፣ የፖለቲካ ልሂቃን የአገር ሽማግሌዎች ዋነኛ ድርሻ ይኖራቸዋል የተባለ ሲሆን ከፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ እና ሳልቫኪር በተጨማሪም የአምስት አገራት የአገር መሪዎች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

Read 6922 times