Print this page
Saturday, 17 August 2019 12:57

የመንግስት የዓመቱ አጣዳፊ ስራ - 3.ሚ የስራ እድል ፈጠራ

Written by  ሰላም ገረመው
Rate this item
(2 votes)

 - 250 ሺ የስራ እድል በአዲስ አበባ ለመፍጠር ዓመት አይፈጅም - ከንቲባው
         - የኢኮኖሚ እድገት፣ ለሚሊዮኖች የስራ እድል በመፍጠርና ኑሮ በማሻሻል ይለካል ብለዋል - ጠ/ሚ ዐቢይ
                   
        በአዲሱ ዓመት፣ የዜጐችን ኑሮ የሚያሻሻልና ለ3 ሚሊዮን ወጣቶች በቂ የስራ እድል የሚፈጥር፣ አስተማማኝ የኢኮኖሚ እድገት እውን እንደሚሆን ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ የገለፁ ሲሆን፣ የአዲስ አበባ ከንቲባ በበኩላቸው ሩብ ሚሊዮን የስራ እድል እንደሚፈጠር ረቡዕ እለት ተናግረዋል፡፡
አሁን በጀመርነው ፍጥነት ተግተን ከሰራን፣ ከ250ሺ በላይ የስራ እድሎችን መፍጠር እንችላለን ያሉት ከንቲባ ታከለ ኡማ፣ በወሬ የምናጠፋው ጊዜ የለም፤ ወደ ተግባር ገብተናል ብለዋል፡፡
በከተማዋ የሚገነቡት ትልልቅ ፕሮጀክቶች፣ በቀጥታ የስራ እድሎችን እንደሚፈጥሩ፣ ለሌሎችም መነሻ እንደሚሆኑ ከንቲባው ጠቅሰዋል፡፡ በመንግስት በኩል የሚቀርቡ ብድሮችና ድጋፎች፣ ከተንዛዛ አላስፈላጊ ውጣ ውረድ በመላቀቅ፣ ፈጣንና ውጤታማ ይሆናሉ ተብሏል፡፡
የመንግስት ፕሮጀክቶችና የብድር ድጋፎች ግን፣ ካሁን በፊት እንደታየው፣ የዜጐችን የግል ጥረት የሚገድቡ፣ የግል ኢንሽትመንትን የሚገቱ፣ የግል ቢዝነስን የሚያመነምኑ እየሆኑ፣ የሚያዛልቅ አስተማማኝ ውጤት ማምጣት አይችሉም፡፡
ጠ/ሚ ዐቢይ፣ የዜጐች የግል ጥረትና ኢንቨስትመንት፣ በየቦታውና በየጊዜው ከሚገጥማቸው መሰናክል ተገላግለው እንዲያድጉ፣ የስራ እድሎችንም በስፋት እንዲፈጥሩ፣ እንቅፋቶችን ማስወገድና ማጽዳት ዋና ትኩረታችን ነው ብለዋል፡፡
የተረጋጋ ሰላም፣ ማንኛውም ለህይወቱና ለንብረቱ የማይሰጋበት፣ ህግ የተከበረበትና መተማመን የሰፈነበት አገር ሊኖረን እንደሚገባ ገልፀው፤ የመንግስት ትኩረትና በጀትን፣ የምንዛሬና የብድር፣ የታክስ ህግና አሰራርን፣ የትምህርትና የሙያ ስልጠናን ሁሉ በሚያስተካክል፣ በተጣጣመ ቅኝት፣ በተደመረ አስተሳሰብ እንሰራለን ብለዋል፡፡ የተበጣጠሰ አስተሳሰብ ዋና ችግር ነው ብለዋል- ጠ/ሚ ዐቢይ፡፡
ኢትዮጵያ፣ የዜጐችን ጥረት የሚያደናቅፉ መሰናክሎችን በማስወገድ፣ ለግል ኢንቨስትመንትና ለስራ ፈጠራ አመቺ አገር እንድትሆን የወጣውን የመንግስት እቅድ በተመለከተም፤ የኢትዮጵያ የስራ ፈጠራ ዳሬክተር ዶ/ር ኤፍሬም፤ ትክክለኛ እቅድ መሆኑን የጥናት መረጃዎችን በመጥቀስ ተናግረዋል፡፡
ከ189 አገራት መካከል ኢትዮጵያ ያለችበት ደረጃ 159ኛ እንደሆነ ዶ/ር ኤፍሬም ገልፀው፤ ለትልልቅም ሆነ ለትናንሽ ተቋማት፤ የንግድ ፍቃድ አሰጣጥ የተንዛዛ ከመሆኑም በላይ አላግባብ በማመላለስ ዜጐችን የሚያጉላላና ስራ ፈጣሪዎችን የሚያደናቅፍ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የጐዳና  ንግድ ላይ የተሰማሩትን ዜጐች ከማባረር ይልቅ ወደ ሕጋዊነት ማምጣት ይሻላል ያሉት ዶ/ር ኤፍሬም፤ በዚህም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚያስመሰግን አሰራር መጀመሩን ገልፀዋል፡፡

Read 7687 times