Saturday, 17 August 2019 12:55

“ወንጀል ሰርተው የተሸሸጉ ከ600 በላይ ተጠርጣሪዎችን ለህግ ለማቅረብ እየሰራሁ ነው” - ፖሊስ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(1 Vote)


       በሰብአዊ መብት ጥሰትና በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በክልሎች የተደበቁትን ለህግ ለማቅረብ እሰራለሁ ብሏል
                                      
              የተለያዩ የሰብአዊ መብት ጥሰትና የሙስና ወንጀሎችን ፈጽመው፣ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተደበቁ ተጠርጣሪዎችን በመያዝ ለህግ ለማቅረብ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እየሰራ መሆኑን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
ኮሚሽኑ ለሁለት ቀናት ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የፀጥታ አካላት ጋር ባደረገው ውይይት ላይ እንደተገለፀው፤ የህግ የበላይነትን ለማስከበር በሚደረገው እንቅስቃሴ፣ ከባድ ወንጀል ሰርተው በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎችና አካባቢዎች የተደበቁ ተጠርጣሪዎችን፣ በቁጥጥር ስር በማዋል፣ ለህግ የማቅረቡን ተግባር አጠናክረን እየሰራንበት ነው ብሏል፡፡
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ጄይላን አብዱ እንደተናገሩት፤ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ተከስተው የነበሩ የፀጥታ ችግሮችን ለማሻሻል የኮሚሽኑ አባላት ከፍተኛ መስዋዕትነትን የከፈሉ ሲሆን፤ በአጭር ጊዜ ውስጥም ችግሩን በቁጥጥር ስር በማዋል፣ ህብረተሰቡ ሰላማዊ እንቅስቃሴውን እንዲቀጥል መደረጉን ተናግረዋል፡፡ ከሁሉም ክልሎችና ከሁለቱ መስተዳድሮች የፀጥታ አካላት ጋር ውይይት ያደረገው ኮሚሽኑ፤ በወቅታዊ የአገሪቱ የፀጥታ ሁኔታ ላይ በስፋት መክሯል፡፡ የህብረተሰቡን ሰላም ለመጠበቅና የህግን የበላይነት ለማስከበር፣ ከሁሉም ክልሎችና መስተዳድሮች ጋር በትብብር እንደሚሰራ ያስታወቀው ኮሚሽኑ፤ በቀጣይ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ የሙስና ወንጀልና የተለያዩ የሰብአዊ መብት ጥሰት ወንጀሎችን ፈጽመው፣ በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎችና አካባቢዎች ተሸሽገው የሚገኙትን ከ600 በላይ የሚሆኑ ተጠርጣሪዎች፣ በቁጥጥር ስር በማዋል፣ ለህግ ለማቅረብ እየሰራ መሆኑንም አመልክቷል፡፡  


Read 1255 times