Saturday, 17 August 2019 12:52

አዲስ አበባ ልመናና የጎዳና ኑሮን በሕግ ልትከለክል ነው

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

 - በየመንገዱ ላይ ለሚለምኑ ወገኖች መስጠት የሚያስቀጣበት አሠራር ተግባራዊ ይደረጋል
              - ከአገሪቱ የትኛውም ክልል መጥቶ መኖር ይቻላል - ጎዳና ላይ ግን መኖርም ሆነ መለመን አይቻልም
                          - ኢንጅነር ታከለ ኡማ
                              
           በአዲስ አበባ የጎዳና ላይ ኑሮንና ልመናን በህግ ለመከልከል ዝግጅት እየተደረገ ሲሆን በከተማዋ ሰርቶ መኖር እንጂ ጎዳና ላይ መኖርና ልመና እንደማይፈቀድ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ አስታወቁ::
ምክትል ከንቲባው ሰሞኑን በሚሊኒየም አዳራሽ በተካሄደው ‹‹ያገባኛል ይመለከተኛል የመዝሙር ኮንሰርት ላይ እንደተናገሩት፤ ከአገሪቱ የትኛውም ክልልና አካባቢ መጥቶ በአዲስ አበባ ውስጥ ሰርቶ መኖር የሚቻል ቢሆንም፣ ጎዳና ላይ ማደርና መለመን ግን አይቻልም ብለዋል:: ሰርተን መለወጥ እየቻልን በልመና ተግባር ላይ መሰማራት አሳፋሪ ተግባር ነው ያሉት ምክትል ከንቲባው፤ ከዚህ አሳፋሪ ተግባር ለመውጣት የሁላችንም ርብርብ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ገቢው የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ጎዳና ላይ የወጡ ዜጎችን ለማንሳትና የመሰረተውን የማህበራዊ ትረስት ፈንድ ለመደገፍ ይውላል በሚል በሚሊኒየም አዳራሽ በተዘጋጀው የ‹‹ያገባኛል ይመለከተኛል›› የመዝሙር ኮንሰርት ላይ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ እንደተናገሩት ልመና የማንነታችን መገለጫ ሊሆን አይገባም:: መስጠታችን ትውልድን የማይገነባ ከሆነና አገር መቀየር ካልቻለ  ባንሰጥ ይሻላል ብለዋል:: በየጎዳናውና በየቦታው ለሚለምኑ ወገኖች የሚሰጡ ሰዎችም ለዚሁ ተግባር በተቋቋመውና የልመና ተግባሩን የሚያከናውኑና ጎዳና ላይ የወደቁ ወገኖችን ለማቋቋም ለተደራጀው ተቋም የሚሰጡትን መስጠት እንደሚችል ገልጸው፣ ከዚህ ውጪ ግን በየጎዳናው ለሚለምኑ ሰዎች የሚሰጡ ሰዎች ግን ሊቀጡ የሚችሉበት አሰራር ተግባራዊ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡  

Read 1026 times