Print this page
Tuesday, 13 August 2019 00:00

የዘመናዊ ሕክምና ፍልስፍናዊ መሰረት

Written by  ብሩህ ዓለምነህ (በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር)
Rate this item
(3 votes)

(ይህ ፅሁፍ ሳንቴ ሜዲካል ኮሌጅ ሐምሌ 20፣ 2011 ዓ.ም ባዘጋጀው 4ኛው አገር አቀፍ የሕክምና አውደ ጥናት ላይ የቀረበ ነው)

                        (ክፍል-፩)

          ሕክምና ከጥንት ዘመን ጀምሮ በሁሉም ማህበረሰቦች ውስጥ የነበረ ራስን ከበሽታ የመፈወሻ ጥበብ ነው፡፡ ይሄም ጥበብ በዋነኛነት በባህል ሕክምና አዋቂዎች አማካኝነት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ ኖሯል፡፡ ሆኖም ግን፣ እነዚህ የባህል ሕክምና አዋቂዎች መድሃኒትን ከተለያዩ ዕፅዋት በመቀመም የሚያዘጋጁ ቢሆንም፣ ብዙ ጊዜ ግን ለመመለስ የሚቸገሩባቸው ጥያቄዎች ይደቀንባቸዋል፡፡ ለምሳሌ፣ የሕክምና ዕፅዋት አመራረጥ፣ መድሃኒቱ ስለሚወሰድበት ጊዜና መጠን፣ የመድሃኒቱ የጎንዮሽ ጉዳት፣ ለመድሃኒቱ የሚወሰዱና የሚከለከሉ ምግቦችና መጠጦችን በተመለከተ የባህል ሕክምና አዋቂዎች ዕውቀት ላይ የተመሰረተ መልስ ለመስጠት ሲቸገሩ ይታያሉ፡፡
ሕክምና ከባህላዊነት ወደ ዘመናዊነት የተሸጋገረው ለእነዚህ ጥያቄዎች አስተማማኝ መልስ ማግኘት ሲጀምር ነው፡፡ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ደግሞ የሰው ልጅ በአመክንዮ እስኪያድግ መጠበቅ ነበረበት፡፡ የሰውን ልጅ በአመክንዮ ከሚያሳድጉ ትምህርቶች ውስጥ ደግሞ ዋነኛው ፍልስፍና ነው፡፡ በመሆኑም፣ የሕክምና እድገት ከሰው ልጅ የአመክንዮ እድገት ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ነው፡፡
ሜታፊዚክስና ሕክምና
የተለያዩ ማህበረሰቦች የተለያየ የሕክምና ዘዴዎች አሏቸው፡፡ ለምሳሌ፣ አውሮፓውያን፣ አፍሪካውያንና ሩቅ ምስራቃውያን የተለያዩ የሕክምና ጥበቦች አሏቸው፡፡ እናም ጥያቄው፣ እነዚህ አካባቢዎችና ማህበረሰቦች ለምንድን ነው የሕክምና ጥበቦቻቸው የተለያየ የሆነው? የሚለው ነው፡፡ ልዩነቱ የመጣው ማህበረሰቦቹ በሜታፊዚክስ (ስለ ሰውና ስለ ዓለም ያላቸው አመለካከት) የተለያዩ ስለሆነ ነው፡፡ ላብራራው!!
በመጀመሪያ፣ በታሪክ ውስጥ የሚታወቁ ሦስት ሥነ ዓለማዊ አመለካከቶችን እንምረጥ - ዲሞክሪተስ፣ ክርስትናና ሬኔ ዴካርት፡፡ ዲሞክሪተስ የጥንታዊ ግሪክ ፈላስፋ ሲሆን ‹‹ዓለም በዓይን ከማይታዩ ጥቃቅን ተንቀሳቃሽ ንጥረ ነገሮች (አተሞች) የተሰራች ናት›› በማለት ይከራከራል፡፡ በመሆኑም፣ በዓለም ላይ ያሉት ህይወት ያላቸውም ሆኑ ህይወት የሌላቸው ነገሮች የተሰሩት ከእነዚህ ተንቀሳቃሽ አተሞች ነው፡፡
በዚህ የዲሞክሪተስ ሥነ ዓለማዊ አመለካከት መሰረት፣ አንድ ሰው ታመመ የሚባለው ሰውየው የተሰራበት የአተም አወቃቀር ሲፋለስ ሲሆን፣ ሕክምናውም ይሄንን የተፋለሰውን የአተሞች አወቃቀር ወደ ቀድሞው ሁኔታ መመለስ ነው፡፡ ሕክምናው ሥነ ዓለማዊ አመለካከቱ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ የክርስትናን ሥነ ዓለማዊ አመለካከት ደግሞ እንመልከት፡፡ ክርስትና ‹‹ዓለም የተፈጠረችውም ሆነ የምትገዛው በመንፈስ ኃይል ነው›› ብሎ ያምናል:: መንፈስም ሁለት ዓይነት ነው - ቅዱስና እርኩስ መንፈስ፡፡ በዚህ እሳቤ መሰረት፤ የመልካም ነገሮች ሁሉ (ጤንነትን ጨምሮ) መንስኤው ቅዱስ መንፈስ ሲሆን፣ የመጥፎ ነገሮች ሁሉ (በሽታን ጨምሮ) መንስኤው እርኩስ መንፈስ ነው፡፡ በዚህ ሥነ ዓለማዊ እሳቤ መሰረት፤ ሕክምና ማለት እርኩስ መናፍስትን ከታማሚው ሰውነት ማስወጣት ነው፡፡
ወደ ሩቅ ምስራቅ ስንሄድ ደግሞ አኮፓንቸር፣ ሜዲቴሽንና ዮጋን የመሳሰሉ የሕክምና ዓይነቶች እናገኛለን፡፡ እነዚህ ሕክምናዎች የመነጩት ከራሳቸው ሥነ ዓለማዊ አመለካከቶች ነው፡፡
የዘመናዊ ሕክምና ሥነ ዓለማዊ መሰረት
የዲሞክሪተስን ሥነ ዓለማዊ አመለካከት፣ በዘመናዊ ዓለም ውስጥ ተስፋፍቶና አድጎ የምናገኘው፣ የዴካርት ፍልስፍና ውስጥ ነው:: ሬኔ ዴካርት በ17ኛው ክፍለ ዘመን የነበረ የሒሳብ ሊቅና ፈላስፋ ነው፡፡ በሒሳብ ሊቅነቱ በጂኦሜትሪ ትምህርት የምናውቀውን ‹‹Cartesian Coordinates›› የተባለውን ሒሳብ የፈጠረ ነው:: በፈላስፋነቱ ደግሞ ‹‹Cartesian Dualism›› የተባለውን የ‹‹ሁለትዮሽ›› ፅንሰ ሐሳብ ያፈለቀ ነው፡፡
ይህ የሁለትዮሽ ፅንሰ ሐሳብ የሰውን ልጅ የአእምሮና የአካል (mind and body) ጥንቅር አድርጎ ያቀርበዋል፡፡ ዴካርት ‹‹አእምሮ›› ሲል አንጎል ማለቱ አይደለም፤ አንጎል ራሱ አካል ነውና:: ‹‹አእምሮ›› ከአካል የተለየ ተፈጥሮና ባህሪ ያለው፣ በአንጎል ውስጥ የሚገኝ ‹‹ንቃተ ህሊና›› ነው፡፡ በአንፃሩ ‹‹አካል›› ደግሞ የሚታይ፣ የሚዳሰስና ግዝፈት ያለው ሲሆን፣ እንቅስቃሴውም ሜካኒካዊ ነው፡፡
አካልን ከአእምሮ የሚለየው ይህ የዴካርት የሁለትዮሽ ፅንሰ ሐሳብ፣ ለዘመናዊ ሕክምና ፍልስፍናዊ መሰረት ጥሏል፡፡ ልክ እንደ ዴካርት ሁሉ፣ ዘመናዊ ሕክምናም አካልን እንደ ሜካኒካዊ ማሽን ነው የሚያየው፡፡ በዚህ የዘመናዊ ሕክምና ግንዛቤ መሰረት፤ ‹‹ሕክምና ማለት የታመመን ‹‹አካል›› የሚመረምርና የሚያክም ነው፡፡››
በዚህም ግንዛቤው፣ ዘመናዊ ሕክምና የሰውን ልጅ ወደ ‹‹አካል›› ያወርደዋል፡፡ አካል ደግሞ ሜካኒካዊ ማሽን ነው፡፡ ልክ ማሽንን ወደተለያዩ ክፍሎች እንደምንበታትነው ሁሉ፣ ዘመናዊ ሕክምናም አካልን ወደ ወደተለያዩ የአካል ክፍሎች (organs) እና ሴሎች በመተንተን ይመረምረዋል፤ ያጠናዋል፡፡ እናም በዚህ ሒደት ውስጥ ሐኪሙ ግንኙነቱ ከታማሚው ሰው ጋር ሳይሆን ከታመመው የአካል ክፍል ጋር ነው፡፡
እንግዲህ የታመመውን ሰው በሦስት ደረጃዎች ልናስቀምጠው እንችላለን - ‹‹ሰው ነው››፣ ‹‹አካል አለው››፣ ‹‹የታመመ የአካል ክፍል አለው››፡፡ ከእነዚህ ሦስት ደረጃዎች ውስጥ ሐኪሙ ግንኙነት የሚፈጥረው ከታማሚው ‹‹ሰው›› ጋር አይደለም፤ ከታማሚው ‹‹አካል›› ጋርም አይደለም፤ ይልቅስ ‹‹ከታመመው የአካል ክፍል›› ጋር እንጂ፡፡ በዚህም ተግባሩ ዘመናዊ ሕክምና የሰውን ልጅ ከማሽንነትም አልፎ ወደ ታመመ የአካል ክፍልነት ያወርደዋል፡፡
የሕክምና መሳሪያዎችም ሐኪሙ ከታማሚው ሰው ጋር ሳይሆን ከታመመው የአካል ክፍል ጋር ብቻ ግንኙነት እንዲፈጥር ያስገድደዋል፡፡ አልትራ ሳውንድን እንደ ምሳሌ እንውሰድ፡፡ ዘመናዊ ሕክምና ከሚተማመንባቸው በሽታን የመለያ መሳሪያዎች ውስጥ ዋናው አልትራ ሳውንድ ነው፡፡ በአልትራ ሳውንድ የሰው ልጅ አካል ሳይቀደድ የውስጥ የሰውነት ክፍሎቹ በስክሪን እንዲታይ ያደርጋል፡፡ በዚህ መሳሪያ ግፊት የተነሳ፣ ሁልጊዜ አልትራ ሳውንድ ላይ የሚሰራው ሐኪም ‹‹ሰው ማለት የውስጥ የአካል ክፍሎቹ ነው›› የሚል ሜካኒካዊ ግንዛቤ እንዲፈጥር ያደርገዋል፡፡
የሕክምና ሙያዊ ቃላትም (Medical Terms) ሐኪሙ የሰውን ልጅ ከዕቃ ጋር እንዲያመሳስል ያስገድደዋል፡፡ መቅደድ፣ መስፋት፣ መቁረጥ፣ መቀጥቀጥ፣ መሰበር… የመሳሰሉ ቃላትን (ፅንሰ ሐሳቦችን) ለሕክምናና ለዕቃ እኩል እንጠቀምባቸዋለን፡፡ እነዚህ ቃላት የሰው ልጅ አፈጣጠርም ሆነ የአካሉ ተግባራት ከሜካኒካዊ ማሽንነት የተለየ እንዳልሆነ ሐኪሙ እንዲያስብ ያስገድደዋል፡፡
‹‹ሰውን እንደ ማሽን›› አድርጎ የመመልከቱ ተግባር በዘመናዊ ሕክምና ውስጥ ጎልቶ ቢታይም፣ የዚህ አመለካከት አመጣጥ ግን ከሳይንስ ውልደት ጋር የተያያዘ ታሪክ አለው፡፡ በምዕራቡ ዓለም የሐሳብ ታሪክ ውስጥ ከኮፐርኒከስ (1543) እስከ ኒውተን (1700) ዘመን ድረስ ያለው ጊዜ ‹‹የሳይንስ አብዮት›› በመባል ይታወቃል፡፡ ይህ ጊዜ ስለ ሰው ልጅ፣ ስለ ዩኒቨርስና ቁስ አካል በርካታ አዳዲስ ግኝቶችና ሳይንሳዊ አስተሳሰቦች የተወለዱበት ወቅት ነው፡፡
እነዚህን ሳይንሳዊ ግኝቶች ተከትሎ፣ ‹‹ልክ እንደ ዩኒቨርሱ ሁሉ የሰው ልጅ ተፈጥሮም ሜካኒካዊ ነው›› የሚሉ አስተሳሰቦች መምጣት ጀመሩ፡፡ ለምሳሌ፣ ከላይ የጠቀስነው ፈላስፋ ዴካርት፣ የሰውን አካል ሜካኒካዊ አድርጎ አቅርቦታል፡፡ ላ ሜትሪ የተባለ ሌላኛው ፈረንሳዊ ፈላስፍ ደግሞ ‹‹ሰው እንደ ማሽን ነው›› የሚል መፅሐፍ ያዘጋጀ ሲሆን፣ እንግሊዛዊው ፈላስፋ ቶማስ ሆብስ ደግሞ ‹‹የሰው ልጅ የአካል ሥርዓቶቹ - የደም ዝውውሩ፣ የምግብ መፈጨት፣ የነርቭ ሥርዓቱ፣ አተነፋፈሱ ወዘተ - ሁሉ ሜካኒካዊ ናቸው፤ በመሆኑም የሰው ልጅ ውስብስብ የሆነ ባዮሎጂካዊ ማሽን ነው›› በማለት ፅፏል፡፡
እንግዲህ፣ ይሄ ፍልስፍናዊና ሳይንሳዊ አስተሳሰብ ነው በሂደት ጎልብቶ፣ አሁን ባለንበት ዘመን ላይ የዘመናዊ ሕክምና አስተሳሰብ መሰረት ለመሆን የበቃው፡፡ ምንም እንኳ ይህ አስተሳሰብ የሕክምና ሳይንስን በጣም ያሳደገው ቢሆንም፣ አስተሳሰቡ የሕክምና ባለሙያዎችን በጣም አደገኛ ለሆነ የሥነ ምግባር ግድፈት እንዲጋለጡ አድርጓቸዋል፡፡
በክፍል-2 ፅሁፌ፣ ዘመናዊ ሕክምና የሰውን ልጅ ከማሽንነትም አልፎ ወደ ‹‹ታመመ የአካል ክፍልነት›› ማውረዱ እንዴት በሕክምና ባለሙያዎች ላይ የሥነ ምግባር ግድፈቶችን እየፈጠረ እንደሆነ በኮንፈረንሱ ላይ ከራሳቸው ከሕክምና ባለሙያዎች የተሰጡትን ምስክርነቶች እየጠቃቀስን መፍትሔውን እንመለከታለን፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 2285 times Last modified on Friday, 16 August 2019 10:40