Print this page
Wednesday, 14 August 2019 00:00

የአድማስ ትውስታ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 “የብሔር - ብሔረሰብ” ድርጅቶች ይፍረሱ!

     ከአዘጋጁ፡-
ጋዜጣችን አዲስ አድማስ የተመሰረተችበትን 20ኛ ዓመት ከጥቂት ወራት በኋላ ታከብራለች:: የመጀመሪያው የአዲስ አድማስ ዕትም፣ ቅዳሜ ታህሳስ 29 ቀን 1992 ዓ.ም ነበር ለአንባብያን የደረሰው፡፡ ወደ 20ኛው ዓመት በዓላችን በሚያዳርሱን ጥቂት ወራት “የአድማስ ትውስታ” በሚል በሰየምነው በዚህ አዲስ ዓምድ፤ ከቀድሞ ዕትሞች እየመረጥን ጊዜውንና ጋዜጣችንን እናስታውሳችኋለን፡፡ (ሰኔ 1 ቀን 1994)
                     


              በአዋሣ የታየውን አሳዛኝ ክስተት መነሻ በማድረግ በCapital ጋዜጣ የወጣ አንድ ጽሑፍ “Is Ethiopia Dying” በሚል ርዕስ ይጀምራል፡፡ በእርግጥ አገርን የሚገድል ጉድ ሊፈጠር መቻሉን ለሚጠራጠር ሰው፣ “ኢትዮጵያ እየሞተች ነውን?” የሚለው ርዕስ ያልተጠበቀ አደጋ የመጣ ያህል ሊያስደነግጠው ይችላል፡፡
የመጐዳት ወይም የመሞት አደጋ የሚደርሰው በሰው ላይ መሆኑን ለሚገነዘቡ ደግሞ ጥያቄው ግር ሊያሰኝ ይችላል፡፡ የጽሑፉ አቅራቢ ሃሳባቸውን ለማብራራት ጥረዋል፡፡ በቢዝነስ ስራ ታታሪነታቸውና በሰከነ ምሁርነታቸው የሚታወቁት የቀድሞ የአዲስ አበባ ንግድ ም/ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ክብሩ ገና ናቸው - ፀሐፊው፡፡
በአዋሳ በተፈጠረው ብጥብጥ የበርካታ ሰዎች ህይወት መጥፋቱን በጽሑፋቸው መግቢያ ላይ የጠቀሱት አቶ ክቡር ገና፤ “እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በሰላም ሲኖሩ የቆዩ የጐሳ ቡድኖች፤ አላአግባብ በቸልታ የታየ በሚመስል አንድ የፖለቲካ ውሳኔ ዙሪያ ተጋጭተዋል” ካሉ በኋላ የሚያስጨንቁ ጥያቄዎችን አቅርበዋል፡፡
“Have we passed the poing of no return? Are we on the Slippery slope of ethnic violence? Are we heading to oblivion?” አቶ ክቡር ከአዋሳው ግጭት በፊትም እነዚህን ጥያቄዎች ሲያነሱ እንደነበሩ ጽሑፋቸው ያመለክታል፡፡
“የመመለሻ እድል ከሌለበት ቦታ ላይ ደርሰናልን? የምንገኘው በአንሸራታቹ የጐሳ ግጭት ቁልቁለት ላይ ነውን? እያቀናን ያለው ወደ ጠቅላላ ጥፋት ነውን? ለተወሰነ ጊዜ እነዚህን ጥያቄዎች ለራሴ ሳቀርብ ቆይቻለሁ፡፡ እንዲያውም እቅጩን ለመናገር፤ ኢትዮጵያ በህይወት ስለመኖርዋ ወይም ሞታ እንደሆነ ራሴን ጠይቄአለሁ፡፡”
እኔ እንደተረዳሁት፤ አቶ ክቡር “ኢትዮጵያ እየሞተች ነውን?” በሚል ርዕስ ሲጽፉ፤ አገርን የሚገድል አዲስ ያልተጠበቀ አደጋ ተፈጥሯል ለማለት አይደም፤ አደጋው የጐሳ ግጭት እንደሆነ ገልፀዋልና፡፡ የጐሳ ግጭት ደግሞ ከኛው ጋር የከረመ እንጂ ያልተጠበቀ አደጋ አይደለም፤ የሚያስፈራ እንጂ እንደ አዲስ አያስደነግጥም፡፡
“አገር እየሞተች ነውን?” ማለትስ ግር ያሰኛልን? አንዳንዴ በእርግጥም ግር ከማሰኘትም አልፎ ትርጉም የለሽ ይሆናል፡፡ የ“ኢትዮጵያ ትቅደም” መፈክር ይዞ፤ “ከራስህ በፊት አገርህን አስቀድም” ብሎ፤ አገር ከዜጐች ውጭ በራሱ ሕይወት ያለውና የሚመለክ ነገር አድርጐ ማቅረብ ፈጽሞ ለአእምሮ የማይገባ እብደት ነው፡፡
አገር ማለት ለሰዎች ጥቅም፤ ለዜጐች ነፃነትና መብት መከበር ሲባል መፈጠር ያለበት እንጂ ሰዎች የሚያመልኩትና በባርነት የሚገዙለት ጣዖት ለማየት አይሞክርም፤ “ኢትዮጵያ እየሞተች ነውን?” ሲሉ፤ ጭንቀታቸው የዜጐች ህይወት እንደሆነ ገልፀዋል:: አገራችን ማቆምያና መመለሻ ወደሌለው የጐሳ ግጭት እያመራች፣ እንደ አውሬ ወደምንበላላበት እንጦሮጦስ እየተንደረደርን እናልቅ ይሆን? ሲሉ ነው የሚጠይቁት፡፡ ወደዚህ የዜጐች ጠቅላላ እልቂት ማምራት ነው የአገር መሞት - ለአቶ ክቡር ገና፡፡ ለዚህም ነው ጽሑፋቸውን የወደድኩት፡፡ እንዴት ብትሉ፤ ኢትዮጵያውያን ከመከራና ከእልቂት መገላገል ያቃታቸው፤ ዜጋን ሰውን የሚያስቀድም ትክክለኛ የፖለቲካ አስተሳሰብ በአገራችን ጐልቶ የወጣበት አጋጣሚ እስከ ዛሬ ሳይፈጠር በመቆየቱ መሆኑን ስለማውቅ ነው፡፡
አሁን ደግሞ “ከራስህ በፊት ብሔር ብሔረሰብን አስቀድም” በሚል የፋሺዝም ፖለቲካ ሳቢያ እየባባሰ የመጣ የጐሳ ግጭት ትልቅ የእልቂት አደጋ ደቅናኖብናል፡፡ አደጋው በጣም ያስፈራል፡፡ በየጊዜው የጐሳ ግጭት ሲከሰት በይፋ ሲገለጽ የማንሰማው፤ በሰፊው ውይይት ሲካሄድበት የማናየውም በጣም ስለሚያስፈራ ይመስለኛል፡፡ እንዲያ ባይሆን ኖሮማ፣ በተለይ ባለፉት ሦስት ዓመታት በአገራችን ታይቶ በማይታወቅ መጠንና ስፋት ከዳር እስከዳር የጐሳ ግጭቶች መበራከታቸው ማንም ሊክደው የማይችል እውነት ሆኖ እያለ እንዴት ተድበስብሶ ችላ ይባላል? በእጅጉ የሚዘገንን እልቂት የሚያስከትል አደጋ በአካባቢው ሲፍለቀለቅ አይቶ እንዳላየ ማለፍስ ከፍርሃት ሌላ ምን ምክንያት ይኖረዋል? ከፍርሃት ሌላ ተጨማሪ ምክንያትማ አሳፋሪነቱ ነው፡፡ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ፤ ስለ ጐሳ ግጭት፣ ማውራት ያሳፍረዋል:: በዘር ተቧድነው የሚጋጩ ሰዎች ስለመኖራቸው ከመስማትም ሆነ ከመናገር ይሸሻል - አብዛኛው ኢትዮጵያዊ፡፡
ይሁንና፤ የጐሳ ግጭት አስፈሪና አሳፋሪ ቢሆንም በመሸሽ፣ አይንን በመጨፈንና ጆሮን በመድፈን በሰበቡ ከሚመጣ ዘግናኝ መአት መዳን አይቻልም:: መፍትሔ አይደለም፡፡ እንዲያውም የጐሳ ግጭት አሳፋሪና አስፈሪ መሆኑ አይተን እንዳላየን እንድናልፈው ሳይሆን እውነታውን አይተን ወደ ጠቅላላ ጥፋት ከመድረሳችን በፊት እንድናስወግደው የሚያነሳሳን መሆን አለበት፡፡ ችግሩ የጐሳ ግጭትን የማስወገድ ፍላጐትና ቅንነት ቢኖረን እንኳ በቂ አለመሆኑ ነው፡፡ ፍላጐትና ቅንነትማ በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ዘንድ አለ፡፡ የጐሳ ግጭትን ማስወገድና በሩዋንዳ እንደደረሰው አይነት የሚሊዮን ሰዎች እልቂት እንዳይከሰት መከላከል የሚቻለው ለጐሳ ግጭት የሚዳርግ የተሳሳተ እኩይ አስተሳሰብን በትክክለኛ የስነምግባርና የፖለቲካ አስተሳሰብ ውድቅ በማድረግ፣ ከዚያም በተግባር በመተርጐም ብቻ ነው፡፡ በትክክለኛውና በተሳሳተው አስተሳሰብ መካከል ያለውን ልዩነት በማወቅና ትክክለኛውን በተግባር ላይ በማዋል ነው፡፡
ጥያቄው፤ አእምሮውን በመጠቀም ራሱን የሚቆጣጠር ነፃ ሰው በመሆን እንዲሁም አእምሮን ጥሎ በጐሳ መሪ የሚነዳ የመንጋ አባል (እንስሳ) በመሆን መካከል ነው፤ ጥያቄው፤ ራስን የመቻል ሰብዕናን ለመቀዳጀት በመምረጥና፤ እንደ ተባይ በደምና በአጥንት ቆጠራ ለመኖር፤ በዘር ሀረግ ለመንጠላጠል በመመኘት መካከል ነው፡፡ ጥያቄው፤ በሰብአዊ መብት ፖለቲካና በብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ መካከል ነው፡፡
በእርግጥም ጥያቄው በነፃነት፣ በሰላምና በብልጽግና የመኖር የስነምግባርና የፖለቲካ ጥያቄ ነው፡፡ ሰው በአእምሮው የሚጠቀም፤ አስቦ የሚሰራ፣ በጥረቱ ውጤትና በምርቱ የሚኖር፤ የራስ አክብሮትንና ኩሩ ስብዕናን የሚቀዳጅ ሊሆን ይገባዋል? ወይስ፤ “የኛ ዘር” በሚለው የጐሳ መሪ የሚነዳ፤ የራሱ ሃሳብ ሳይኖረው “የኛ ዘር” የሚላቸውን ሰዎች ለማስደሰት የሚርመጠመጥ፤ አንዳች ነገር ሳያመርት “የኛ ዘር ንብረት፤ የኛ ብሔረሰብ ሀብት” የሚል፤ የራስ አክብሮትና ስብዕና የሌለው የመንጋ አባል መሆን አለበት?
እያንዳንዱ ሰው ከሌሎች ከሰዎች ጋር የሚኖረው ግንኙነት በነፃነትና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ የሃሳብ ልውውጥ፣ የስራ ክፍፍልና የምርት ንግድ ሊሆን ይገባዋል? ወይስ “ለኛ ዘር መስዋዕት መሆን ይገባኛል ይገባችኋል” የሚል ትዕዛዝ የመስጠትና የመበል፤ ንብረትን የመንጠቅና የማከፋፈል መሆን አለበት?
ሰውን ጥሩና መጥፎ የሚለው አእምሮውን በመጠቀም የሰውየውን አስተሳሰብ፣ ተግባርና ባህርይ በማየትና በመመዘን መሆን ይገባዋል? ወይስ አእምሮውን አደንዝዞ በጭፍን “የኛ ዘር ጥሩ፤ የዚያ ዘር ጠላት” የሚል መሆን ይገባዋል? ወይስ እሱስ ጥሩ መባል የሚፈልገው በአስተሳሰቡ፣ በተግባሩና በባህርይው መሆን አለበት? ወይስ “የኛ መንጋ አባል ነው” በሚል ምክንያት?
“እያንዳንዱ ሰው፤ ስራው ያውጣው” የሚል የፍትህ መርህ መኖር አለበት? ወይስ ደምና አጥንቱ እየታየ? ሁሉም ሰው በተፈጥሮው አንድ አይነት ሰብአዊ መብት አለው? ወይስ የዚያ ዘር ተወላጅ በመሆኑ የሚቀነስበት አልያም የሚጨመርለት መብት አለው?
የአንድ አገር መንግስት፤ የሁሉም ዜጐች ሰብአዊ መብት አንድ ዓይነት መሆኑን ተገንዝቦ፣ ዘርንና ብሔረሰብን ሳያይ፣ የሁሉንም ሰብአዊ መብት ያስከብር? ወይስ “አንተ የማን ዘር ነህ? አንተኛው የማን ብሔረሰብ ተወላጅ ነህ?” እያለ ዘር ይቁጠር?
የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ መልስ ምን እንደሚሆን የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ዘር መታየት የለበትም እንደሚል እርግጠኛ ነኝ፡፡ ዘረኛ፤ የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካን እንደሚጠላ እርግጠኛ ነኝ፡፡
አእምሮውን የሚጠቀም፤ ራሱን የቻለ፤ ነፃ፣ የራስ አክብሮት ያለው ኩሩ ሰው መሆን እንጂ በጐሳ መሪ የሚነዳ የመንጋ አባል፣ ተባይ፣ ባዶ፣ እኩይ መሆን ለሰው ተፈጥሮ ተገቢ እንዳልሆነ
ጥሩነት በአስተሳሰብ፣ በተግባርና በባህርይ እንጂ ራሱንም ሆነ ሌላውን በዘር ሀረግ መመዘን እንዲሁም በደምና አጥንት መኩራትም ሆነ ማፈር ተባይነት እንደሆነ
የዚህ ብሔር ወይም የዚያ ብሔረሰብ ተወላጅ በመሆን የሚጨመርም ሆነ የሚቀነስ መብት እንደሌለና የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ ዋነኛ የሰብአዊ መብት ጠላት እንደሆነ መገንዘብ፤ የተሳሳተና እኩይ አስተሳሰብን ውድቅ የሚያደርግ ትክክለኛና ቅዱስ አስተሳሰብን መያዝ ማለት ነው፡፡
ከዚህ ቀጥሎ የሚመጣው የመጀመሪያ እርምጃ፤ በተገኘው አጋጣሚ ይህንን ትክክለኛ አስተሳሰብ ይዞ ዘረኛ አስተሳሰብን መመከትና በድፍረት ያለመታከት መከራከር፤ ወላጆችም ለልጆቻቸው በግልጽ ማስተማር ይሆናል፡፡ እያንዳንዳ ዜጋ በተለይም ወጣቶች በአሁኑ ጊዜ ከዚህ የበለጠ ቅዱስ አላማ እንደሌለ ተረድተው በጽናት ጥረት ሊያደርጉ ይገባል:: ከዚህ በኋላ መስራት የሚኖርባቸው በርካታ ነገሮች አሉ፡፡
መንግስታዊ በሆኑ ማናቸውም ነገሮች ውስጥ ብሔርህ፤ ብሔረሰብሽ ምንድነው ተብሎ እንዳይመዘገብ፤ “የዚህ ብሔር ክልል፤ የዚያ ብሔረሰብ ዞን፤ የእገሌ ዘር ወረዳና ከተማ” የሚባል ነገር እንዲቀር፤ በሃህገ መንግስቱና በሌሎች ህጐች ውስጥ “የብሔር - ብሔረሰብ መብት”፤ “የብሔር - ብሔረሰብ ተወካይ”…ወዘተ ተብለው የተጠቀሱ ጽሑፎች እንዲሰረዙ ድምጽን ማሰማት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
በተለይ ደግሞ ሁሉም ሰው፤ ልጆቹን ከመርዘኛ ዘረኝነት ለማዳን መትጋት አለበት፡፡ ዘረኝነትንና የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካን የሚሰብኩ የትምህርት መፃሕፍት፣ የወጣው ወጪ ወጥቶ በአፋጣኝ እንዲለወጡ ወይም እንዲቀሩ ማድረግ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ተግባር ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እስከዛሬ “በብሔር በብሔረሰብ በዘር” ስም የተደራጁ ኢህአዴግን ጨምሮ በርካታ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፤ መንገዳቸው ዘረኝነትን የሚያስፋፋ መሆኑን ተገንዝበው፣ ስህተታቸውን እንዲያርሙ ግፊት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ፓርቲ መመስረት ያለበት በፖለቲካዊ አስተሳሰብ ዙሪያ እንጂ በዘር መሆን እንደሌለበት ተረድተው፣ ስህተታቸውን ለማረም የማይፈቅዱትን ድርጅቶች፣ በጥብቅ ማውገዝና ድጋፍ እንዲያጡ መቀስቀስ፣ የዜጐች የእለት ተእለት ተግባር መሆን አለበት፡፡ “የዚህ ብሄር ምሁራን፤ የዚያ ብሔረሰብ ወጣቶች፣ የእገሌ ዘር የልማት ድርጅት” እየተባሉ የሚቋቋሙ ማህበራት፤ በአጠቃላይ ዘርን እንደ መሰባሰቢያ ቆጥረው የሚፈጠሩ ቡድኖችን መኮነን፣ የእያንዳንዱ ቀና ዜጋ ሃላፊነት መሆን አለበት፡፡
ስነምግባርና ፖለቲካ ፍፁም ከዘር ቆጠራና ከብሔር ብሔረሰብ ትንተና ለማጽዳት መጣር አለበት፡፡ ሰው የመሆን ክብርን ለመቀዳጀት የሚፈልግ ኢትዮጵያዊ ሁሉ፤ በጐሳ ግጭት ከሚመጣ እልቂት ለመዳን የሚፈልግ ሰው ሁሉ፤ የዚህ ወይም የዚያ ዘር ተወላጅ ሳይባል የሁሉም ኢትዮጵያዊ መብት የሚከበርበትና ዘርን የማያይ የፖለቲካ ስርዓት እንዲፈጠር የሚፈልግ ዜጋ ሁሉ!!    

Read 1421 times
Administrator

Latest from Administrator