Wednesday, 14 August 2019 13:17

ከ‹‹ሙከራ ሥርጭት›› ያልወጡ ጣቢያዎች!!››

Written by  ደ.በ
Rate this item
(3 votes)

   ቴሌቪዥን፤ ለፖለቲካ፣ ለሀገራዊ አንድነት፣ ለህዝቦች መከባበር… የሚጫወተው ሚና ቀላል ባይሆንም፣ ተመልካቾች መርጠው ካላዩት የሚፈጥረው ማህበራዊና ስነ ልቡናዊ ቀውስ ቀላል አይደለም ያለማልም - ያጠፋልም፡፡ ‹‹Television Influences people, culture and other media” የሚባለውም ያለምክንያት አይደለም፡፡
የእኛ ሀገር የቴሌቪዥን ምርኮኝነት እንደ ፈረንጆቹ የተጋነነ ባይሆንም፣ እንደ አሸን እየፈሉ የመጡት ጣቢያዎች፣ የፈጠሩት ለውጥ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ አንዳንዶቹ በጐ ተፅዕኖ ሲያሳድሩ፣ ሌሎቹ ደግሞ አሉታዊ ሚና መጫወታቸው አልቀረም፡፡
ሁሉም ነገር በስርዓትና በልክ ከሆነ፣ ማህበረሰብን ከመጉዳት ይልቅ ሊጠቅም ይችላል፡፡ በኛ ሀገር ታሪክ 50 ዓመቱን ያከበረው ኢቲቪና የእርሱ ታናሽ ወንድም ኢቢኤስ፤ የጐዘጐዙበትን እልፍእኝ የሚያጣብቡ አዳዲስ ጣቢያዎች መከፈታቸው በአማራጭነት የሚታይ ቢሆንም፣ አንዳቸውም ግዘፍ ነስተው አላስደነገጡንም ወይም ትኩረታችንን አልሳቡትም፡፡ አስደንጋጭና አስደማሚ አዲስ ነገር በማምጣት “ፓ! እንዲህ ነው!” የሚያሰኝ አንድም ጣቢያ ወይም ፕሮግራም አላሳዩንም፡፡ በሌላ በኩል በተለይ ከ97 ምርጫ ወዲህ ያየውን እንዳላየ “ዐይኔን ግንባር ያድርገው” ሲል የከረመውና ለዓመታት “ዐይንህ ላፈር” የተባለው ኢቲቪ፤ ከቀድሞው ራሱን አሻሽሎ ብቅ ብሏል፡፡ ዋልታና ፋናም ‹‹የገዢው ፓርቲ አጋፋሪዎች ናቸው” ተብለው “በጠላት ዓይን” እንዳልታዩ ሁሉ ዛሬ የራሳቸው ተመልካች ማፍራት ችለዋል፡፡  የዕድሜያቸውን ያህል ግን ብስለትና ጥልቀት አላሳዩም፡፡
አንዳንዱ ተመልካች ዛሬም ድረስ የመንግስት ሚዲያዎችን ከመጠራጠር ገና ስላልወጣ፣ ለማመሣከሪያነት የሚጠቀመው “ኢሳት” የተባለውን የቴሌቪዥን ጣቢያ ነው፡፡ ይህ ጣቢያ በተለይ ለለውጥ በሚደረገው ሁለንተናዊው ትግል፣ ከማንም በተሻለ ሃላፊነቱን የተወጣ፣ የህዝብ መከታና ዓይን ስለነበር፣ ዛሬም በብዙዎች ልብ ተዐማኒነት አለው፡፡
አንድ ሰሞን ሀገር አቅብጦ፣ ነባሮቹን ጣቢያዎች በጥብጦ የነበረው ‹‹ቃና›› ቴሌቪዥን፤ ተመልካቹ ቀስ በቀስ እየቀነሰ መጥቶ፣ አሁን ደንበኞቹ የቤት እመቤቶችና የጓዳ ሠራተኞች የሆኑ ይመስላል - በመረጃ ባይረጋገጥም፡፡ ያኔ ስንቱን ባልና ሚስት እንዳፋታ ፈጣሪ ይወቀው!  አሁን… ግን እንደ ዛራና ቻንድራ ዘመን በየሆቴሉ፣ በየካፌውና በየቢሮው የሚወራለት አልሆነም፡፡ አንዳንዶች ደግሞ የቃና ተመልካች የቀነሰው የጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ የለውጥ ቡድን ሥልጣን ከያዘ በኋላ ነው ይላሉ፡፡
ይልቅስ ቃና ቴሌቪዥን ጉልበት የሰጣቸው፣ ጥበብ የጨመረላቸው ለውድድር እንዲታጠቁ ያደረጋቸውም ጣቢያዎች አለ፡፡ ከነዚህ አንዱ ኢቢኤስ ነው፡፡ ከኢቲቪ በስተቀር ምርጫ በሌለን ወቅት ደርሶ የተሞላቀቀብንና ያሞላቀቀን ጣቢያ ነበር፡፡ በኢቲቪ የተናደድን ሁሉ፣ እርሱን ጥርቅም አድርገን “ኑሮ በአሜሪካ፣ ‹‹ሄለን ሾው››፣ ‹‹አርአያሰብ›› ወዘተ… እያማረጥን ከሰው እኩል የሆንንበት ጣቢያ ነበር:: ከዚያ በኋላም ድራማውንና መዝናኛውን ይዞልን መጥቷል፡፡ አንዳንዴ ልክ ከሚያጣው የሙዚቃ ምርጫው በስተቀር ብዙ ነገሩ፣ ኢቲቪ የወጋንን ቁስል የሻረልን ነበር፡፡
በኋላ ግን ቃና ሲመጣ፤ ገና ዳዴ የጀመረውና በአጭር የተቀጨው “ናሁ” ቲቪና ኢቢኤስ ፈተና ላይ ወድቀው ነበር፡፡ ይሁንና ኢቢኤስ ሁሌ በማደንቀው ጥበብ፣ ፊቱን ታጥቦ ልብሱን ቀይሮ፣ ሌላ ቪሎ አጥልቆ፣ አዲስ ሙሽራ ሆኖ ብቅ አለ፡፡ በውድድሩ ከመደንገጥ ይልቅ የራሱን ደካማ ጐኖች ፈትሾና ነቅሶ፣ አዳዲስ ፕሮግራሞች ይዞ፣ ቅርፁን ቀይሮ ከተፍ አለ፡፡ በጣም የሰለጠነ አካሄድ በመሆኑ አድናቆቴ የትየለሌ ነው፡፡ አዲስ ሲመጣብን በአሮጌ ቆዳ ከመንከርፈፍ ራሳችን አድሰን አደባባዩን መሙላት እንደምንችል ለብዙዎቻችን አስተምሯል፡፡ ነገር ግን አሁንም ቢሆን የማይመቹ መረን የለቀቁ፣ ባህላችንን የሚያኮስሱ አቀራረቦችና ያልተገሩ አንደበቶች ይስተዋሉበታል:: አልፎ አልፎ  ጭንቅላት አልባ የሆኑ…አፍ ብቻ ምስኪኖች ይፏልሉበታል፡፡
‹‹ናሁ›› ቴሌቪዥን ጣቢያ ገና ሲጀምር የነበረውን  መልካም አጋጣሚና ዕድል በቅጡ ቢጠቀምበት ኖሮ… ይሄኔ የት በደረሰ ነበር፡፡ ለአዲስ ጣቢያ፤ በአሮጌ አስተሳሰብ ወንበር ከያዝን ግን የሚጠብቀን ሌላ ሳይሆን ዘጭ ብሎ መቅረት ነው፡፡ ናሁ የገጠመውም ይኸው ይመስለኛል፡፡ ከዕለት ተዕለት ከመሬት የማይነሳ… መሆኑ፣ ህልምና ራዕዩ ምንድን ነው? ያሰኛል፡፡ ሰው አንድ ቦታ ለመቆም እንዴት ጉዞ ይጀምራል?
እንደ ኢቢኤስ ችግሩን አጥንቶ በተሻለ መንገድ መጓዝስ አይቻልም ነበር? የገንዘብና የሰው ሃይል ብክነትም ጭምር ነው፡፡ ተመልካቹ ግን አሁን ለዚህ ደንታ የለውም፡፡ ሲያሻው ፋናን አሊያም ዋልታን እያለ ፖለቲካውን… መዝናኛውን… ድራማውን ያጣጥማል - “ይብላኝ ተኝተው ለቀሩት”  እያለ፡፡
ዛሬም ድረስ ከእናታቸው ጀርባ ያልወረዱና ዕድሜያቸውን ሁሉ “የሙከራ ስርጭት” እያሉ ጡጦ ካፋቸው ያልለቀቁ፣ ግራ የሚያጋቡ ጣቢያዎችም አሉ፡፡ እንደኔ እንደኔ፤ አንዳንዶቹ ሰው ያደረገው አይቅርብኝ ካልሆነ በቀር ጨርሶ መጀመርም  የነበረባቸው አይመስለኝም፡፡ ለምሣሌ ጥሩ የሬዲዮ ፕሮግራም ያላቸው ጣቢያዎች፤ ቴሌቪዥን መጀመር የግድ ነው ያላቸው ማነው? የተወደደላቸውን አጠናክረው ቢቀጥሉ ይመረጥ ነበር፡፡ ሁሉንም ድስት በአንድ ጊዜ መጣድ ምን አመጣው!? እነዚህ ጣቢያዎች ካፈርን አይመልሰን ብለው ካልተፈጠሙ በቀር፣ የያዙትን ጠበቅ አድርገው መቀጠል ይችሉ ነበር፡፡
የቴሌቪዥን ጣቢያ ብቻ የጀመሩትም ቢሆኑ በተሻለ መንገድ መቀጠል አለዚያም ማቆም ነው ያለባቸው፡፡ ዓመት ሙሉ “የሙከራ ሥርጭት” እያሉ… በዓመት አንዴ እንኳን አንድና ሁለት  የተሻሉ ፕሮግራሞችን ይዞ ብቅ ያለማለት ያስገርማል፡፡
ከዚህ ቀደም ከአውሮፓ ባለሙያ አስመጥቷል የተባለው ‹‹አርትስ ቲቪ›› አንድ ሰሞን የግጥም ምሽት እያለ… በሙከራ ስርጭት ብቻ አሰልችቶን ነበር፡፡  አሁን  ግን አርትስ ዐይኑን በጥሩ ሁኔታ እየገለጠ ያለ ይመስላል፡፡ የአዲሷ ስራ አስኪያጅ አሻራዎች በሚያስገርም ሁኔታ እየተገለጡ ነው፡፡ ከበዓሉ ግርማ  ልብወለድ “ከአድማስ ባሻገር” ላይ ተቀንጭቦ የተሰራው፣ የፋሲካ ዋዜማ ላይ ያተኮረ ዶክመንተሪ፣ ተአምር የሚያሰኝ ነው - ድንቅ ሥራ! በቅርቡ ፕሮግራም የጀመረው ጋዜጠኛ ደረጀ ሀይሌ እንዲሁም ፀሐፌ ተውኔት አዜብ ወርቁ፣ በየፊናቸው የተሻሉ ፕሮግራሞች እንደሚያቀርቡልን ተስፋ እናደርጋለን፡፡
የቴሌቪዥን ጣቢያ ማቋቋም፤ አንድ ፕሮግራም እንደ መሥራት ቀላል አይደለም፡፡ ብዙ ዝግጅት፣ የተሻለ የሰው ሃይል፣ አቅምና ብቃት ይጠይቃል:: ገንዘብ ብቻውን ተአምር አይሠራም፡፡ ተዓምር የሚሠሩ ሰዎችን ግን መቅጠር ያስችላል፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ባለሙያ መምረጥ፣ አዲስ ሃሳብ ማመንጨት… ሌላ ጥበብ ይጠይቃል፡፡ አንድ እንጨት ብቻውን አይነድድም፤ ሁለት እንጨትም ጥዶ አያበስልም፡፡ ቴሌቪዥን የቡድን ሥራ ነው - የሃሳብ፣ የምስል፣ የቴክኒክ ወዘተ፡፡ ስለዚህ ብልጭ ብልጭ እያሉ… ከእናታቸው ጀርባ ያልወረዱ፣ ወይም እየዳሁ ቀና ማለት የተሳናቸው የቴሌቪዥን ጣቢያ “የሙከራ ስርጭቶች”፤ ወይ ተነስተው መቆም፣ አሊያም ራሳቸውን ከመድረኩ ማሰናበት ሳይኖርባቸው አይቀርም፡፡
በተረፈ በጥሩ አቋም የጀመራችሁ እየጨመራችሁ፣ ለሀገርና ለወገን በሚጠቅም መንገድ ብትሠሩ ለሁላችንም ይበጀናል፡፡ ጋዜጠኞቻችንም የምትጠቀሙባቸውን ቋንቋዎች እያጠራችሁ፣  ራሳችሁን  በንባብ አሻሽላችሁ፣ እኛም የምንሻሻልበትን መንገድ ጠቁሙን፡፡ እንደ “ሸገር” ያሉ የሬዲዮ ጣቢያዎች የሚሰጡንን የታሪክ፣ የባህል፣ የማንነት፣ የፖለቲካ ዕውቀትና ተሞክሮ ሥጡን፡፡ ከጠለቀ ዕውቀታቸውና ልምዳቸው የሚያካፍሉን አንጋፋ ባለዕውቀቶችን እየጋበዛችሁ አበልጽጉን አደርጁን፡፡
ከወገብ በታች ውዝዋዜ የናፈቀን ይመስል… እርቃን የሚበዛባቸው የዘፈን ክሊፖችን በተለይ ቤተሰብ በሚሰባሰብበት ሰዓት (ለምሳሌ ምሽት እራት ላይ) እያሳያችሁ አታሳቁን፡፡ ለኢትዮጵያውያን ቤተሰቦች ክብር ስጡ፡፡ የአንጋፋዎችን የሙዚቃ ሥራዎች ያለ ይሉኝታ እየመነተፉ፣ ያውም (Live ከስቱዲዮ) የሚያቀነቅኑ ‹‹ይሉኝታ ያልፈጠረባቸው›› ወጣት አርቲስቶችን እያመጣችሁ፣ የአዕምሮ ፈጠራ ዝርፊያን አታበረታቱ፡፡ ፈጠራንና ኦሪጂናሌነትን አታቀጭጩ፡፡
በመጨረሻም የወደቃችሁ እንድትነሱ፣ ዳዴ የምትሉ… ለወፌ ቆመች እንድትደርሱ፣ የምትራመዱም ሩጫ ጀምራችሁ በአድናቆት ለማጨብጨብ እንዲያበቃን እመኛለሁ፡፡    

Read 2579 times