Wednesday, 14 August 2019 10:31

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(1 Vote)


            “አንድ ነገር እንፈልጋለን እንበል፡፡ ነገሩን ለማግኘት የሚያጓጓን፣ እንድንፈልገው ያደረገን ወይም ያስገደደን ምክንያት ይኖራል፡፡
ከምክንያታችንና ከመፈለጋችን በፊት ግን ስለ ነገሩ “መኖር” ዐውቀናል ማለት ነው፡፡ ነገርዬው በሌለበት እንድንፈልገው የሚያደርገን
ምክንያት አይኖርም፡፡ ምክንያት መፍጠር ነገሩን እንዲኖር አያደርገውም፡፡ --”
                           ተረት፣ ተረት!
አንድ ቀን፤ አንዲት ድንቢጥ ወደ እግዜር ዘንድ ቀርባ፡-
“ንጉሡ አደጋ ላይ ነው”  
እግዜርም፡-
“የቱ ንጉሥ?”  
ድንቢጧ፤ ወደ ጆሮው ተጠግታ  ሹክ አለችው፡፡  
እግዜርም ዑራን ጠርቶ ንጉሡን እንዲታደግ ላከው፡፡ ችኩልና ልበ ቢስ የሆነው ዑራ፤ በሰው ተመስሎ እየተጣደፈ ከመሬት ዱብ አለ፤ እንደ ተርሚኔተር፡፡ ከአንድ ዛፍ ስር አረፍ ከማለቱም አሸለበው፡፡ ብንን ሲል ከደቂቃዎች በፊት (በሰማያት አቆጣጠር፤1 ደቂቃ 100 ዓመት ነው) ያየውና የነበረው ሁሉ ተለዋውጧል፡፡ ክፉኛ ደነገጠ፡፡ መደንገጥ የአማልክት ተፈጥሮ አልነበረም፡፡ ዑራ ህግ በመሳቱ ፀጋውን አጣ፡፡ ከሰማይ አካላት ጋር የነበረው የመንፈስ “ኔትዎር” ተቋረጠ፡፡ ወደ መላዕክትነቱ ሊመለስ ቢሞክር አቃተው፡፡ ሰው እንደመሰለ ቀረ፡፡
ሰውየው ዑራ “ንጉሡ፤ አደጋ ላይ ነው” ሲባል የሰማውን አልረሳም፡፡ በየቦታው እየተዘዋወረ፤ “ንጉሡ የታለ? ንጉሡ ማነው?” እያለ ማጠያየቅ ጀመረ፡፡ “አቤት” የሚለው፤ መልስ የሚሰጠው ግን አላገኘም፡፡ ብዙ ሰዎች በዚህ ዘመን፤ “ንጉሥ፣ ንጉሥ” እያለ የሚያደነቁረን ኋላ ቀር ከየት መጣ?” እያሉ ይስቃሉ፡፡
አንደ ቀን፣ አንድ ቦታ “ንጉሡን አይታችኋል? እያለ ሲለፈልፍ፣ ትንሿ ወፍ በዛ በኩል ስታልፍ ሰምታው፤
“አንተ የቁራ መላዕክተኛ! ሰው ሆነህ አረፍከው?” ብትለው፣ ዑራ ለሁለተኛ ጊዜ “ክው” አለ፡፡ “ቁራ ነበርኩ እንዴ?” ብሎ ከማሰቡ ወደ ቁራነት ተቀየረ፡፡ ድንቢጧን ተከትሎ እየበረረ፣ ማረፊያ ሲፈልግ፣ ብዙ ሰዎች መጥረቢያ ይዘው የከበቡት ትልቅ ዋርካ ጋ ደረሰ፡፡ አናቱ ላይ እያንዣበበ “ንጉሡ! ንጉሡ!” እያለ እንደለመደው ሲጮህ፣ ዋርካው በሃይል ተነቃነቀ፡፡ …ፍሬዎቹም ምድር ላይ ተዘረገፉ፡፡ የተሰበሰበውም ህዝብ ቀና ብሎ አሞራውን ተመለከተ፡፡ “እልል! ትንቢቱ ተፈፀመ!” እያለም መጥረቢያውን ወረወረ::-- ምን ነበር ትንቢቱ?
***
ወዳጄ፡- አንድ ነገር እንፈልጋለን እንበል:: ነገሩን ለማግኘት የሚያጓጓን፣ እንድንፈልገው ያደረገን ወይም ያስገደደን ምክንያት ይኖራል፡፡ ከምክንያታችንና ከመፈለጋችን በፊት ግን ስለ ነገሩ “መኖር” ዐውቀናል ማለት ነው፡፡ ነገርዬው በሌለበት እንድንፈልገው የሚያደርገን ምክንያት አይኖርም፡፡ ምክንያት መፍጠር ነገሩን እንዲኖር አያደርገውም፡፡  ከጥበብ ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች ማለትም ለስነጽሑፍ፣ ለሲኒማ፣ ለስዕልና ለመሳሰሉት ግብዓት እንዲሆነን ካልሆነ በስተቀር ለጥበብ ስራ በተለይ ደግም ለፈጠራ ሲሆን፡፡ ግን አእምሯችን ውስጥ የሃሳብ ምስል (imagination) መቅረጽ እንችላለን፡፡ እያፈረስን እየገነባን መልክ እናበጅለታለን፡፡ ለሰይጣን ወይም ለአማልክቶቹ እንደምናደርገው፡፡
ቤት ለመስራት ወይም ህንፃ ለመገንባት ከሆነ የፈለግነው፣ ብሉ ፕሪንት እናዘጋጃለን፡፡ ብሉ ፕሪንቱ ወደ ወረቀት የወረደ ሃሳባችን ነው፡፡ ለማረምና ለማሻሻል ስንፈልግ እንደገና ሃሳባችንን ማስተካከል ይኖርብናል፡፡ ብሉ ፕሪንቱን መሬት ላይ ካቆምነው፣ ሃሳባችን ዕውን ይሆናል፡፡ ካልገነባነው ግን ወረቀት ሆኖ ይቀራል፡፡ ወረቀቱን ከቀደድነው ደግሞ ሃሳብ፡፡ ወረቀት ላይ የመውረዱ ጥቅም ሃሳባችንን ለማስተላለፍ ወይም ለሌሎች ፍጆታ እንዲሆን ይረዳል፡፡ ተፅፎ እንዳልታተመ ወይም ደራሲው እንዳልታወቀ መጽሐፍና ሙዚቃ ይቆጠራል፡፡
አለበለዚያ ልናውቀውና ልከኛ ምስል መፍጠር የማንችለውን ነገር በተጨባጩ ዓለም መፈለግ አየር እንደ መጨበጥ ነው፡፡ ባዶ ቅዠት፡፡ ሊሆን እየቻለ ማድረግ ያቃተን ነገር ከሆነ ግን ችግር የለም፡፡ ግፋ ቢል “ፋንታዚ” ወይም የተሳሳተ ግምት ቢሆንብን ነው፡፡
አንድ ቀን አንድ ሰው ወደ ሻርሎክ ሆልምስ ቢሮ መጣ፡፡ ሆልምስ በግሉ የሚሰራ የወንጀል መርማሪ (Private investigator) ነው፡፡ ሰውየው ቁጭ ብሎ የመጣበትን ጉዳይ ከመናገሩ በፊት፡-
“ብዙ ጊዜ በጽሕፈት ሥራ ላይ የቆየህ ሰው ነህ፣ የመጣኸው ደግሞ ከከተማችን ደቡባዊ ክፍል ነው” አለው ሆልምስ፡፡
ሰውየው በመገረም “እንዴት ዐወቅህ?”
 “የለበስከው ካፖርት የቀኝ እጅጌው ቁልፍ በግራ በኩል ከሚገኘው የበለጠ ስለሚያብለጨልጭ ወይም የተፈተገ ስለሆነ ነው፡፡ የመጣኸው ከደቡባዊው የከተማ ክፍል ነው ያልኩህ ደግሞ በጫማዎችህ የረገጥከው የጭቃ አፈር ያለው እዛ አካባቢ በመሆኑ ነው” አለው፡፡
እረሳሁት እንጂ ስለ ከረባቱና ስለ ሌሎች ነገሮችም ነግሮት ነበር፡፡ ሁሉም ትክክል ነበሩ:: እንደነዚህ ዓይነት በተጨባጭ ሁኔታዎች ላይ የተመሰረቱ ግምቶች (deducational reasonings) ከሞላ ጐደል ዋጋ ከሚያፈሩ፣ ተያያዥነት ባላቸው አጋዥ ሃሳቦች ስለሚደገፉ ሎጂካል ሊሰኙ ይችላሉ፡፡ ባለጉዳዩ ግራኝ ቢሆን፣ ወይም ካፖርት፣ ጫማውንና ክራባቱን ከሌላ ሰው ተውሶ የመጣ ቢሆን ኖሮ ግን ጨዋታው “ስኮር” አያደርግም፡፡ ባዶ ግምትና ጥርጣሬ ወይመ “ምንም” ሆኖ ይቀራል፡፡ በነገራችን ላይ ሆልምስ ራሱ የሰር ኮናል ዶይል ሃሳብ ነው፡፡
ወዳጄ፡- አንድ ሰው የሌላውን ሰው ሃሳብና ዕውቀት ለመረዳት፣ ከሰውየው የተሻለ ዕውቀት ወይም የመረዳት ችሎታ እንዲኖረው ያስፈልጋል:: ለምሳሌ ሰውየው የኮምፒውተር ባለሙያ፣ ባዮሎጂስት ወይም ሰዓሊ ቢሆን ሰውየውን መለካት ወይም መገምገም የፈለገው ሰው፣ ስለ ጉዳዩ ጥልቅ ዕውቀት ከሌለው ትርፉ ጊዜና ጉልበት ማባከን ነው:: የጀርባው ምክንያት ለመማር ብቻ ካልሆነ በቀር፡፡ የኢንተሊጀንስ ስራም እንደዚያ ነው፡፡ መርማሪው ተመርማሪ፣ ሰላዩ ተሰላይ ይሆናል፡፡ በዓሳ መንጠቆ አሳ ነባሪ ለማጥመድ፣ በዓይጥ ወጥመድ ዝሆን ለመያዝ መሞከር በቅዠት እንደመስከር ነው፡፡ መዶሻ ለጨበጠ ሁሉም ነገር ሚስማር ይመስለዋል (To the man who only has a hammer, everything he encounters begins to look like a nail” እንደሚባለው እንዳይሆን ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡
***
ወደ ተረታችን ስንመለስ፡- አምላክ ዑራ የተላከባት ከተማ፣ ህዝቦች፤ ዛፍ ቅዱስ ነው፣ ዛፍ ንጉሥ ነው በማለት የሚያምኑ ነበሩ፡፡ “አምላካችን በአሞራ ተመስሎ የዛፎቻችንን ንጉስ ካላዳነ፣ የመጨረሻው ዛፍ ሲቆረጥ ከተማችን ትወድማለች” የሚል ትንቢት ስለሚነገር ይሰጉ ነበር፡፡
ጊዜ እየተለወጠ፣ ከተሜነት ሲስፋፋ፣ ዛፎቹ እየተመናመኑ፣ ትንቢቱም እየደበዘዘ መጣ፡፡ ዛሬ በከተማዋ መሃል ያለ ዋርካ ባለበት ቦታ ላይ ህንፃ እንዲሰራ መሠረት የሚጣልበት ቀን ነው፡፡ ቦታው በሊዝ ስለተሸጠ ትልቁ ዛፍ ይቆረጣል፡፡ የከተማው ነዋሪዎች መጥረቢያቸውን ስለው ከየቅርንጫፎቹ እየዘነጠሉ ሊወስዱ እየተጠባበቁ ናቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ነው ቁራው ደርሶ “ንጉሡ” ንጉሡ” እያለ መጣራትና መጮህ የጀመረው፡፡ ዋርካው አቤት እንደማለት ሲነቃነቅ፤ ዑራ ፀጋው ተመለሰለት፡፡ የዋርካው ፍሬዎችም ተዘረገፉ፡፡
በዚያው ቅጽበት ህዝቡ ባነነና ፍሬዎቹን እየተሻማ በመውሰድ በየጓሮው አፈላቸው፡፡ ከተማዋም ዳነች፡፡ ወፊቱም ያቅሟን፣ ዑራም የቻለውን አፍሶ ወደ መጣበት ተመለሰ፡፡ ሰማየ ሰማያትም ላይ ተከተላቸው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ መንግስተ ሰማያት፤ “ገነት” ሲባል፤ ዋርካውም” “ንጉሥ ተባለ፡፡
እናም እግዜር እንዲህ አለ፡-
It is written on the sign board “Do not pluck the blossom; But it is usless against the wind, it can not READ!!
(ዕውቀትህ በችግኞቹ ይፈተናል ማለትም አይደል?)
ተረቴን መልሱ!
ሠላም!!   


Read 979 times