Saturday, 10 August 2019 00:00

የማይተኛው ገጣሚና የማያስተኙት ግጥሞቹ

Written by  መዘክር ግርማ
Rate this item
(1 Vote)

 ዛሬ - በዋዜማው --- ለነገ ከርሞነት --- እያማጠ ሳለ፥
ትናንትን ለመኾን --- አምናንም አከለ፡፡
ዛሬ በዋዜማው፡፡ ---
(ወንድዬ ዓሊ)
   
           (የመጨረሻ ክፍል )
የተወለደው ‹‹የስጋ አገር›› ተብላ በምትታወቀው ካቤ ነው፡፡ ካቤ የስጋ ብቻ ሳትሆን የነፍስም አገር መኾኗን ራሱን ምስክር እጠራለሁ፡፡ ገጣሚ ለመሆን የተቀረፀውም በዚችው አካባቢ ነው፡፡ ‹‹ሁሉም ሰው ሲያፈቅር ገጣሚ ይሆናል›› ይባላል፤ አባቱንና ማህበረሰቡን አፈቀረ፡፡ ‹‹ብዙ ሰው ሲከፋው ገጣሚ ይሆናል›› ይባላል፡፡ በእንጀራ እናቱ ተከፋ፡፡ ለዚኽ መከፋቱ ‹‹ሲከፉ›› የሚል ርዕስ የሰጣትን የግጥም ደብተር ሠራ፡፡ ‹‹ሲከፉ›› ዛሬም በመንፈስ ግጥሞቹ ውስጥ ትታያለች፡፡ ነገር ግን እነ ‹‹ሲከንፉ›› ንም ጨምሮባት በተስፋ መኖሩን ትናገራለች፡፡
ብርሃኑ ገበየሁ ደህና አድርጎ እንደገለጠው፤ ‹‹የወንድዬ ሌላው የገጣሚነት ምናብ፤ እንደ ቅዱስ ያሬድ ማኅሌት ሥፍራንና ጊዜን ከሚያጥፍ ኪናዊ ዘለዓለማዊነትና ኹለንተናዊነት ይወለዳል፡፡ በሌላ አባባል፤ ስለ ግጥምና ኪነት ሲዘምር በቅኔ ሠረገላ ሰማያትን እያሰሰ፣ ከሰማያት ጉዞ ልምዱ ምስልና ኅብር እያረቀቀ በመቅረጽ ነው፡፡››
እርግጥ ነው፤ የኪነጥበብ ፈጠራ ከገሃዱ ዓለም ነፀብራቅነት ይልቅ፣ ለምናቡ ዓለም መስታወትነት ትቀርባለች፡፡ አዎ! ጥበብ መስታወት ነች፤ ብዙ ጊዜ አስማተኛ መስታወት፡፡ ተርታ መስታወት አይደለችም፡፡ ተርታ መስታወትማ የተንጸባረቀበትን ሁሉ ያሳያል፡፡ ይህችኛዋ ግን ትመርጣለች፡፡ ሽማግሌውን ወጣት አድርጋ ብታሳይ ‹‹ውሸት›› አንላትም፡፡ ከሰማያት ብትዘግብ፤ ረቂቃንን ብትመዘግብ እናምናታለን፡፡ መርፌ ብታወፍር፤ አየር ብትቆፍር እንቀበላታለን፡፡
ወንድዬም ‹‹ሥነ ግጥምን ከሕይወት ወስደን፣ ከተፈጥሮ ምሥጢር አጣልፈን መልሰን ለሕይወት የምናቀርባት ገፀ በረከት ናት፥ መስታወት፡፡ ከሳችም ወፈረችም፥ ነጣችም ወዛች ሕይወት መልኳን፥ መልከ ባህሪዋን ታይበታለች፡፡›› ሲል ይቺኑ አስማተኛ መስታወት አካትቶ ነው፡፡ ‹‹አስቸግርህ ባጣ›› ዐይነት ግጥሞቹ ተርታዋ መስታወት የምታንፀባርቅባቸው አይደሉም፡፡
በአየር --- ደንገላሳ
በጨረር --- የሳንሳ
በነፋስ ትከሻ --- በገሞራ እስትንፋስ፥
ልመንጠቅ - አንደዜ! --- ስውር ጥበብ ላስስ
ትንሽ --- ልፋሰሰው! --- ዛቴን እዚኽ ትቼው
በሰማያት ጀርባ --- በማይጎረብጠው፡፡ …
ታዲያ ይኽ ኹሉ ሥርዐት የማበጀት ነገር ነው:: የተዝረከረከውን መልክ የማስያዝ (የመመንዘም)፤ የራቀውን የማቅረብ፤ የቀረበውን የማርቀቅ፤ ተርታውን የማግዘፍ፤ ለከቱን የመሰልከክ ወይም በመርፌ ቀዳዳ ግመል የማሾለክ ጥበብ፡፡ አሮጌውንም የማደስ ጭምር፡፡ ታዲያ ሁልቀን አይሳካም፡፡ ወንድዬም ላይ እንደዚህ አይቻለሁ፡፡ በተለይ በወፌ ቆመች ከኅትመት እስከ ግጥም ቁመት ቅር የሚሉ ‹‹ንባብ››ኦች አሉ፡፡ ነገር ግን የ‹‹ወፌ ቆመች›› ከፍታ አባት ልጁ ሲቆም የሚሰማውን ደስታ ያጋባል፡፡ ያው እንግዲህ …
አንዳንድ ቀናት አሉ
ሰማያትን የሚዘጉ
ከሰማያትም አሉ (አንዳንድ)
ቀናትን የሚጨፍጉ
በሰማይና በቀን መሐል
ትልቅ ገደል…
የገደሉ ጠርዝ
የሰው ደርዝ
እንዲል፡፡ የራሱ ደርዝ ነው ገጣሚው፡፡ እንደ ‹‹ፍቅሬ›› ያሉ ደርዘኛ ግጥሞችን የሚያነጥር፡፡
ተደፍኖ ማይጠፋ ---
እንደ ጧፍ የሚነድ፤
ያንቺን ያህል መውደድ ---
ቻልኩበት ልቤ
እውነት የራሴ ነው?
ወይስ - አንቺን ሠርቶ ሠርቶ ---
ለቄንጥ አበጅቶ
እልፍኙ ሲያኖርሽ
ቀሊል ብትኾኝበት
አቤት ያምላክ ሥራ
እንድሸከምለት
ልቡን አውሶኝ ነው!?
አንዳንዴ እንዲህ ከፍ ያለው ገጣሚ፤ አንዳንዴ እንዲያ ለኮፍ ሲያደርግ ልታገኘው ትችላለህ:: አንዳንዴ ወንድዬ ዓሊ ደበበ ሠይፉን፣ ጸጋዬ ገ/መድኅንን ይጠራብሃል፡፡ አንዳንዴ እንዴት አመጣው ከምትለው ብኂሉ ጎን እንዴት መጣበት የምትለውን ታያለህ፡፡ አንዳንዴ የብዕሩ ሙዚቀኛ፣ ከቅኝት ሲወጣ ትመለከታለህ፡፡ ትመለከትና ‹‹ለምን?›› ያልክ እንደሁ ራሱ ይመልስልሃል፡፡ ‹‹አንዳንድ ጊዜ›› ይልሃል ‹‹አንዳንድ ጊዜ››
እንደጣይ ዝናብ ደመና --- አንዳንድ ጊዜ፥
በሞኝ መንገድ ከተገኘ ብልጥ --- አንዳንድ ጊዜ፥
የጣይ በረዶ --- መጠጠሩ፥
የብልጥ ሞኝነት መክረሩ፤
ምሽት የፈጠነች ለታ --- አንዳንድ ጊዜ፥
ፈሪ በለስ የቀናው ለታ --- አንዳንድ ጊዜ፥
አቤት! --- ! የቀን ሌሊቱ ማዋለሉ፥
የፈሪም ቀንበር መወደሉ፡፡
ጀግና ሽንፈቱን ሲያማ --- አንዳንድ ጊዜ፥
እውን ከቅዠት ሲስማማ --- አንዳንድ ጊዜ፥
ሽንፈት እጀግና ላይ ክፋቱ፥
የቅዠት ሲሳይ ማስጠላቱ፡፡
ደግነቱ
አንዳንድ ጊዜ ብቻ መምጣቱ፡፡
ሌላው የወንድዬ ፍለጋ ‹‹ጊዜ›› ነው፡፡ ከጸጋዬ ገ/መድኅን፣ ከሰሎሞን ዴሬሳና ከዮሐንስ አድማሱ በስተቀር ለሌሎች ገጣምያን እምብዛም የማይታየውን ዛሬን ከነገ፥ ድሮና ዘንድሮን የመተርጎም ጥበብ የወንድዬ ሥራዎች ድርና ማግ እየሆነ የሚመጣባቸው ሥራዎች እጅግ በርካታ ናቸው፡፡ /ብርሃኑ፣ 2001)
ቀንን ከዓመት ‹‹ቀን -ዓመት›› ብሎ ያስተሳስራል:: ቀን ሲደጋገም ዓመት ነው፡፡ ‹‹ቀን - ዓመትን›› ስትደጋግመው ቀና ዓመት ይሆናል፡፡ አየህ መደጋገም መልካም ስም አለው፤ ልክ እንደዚህ፡፡ እስከ ዛሬማ በመደጋገሙ የሚሰለቸንን ቀን ነው የምናውቀው፤ ‹‹ተኝቶ መነሣት አቤት ሲያቅለሸልሽ›› የሚያሰኘንን፡፡ ወንድዬ ግን የሚባለውን (ይዘት) በመባያው (ቅርጽ) በመደበቅ አዲስ ሥርዓት አበጀለት፡፡ ቀን - ዓመት፤ ቀና - ዓመት ነው ለካ፡፡
ዛሬ - በዋዜማው ---
ለነገ ከርሞነት --- እያማጠ ሳለ፥
ትናንትን ለመኾን --- አምናንም አከለ፡፡
ዛሬ በዋዜማው፡፡
በሌላ ዐይን ደግሞ ‹‹ትላንት፤ ዛሬና ነገን›› እንዲህ ከፍ ያደርጋቸዋል፡፡
ጥሬው፦ ለቀለብኽ፥
ለዛሬዎች ስንቅኽ --- ፍቅርኽን መሳቢያ
ገለባም፦ አትናቅ፥
ላምና ከብትነትኽ - ይኹን ማደለቢያ፡፡
ዳሩ ‹‹ጊዜ››ም ለወንድዬ የሥርዐት አላባ ነው፡፡ በመድበሎቹ ሥርዐትን ያጅባል፡፡ ‹‹የፍጥረት ድር - የኑሮን ክር - የሚፈታ የሚቋጥር [-] የአምላክ ጥፍር›› ኾኖ ቀርቧል፡፡ ሥርዐት ደግሞ የአምላክ እጅ፡፡
ወንድዬ ሀገሩን እንኳ ከሌሎች ሀገሮች አወዳድሮ ሲያደላላት የሚያጣቅሰው ሥርዓቱን ነው፡፡
የአንዱ ዘር --- ገና በጫካ - ቅጠል ፍራፍሬ በጥሶ፥
ለአዳሩ - ሥራ ሥር ምሶ
ሌላውም ገና በዋሻ - የመኖር ዳዴ ሲጀምር፥
ቀለቡን አውሬ ሲያባርር
ይቺ ሽሙንሙን - የውበት ምድር --- እንዲል፡፡
‹‹መለሎ ይኹን ጎልዳፋ፤ የቀና ይኹን ቆልማማ ወይም ሻካራ ቢኾን ለስላሳ … ግን ሌጣ ሬትና ማር የሕይወት ገጽታዎች ፈርቅጬ፤ ዳምጬ፤ ነድፌና አመልምዬ በፈተልኳቸውና በሸመንኳቸው ማጎናጸፊያዎች ጥበባዊ ልቀት ላለብሳቸው ኹለንተናዬን እሰጣለኹ፡፡›› ሲል ስለ ሥርዓቱ ሂደት እየነገረን ነው፡፡
ደጋግሜ ሳየው በወንድዬ ግጥሞች የሚታየኝ ‹‹ገጸ ሰብ›› ብቸኛ ነው፡፡ ፀጥታ የሚወድ ብቸኛ:: አልፎ አልፎ ያፏጫል፡፡ ደጋግሞ ይቆጫል፡፡ ቢኾንም ዐይኑ ከከፍታ አይወርድም፡፡ መውረድ አይወድም:: ከፀጥታው ሊወጣ ‹‹አሣ[ብ] በመንጠቆ፣ ተስፋ በመሰንቆ›› ያሰግራል፡፡ በራሱ ቀልዶ በራሱ ይሥቃል፡፡ ተማላይ አማላይም ነው፡፡ በአጠቃላይ ራሱን ገጣሚውን ይመስለኛል፡፡
ገጣሚው ዛሬ 60 ዓመታትን በተሻገረ ዘመኑ፤ ‹‹ሳልጽፍማ ሞቼአለሁ!›› እያለ ይጽፋል፡፡ ለመኖር:: ላለመሞት፡፡ ይጽፋል፡፡ ሦስተኛ መድበልም ለማውጣት እያሰበ መሆኑን ሰምቻለሁ፡፡ ሲያወጣ የምለው ይኖር ይሆናል፡፡ እስከዚያው ‹‹ደህና መሆን ደህና›› …፡፡

Read 1213 times