Wednesday, 14 August 2019 10:23

እኛ የባህር ዳር አሸዋዎች

Written by  (አሸናፊ በሪሁን ከSeefar)
Rate this item
(1 Vote)


                   ኖረን እኮ አናውቅም
ከባህር ጠርዝ ላይ
እንደ ክቡር ድንጋይ
እሬሳ ስንለቅም።
ከሙሴ ተምረን
ባህር መግመስ ሲያምረን
በታንኳ ሄድንና በሳጥን ተመለስን…….
(በዕውቀቱ ስዩም)
                 

             የመንንና ሶማሊያን የሚለየው የኤደን ባህረ ሰላጤ፣ የአለማችን ትልቁ የባህር ላይ የንግድ መስመር ነው፡፡ በእስያና አውሮፓ ሀገራት፣ ትልቁ የንግድ መገናኛም ይኸ መስመር ነው፡፡ ህገ ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች፣ ስደተኞችን ወደ አረብና  አውሮፓ ሀገራት ለማሻገር የሚጠቀሙበት ዋነኛ መስመርም ነው፡፡  ክፋቱ ታዲያ ከዚህ አካባቢ የሚወጡ ዜናዎች ሁሌም የስደተኞችን አሰቃቂ ሞትና አደጋ የሚያረዱ መሆናቸው ነው፡፡ ከሟች ስደተኞች መካከል ደግሞ አብዛኛውን  ቁጥር የሚይዙት  ኢትዮጵያውያን መሆናቸው ሃዘናችንን ያበረታዋል፡፡ አንገትንም ያስደፋል፡፡
በቅርቡ እንኳን በየመን አድርገው ወደ ሊቢያ፣ ከዚያም ወደ አውሮፓ አገራት ለመግባት በጉዞ ላይ ከነበሩ 300 ስደተኞች መካከል ገሚሶቹ የባህር ላይ አሸዋ ሆነው ቀርተዋል፡፡ ከሟቾቹም ውስጥ ብዙዎቹ የእኛ  አገር ዜጎች ሳይሆኑ እንደማይቀሩ  ይገመታል፡፡ ይህ ደግሞ በተለይ ለወላጆቻቸውና ቤተሰቦቻቸው እጅጉን ሰቅጣጭና ልብ የሚሰብር ነው። የተለያዩ መስመሮችን በመጠቀም፣ ከኢትዮጵያ ወደ ተቀረው ዓለም የሚደረግ ህገ ወጥ ስደት፣ የብዙ ዜጎቻችንን ህይወት መቅጠፉን እንደቀጠለ ነው፡፡
የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን ሪፖርት እንደሚለው፤ ለስደተኞች  ክፍት በተተወ ድንበር፣ ሰው አዘዋዋሪዎች፣ ህገ ወጥ ስደተኞችን እንደ ልብ እያስገቡበት ሲሆን አሁንም ድረስ በወር 7ሺ የሚሆኑ ስደተኞች፣ አደገኛ የባህር ላይ ጉዞ በመጋፈጥ፣ በየመን አቋርጠው ለማለፍ  ይሞክራሉ፡፡ እስከ ሞት የሚያደርስ አደጋ እያጋጠማቸውም ቢሆንም፣ ባለፈዉ ዓመት ብቻ  ወደ 87 ሺ የሚጠጉ ስደተኞች የኢትዮጵያና የሶማሊያ ባህር አቋርጠው ወደ የመን ጉዞ አድርገዋል። በዚህ ጉዞም በርካቶቹን  የባህር ዳር አሸዋ ውጦ አስቀርቷቸዋል፡፡  ባለፈው ዓመት (2018)  ብቻ በሜድትራንያን ባህር አድርገው፣ የአውሮፓ ህብረት ደቡባዊ ድንበር ወደ ሆኑት ጣልያን፣ ግሪክ ፣ማልታና ስፔን የገቡ ስደተኞች ቁጥር ከ112 ሺህ በላይ እንደሆኑ የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን ሪፖርት ይጠቁማል፡፡ ሌሎች ከ6700 በላይ ስደተኞች ደግሞ በእግር ስፔን ገብተዋል። እነዚህ ከአደገኛና ፈታኝ የበረሃና የባህር ጉዞ በኋላ አሸዋ ሳይበላቸው፣ እንደ ዕድል በህይወት ተርፈው፣ አውሮፓ መድረስ የቻሉት ብቻ ናቸው። የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን፤ በዚህ የጉዞ መስመር የሞቱና የደረሱበት ያልታወቀ ስደተኞች ቁጥር ከ2262 በላይ እንደሚሆን በሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡
ታዲያ ይህን የሞት ዜና እየሰሙና እያዩም እንኳን  አሁንም ብዙዎች በህገ ወጥ መንገድ በመጓዝ፣ የባህር ላይ አሸዋ ሲሳይ ለመሆን፣ ሻንጣቸውን ሸክፈው ይጠባበቃሉ፡፡  እነዚህ ስደተኞች፤ ገና እግራቸው ከቤት ሲወጣ በህገ ወጥ አዘዋዋሪዎችና ደላሎች እጅ ውስጥ ነው የሚገቡት፡፡ ከዚያም በእነዚሁ ሰብአዊነት በማይሰማቸው ፍጡራን አስከፊ በደልና ስቃይ ይደርስባቸዋል፡፡ ሲከፋም ህይወታቸውን ይነጠቃሉ፡፡
በአብዛኛው ወጣት ስደተኞች በአደገኛ ጉዞ፣ ከኢትዮጵያ ለመሰደድ ምክንያት ከሚሆናቸው ጉዳዮች መካከል ዋነኛው፤ “ባህር ማዶ በቂ ገንዘብ የሚያስገኝ ሥራ በቀላሉ ይገኛል” የሚል የተጋነነና በቀቢፀ -ተስፋ የተሞላ የህገ ወጥ ደላሎች መረጃ ነው፡፡ ደህንነቱ ያልተጠበቀ  ስደት ጉዳይ ሁላችንም ሊያሳስበን ይገባል፡፡ በየበረሃው ለዱር አውሬዎችና ለባህር አሸዋ ሲሳይ እየሆኑ፣ ያለ ነጋሪና ቀባሪ ተበትነው የሚቀሩ  ስደተኞች፤ የእኛው እህትና ወንድሞች ናቸው:: ህብረተሰቡ፤ በየቀዬው ስደተኞችን ወደ ሞት የሚገፉ ህገ ወጥ አዘዋዋሪዎች እነማን እንደሆኑ ያውቃል። በመሆኑም ስራቸውን በመቃወምና ለህግ አሳልፎ በመስጠት፣ የልጆቹን ህይወት መታደግ ይኖርበታል ፡፡  በየክልሉም ስለ ህገወጥ ስደትና አደጋዎቹ  ግንዛቤ የመፍጠር መጠነ ሰፊ ስራ  ከተሰራ ችግሩን መቅረፍ  ይቻላል። ዝነኛው ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ ) “ኩርኩማ አፍሪካ” በሚለው ዜማው ላይ ፡-
ከእንግዲህ ይብቃ ስቃይ በምድርሽ ላይ
ሄዶ ከመሆን የባዳ አገር ሲሳይ …………
ሲል እንዳዜመው፤ ዜጎቻችን የባህር ላይ አሸዋ ሲሳይ መሆናቸው ይብቃ ማለት ይገባናል፤በአንድ ድምጽ፡፡ ዕውቁ  ገጣሚ በዕውቀቱ ስዩም፣“እኛ “በሚል ግጥሙ፣.የኢትዮጵያውያንን የስደት ስቃይ እንዲህ ይገልፀዋል፡-
ኖረን እኮ አናውቅም
ከባህር ጠርዝ ላይ
እንደ ክቡር ድንጋይ
እሬሳ ስንለቅም።
ከሙሴ ተምረን
ባህር መግመስ ሲያምረን
በታንኳ ሄድንና በሳጥን ተመለስን…….
 ሁሉም ህገ ወጥ ስደትን ለመከላከል ከልቡ በቁርጠኝነት ከተጋ፣በስደት ሳቢያ የሚከሰት አሰቃቂ የዜጎች የሞት ዜናን የማንሰማበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን፤ የአውሬ ሲሳይና የባህር ዳር አሸዋ መሆን ይብቃን ብለን በአንድ ድምጽ እንወስን፡፡    


Read 3360 times