Print this page
Saturday, 10 August 2019 00:00

‘ጤፍ በጄሶ’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ሁለት ጓደኛሞች ጣጣው ባለቀለት የሆነ ምርጫ ላይ እድል ስለቀናው ሰው እየተነጋገሩ ነው፡፡
“ስማኛ፣ እሱ ሰውዬ በደንብ አድርጎ ምርጫውን ሰርቆታል እያልኩህ ነው፡፡”
“እኔ ደግሞ አልሰረቀም፣ ተራ አሉባልታ ነው እያልኩህ ነው፡፡”
“አንተ ስለምትደግፈው ምንም ቢሉህ አታምንም::”
“እሺ እንዳምንህ ማስረጃ ስጠኝ፡፡”
“ቆይ፣ ድምጽ ለሰጡት ሰዎች ገንዘብ አልሰጠም እያልከኝ ነው?”
“እሱን ማን ካደ፤ መስጠትማ ሰጥቷል…”
“ታዲያ ለምንድነው አልሰረቀም እያልክ የምትከራከረኝ?”
“እሱ እኮ ድምጽ ከመስጠቱ በፊት ምረጡኝ ብሎ አይደለም የሰጣቸው፡፡ ቆጠራው አልቆ ከቀናው በኋላ ‘ስለመረጣችሁኝ ደስ ብሎኛል’ ብሎ፤ የፍንጥር ጉርሻ ቢጤ ነው የሠጣቸው፡፡”
አሪፍ አይል! ምርጫ ላይ ‘አሳብሮ መግባትን’ በተመለከተ እንዲህም አይነት ነገር አለ ለማለት ያህል ነው፡፡ አሀ…ልክ ነዋ! የደስ ደስ፤ የፍንጥር ጉርሻ ቢጤ አትስጡ ብሎ ነገር የለማ!
እናላችሁ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ይቺ “ጉርሻ ቢጤ፣” የሚሏት ነገር…አሁንም በሽበሽ ነች ነው የሚባለው፡፡ (“ከማን የፌስቡክ ገጽ ላይ አገኘኸው፣” እንዳትሉኝ!) እንደ ‘ቶክ ኦፍ ታውን’ ከሆነ፣ ሞቅ ብሎ እንደቀጠለ ነው ይባላል፡፡ ነገርዬው…“ወይ ታጎርሳለህ፣ ወይ ራስህ የምትጎርሰው  ታጣለህ፣” አይነት ነገር ይመስላል፡፡
ነገሮች ሁሉ ‘ጤፍ በጄሶ’ ሲሆኑ ልክ አይመጣም::
ታዲያላችሁ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… እንደው ሁሉም ነገር እንኳን ቢያቅተን ጥቂት ጥራት ያላቸው ነገሮች ለማየት አንታደለም! የምርት ጥራት ወርዶ፣ ወርዶ አይደለም እኛን በዓለም አቀፍ ገበያ ለመወዳደር እያቃትን እኮ ነው፡፡ ምርቶች ከተላኩ በኋላ “ጥራት የለውም…” እየተባሉ ይመለሳሉ እኮ:: ይኸው… አለ አይደል…ጤፉ በጄሶ፣ በርበሬው በሸክላ፣ ቅቤው በሙዝ!...ሌላ ሌላውም እንዲሁ፡፡
በብዙ ስፍራዎች የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ወርዶ፣ “ደንበኛ ንጉስ ነው፣” የምትለዋን መፈክር. መጀመሪያ ያወጣ ሰው ቢያየን ኖሮ…“እኔ ታዲያ ሌሎቹን እንጂ እናንተን አልኩ እንዴ!” ይል ነበር፡፡
የትምህርት ጥራት ወርዶ... ተማሪዎች በምረቃ መጽሄቶቻቸው…“ሳትማር ያስተማርከኝን መምህሬን አመሰግናለሁ፣” እያሉ እስከ መቀለድ የደረሱበት ጊዜ ነው፡፡ በየጊዜው ስለ ትምህርት ጥራት መሻሻል ይወራል፡፡ ለዚሁም ቃል የሚገባው፣ የአቋም መግለጫ የሚያወጣውን ስትሰሙ የትምህርት ጥራትን የማሻሻል ተግባር  የዓመታት ሂደት መሆኑ ቀርቶ በመስቀል አደባባይ ሰልፍ የሚስተካከል ይመስላል፡፡ በዚህ ዘመን ደግሞ ማንንም ቢሆን ነጸ የሚያወጣው እውቀትና እውቀት ብቻ ነው፡፡
ነገሮች ሁሉ ‘ጤፍ በጄሶ’ ሲሆኑ ልክ አይመጣም::
እኔ የምለው… የኳሳችን ነገር ጅቡቲ እጅ ላይ ይጣለን! በመከራ ነው እኮ በድምር ውጤት በአንዲት ግብ ልዩነት ‘ያሸነፍናት!’ ተጫዋቾች በየትኛውም ሌላ ፕሮፌሽን የማይከፈለውን በወር ሁለትና ሦስት መቶ ሺህ እያገኙ፣ ከኳስ ጋር ስሟ ተነስቶ የማያውቀው ጅቡቲ፤ ታንከራተን! እንደውም ሰሞኑን ሰዉ “የጅቡቲ ተጫዋቾች ከቂማ ላይ ተነስተው ነው የተጫወቱት፣” እያለ የሚቀልደው የሚለው ቢጠፋው እኮ ነው!
እናማ…የኳሳችን ነገር የጥራት ጉዳይ አይደለም፣የሆነን ነገር ከ‘ጥራት’ ጋር አያይዞ ለመናገር እኮ ነገርየው የሆነ ደረጃ ላይ መድረስ አለበት::  ፊፋ እኮ ህጎቹን ለውጦ “ከእንግዲህ አሸናፊና ተሸናፊ የሚለየው በጎል በመበላለጥ ብቻ መሆኑ ቀርቶ ሀገራቱ በስፖርት የቆዩበት ዘመን፣ የህዝባቸው ብዛት፣ የተጫዋቾች አማካይ የወር ክፍያ ምናመን ሁሉ ታይተው ነው፣” ቢል እኮ አለቀለን፡፡ በአንድ ግበ በለጥን ያልንበት የሦስት ለሁለት ውጤት በአዲሱ ህግ መሰረት ለጅቡቲ አስራ ዘጠኛ ለአንድ ይሆናል…ያውም በይግባኝ አራት ግብ አስቀነሰን፡፡ (ቂ…ቂ…ቂ)::
ታዲያችሁ…የሜዳው ላይ ውጤት ሲገርመን ካፍ የሚሉት ጎጉልቤ መጣና “አንድ ነፍስ ያለው ሰቴዲየም የላችሁም፣” ብሎን እርፍ! በስንት ነገር  ከአፍሪካ አንደኛና ሁለተኛ፣ ከዓለም ምናምነኛ ነን፣” ስንል ከርመን ቴዲየም የላችሁም! (እኔ የምለው… ሦስተኛው ነው አስረኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ የቆምነው!)
ነገሮች ሁሉ ‘ጤፍ በጄሶ’ ሲሆኑ ልክ አይመጣም::
የስቴዲየም ነገር ከተነሳ…አለ አይደል…በዙልን፣ ዘመናዊ ስቴዲየሞች ተሠሩልን ስንል ነበር እኮ የከረምነው፡፡ ነገርዬው ምን መሰላችሁ… እዚህ ሀገር ብዙ ነገሮች የሚሠሩት በውድድር መልኩ ሳይሆን በፉክክር ነው፤ ነገሮች መሠራት ስላለባቸው ቸው ሳይሆን ያኛው ወገን ስለሠራው ብቻ “ማን ከማን ያነሳል!” አይነት ነገር ነው፡፡ አንዱ አካባቢ ስታዲየም ሲያሠራ ሌላው “ለእኛም ያስፈልገናል…” በሚል ሳይሆን… “እነሱ ሠርተው እኛ ለምን ይቀርብናል…” አይነት የመንደር ፉክክር አይነት ነው፡፡ በአካባቢው እኮ፣ አይደለም በስርአት የተደራጁ እግር ኳስ ቡድኖች ማግኘት፣ ኳሷ ራሷ በመከራ የምትገኝ ልትሆን ትችላለች፡፡ እናማ… ከዛሬ የማያልፍ፣ ለ‘መሸለያ’ “እንቁልልጭ፣ እኛም አለን፣” አይነት አስተሳሰብ ቀርቶ ወደፊት ሠላሳና አርባ ዓመት ማሰብ ቢቻል ኖሮ፣ የተሻሉ ሥራዎች ይኖሩ ነበር፡፡
እናማ…ሀሳብ አለን…አፍሪካ ዋንጫን ለሁለተኛ ጊዜ ወስደን ሀያ ዓመት እንድናወራው ‘ስፔሻል ሰርከምስታንስስ ተብሎ የበፊቶቹ አራታችን ብቻ እንድንጫወት ሀሳብ ይቅረብልን! ለነገሩ እንደ እሱ ቢሆንስ ምን ሊመጣ! ጅቡቲ! ጅቡቲ! ጅቡቲ በኳስ ውሀ፣ ውሀ ታሰኘን!
ነገሮች ሁሉ ‘ጤፍ በጄሶ’ ሲሆኑ ልክ አይመጣም::
ይቺን ስሙኝማ…ከተወሰኑ ዓመታት በፊት የሆነ ነው፡፡ የሆኑ ሰፈር ልጆች አንድ የሙት ዓመት መታሰቢያ ድግስ ይገባሉ፡፡ የሚበቃቸውን ያህል በልተው ጠጥተው ሲወጡ አንድ ነገር ነበር ያሉት… “ዓመት፣ ዓመት ያድርሰን፡፡” ምናልባትም እንደዛ የሚባል መስሏቸው፣ ምናልባትም ሆነ ብለው የባህሪያቸውን ጨለማ ወገን ሲያሳዩ፡፡ እናላችሁ…እዚህ ሀገር ችግር “ዓመት፣ ዓመት ያድርሰን፣” የተባለ ይመስል እየተመላለሰብን ነው፡፡ እንዲህ፣ ሆኖ ግን ሁሉም ነገር ጥራቱ እየወረደ መሄዱ ሀገራዊ ‘ኢመርጀንሲ’ ነገር አለማስከተሉ እኛው ሆነን ነው፡፡
ነገሮች ሁሉ ‘ጤፍ በጄሶ’ ሲሆኑ ልክ አይመጣም::
እናማ…የጥራት መጓደል ነክሶና ጨምድዶ የያዘን ጉዳይ ነው፡፡
ደግሞላችሁ …ፖለቲካና ፖለቲከኞቻችንስ ቢሆኑ…ጥራት ጠፍቶ አይደል እንዴ፣ መከራ በሰልፍ አንዱ ሲያልፍ ሌላው የሚተካብን!
የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትም በአፍጢሙ እየተደፋ ነው፡፡ ስሙኝማ…የሆነ ነገር ትዝ ብሎኝ ነው! የመብራት ሰዎች እንደው ምን አደረግናችሁና ነው ይህን ያህል የምንጉላላው? የትኛውን የቤት አጥራችሁን ነቅነቅንባችሁ ነው! ዘመናዊ ልንሆን ነው፣ ቤታችሁ ቄጭ ብላችሁ ልትከፍሉ ነው፣ ሰልፍ ቅብጥርስዮ ብሎ ነገር ሊቀርላችሁ ነው…ነገር  ተብለን አልነበር እንዴ! ጭራሽ የወር ሂሳብ ለመክፈል እንደ ቡናና ጊዮርጊስ ጨዋታ የስታዲየም ሰልፍ መሆን አለበት! ወደ ኋላ ተመልሰን ‘ለሁሉ’ የሚባሉትን “በአፋችንም በሆዳችንም ለረገምናችሁ ሁሉ ይቅር በሉን…” ምናምን ማለት አለብን እንዴ!
እናላችሁ…በየቤተሰቡ ዶሮዋ ተገነጣጥላ ከመቅረቧ በፈት እኮ የብልት ድልድሉ ተካሂዶ አልቋል፡፡ ፈረሰኛው “ለአባወራ ነው፣” አለቀ፡፡ የመብት ጥያቄ ብሎ ነገር፣ “እኛስ አይወድልንም ወይ!” ብሎ ነገር የለም፡፡ “ይህ ጉዳይ ሲወሰን እኛ ስላልተሳተፍንበት እንደገና ይታይ‹” ብሎ ‘ጭቅጭቅ’ የለም፡፡ ሌኒን “ምርጥ ምርጡን ለህጻናት፣” ብሎ ነበር አሉ፡፡ እናማ…ዘንድሮ ምርጥ ምርጡን እነማን እየወሰዱት እንደሆነ ጥናት ይደረግልንማ! ጥያቄ አለን…ቦተሊከኞች፣  ባለቆዳ ወንበሮች፣ ሌሎቹም እንደኛ ሂሳብ ለመክፈል ጠዋት ሁለት ሰዓት ተሰልፈው፣ አምስት ሰዓት ነው የሚደርሳቸው? አንድ ጀልባ ውስጥ መሆናችን አለመሆናችንን ለማረጋገጥ ያህል ነው፡፡ ፈረሰኛው የት፣ ጄሶው የት እንደሆኑ ምልክት ብናገኝ ብለን ነው፡፡ 
ነገሮች ሁሉ ‘ጤፍ በጄሶ’ ሲሆኑ ልክ አይመጣም::
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 2480 times