Wednesday, 14 August 2019 10:17

የማን ቤት ልበለው?

Written by 
Rate this item
(0 votes)


            ለረጅም ጊዜ የተሰጠኝን ኃላፊነት ለመወጣት ስል ከመሯሯጥ በስተቀር ወደ ግል ጉዳይ አላልኩም፡፡ የነበረብኝ ኃላፊነት ከጊዜ ወደ ጊዜ ክብደት ነበረው፡፡ ከ1963 ዓ.ም እስከ 1966 ዓ.ም በደቡብ ግንባር በጦር አለቅነት (ሻለቃ አዛዥነት)፣ ድንበራችን በሱማሌ እንዳይደፈር በኃላፊነት አሠራ ነበር፡፡ በ1966 ዓ.ም መጨረሻ፣ በአብዮቱ ፍንዳታ ጊዜ፣ የአራተኛ ክፍለ ጦር ዘመቻ መኮንን እንደነበርኩ፣ የአስተባባሪ ደርግን ሥራ አስፈፃሚነት ደርቤ መስራት ጀመርኩ፡፡
በ1969 ዓ.ም መጀመሪያ ጀምሮ አንድ ክፍለ ጦር በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዳሰለጥን ታዝዤ፣ በአምስት ክፍለ ሀገሮች በመከፋፈል ማለትም በሸዋ፣ በሲዳሞ፣ በከፋ፣ በሐረርጌና በጎንደር ማሰልጠን ጀመርኩ:: ክፍለ ጦሩ እንደተዘጋጀ በአዛዥነት ይዤ አስመራ ዘመትኩ፡፡ እዚያ እያለሁ የሰሜን እዝ ምክትል አዛዥ ሆንኩ፡፡ ይህ ኃላፊነት በወቅቱ ምን ዓይነት እንደነበረ ያየ ያውቀዋል፡፡ውጤቱ ግን ክፉ አልነበረም፡፡
በ1972 ዓ.ም የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሆንኩኝ፤ጥሩ ሹመትና ጥሩ ስራ ነበር ፡፡
በ1973 ዓ.ም በጥር ወር፣ ባላሰብኩት ሰው ገጭቼ ጡረታ ተባልኩ፡፡
አሁን ጎጆዬን ማየት ግድ ሆነ፡፡ ፈራርሳለች፣ ተጣማለች፣ ማቃኛዋ ቀላል አልሆነም፡፡ ለጊዜው 1,200፡00 ብር ብቻ እጄ ላይ ነበረች፡፡ በሷ ምን መስራት ይቻላል ቀደም ሲል የመጣ ሁለት መኪና ድንጋይ በራፍ ላይ ነበረኝ  ብቻውን ምን ዋጋ አለው?
‘’ጡረታ ወጥቷል ያውም  በጥፋት ነው’’ የሚባለው ወሬ ተሰማ፡፡ በዚህን ጊዜ ባለቤቴ ሆስፒታል  ልጄ እስር ቤት ነበሩ፡፡ ጡረታ የወጣው በጥፋት ነው  የሚለው  ቃል  የዕለት  ጓደኞቼን ሲያርቅ እውነተኛ ጓደኞቼን ይበልጥ ሰበሰበልኝ፡፡
ጀነራል መርዕድ በዚህ አጣብቂኝ ውስጥ እያለ ከቤታችን ከማይጠፉት ዘመዶቻችን መካከል ከጋሽ ተሰማና ከአቤ (ኢንጂነር ተሰማ ያኢና ኢንጂነር አበበ ነጋሽ) ጋር ማታ ቁጭ ብለው መወያየት ይጀምራል:: በማስታወሻው ላይ ስብሰባ ብሎ በሰየመው ርዕስ ይህንን ጭውውት  ከምን ተነስቶ ምን እንደደረሰ እየተረከ እንዲሁም በችግሩ ጊዜ የደረሱለትን ሰዎች እያነሳ ምስጋናውን ያቀርባል፡፡
ስብሰባው፡-የሀዘንና የትካዜ አልነበረም፡፡ በሚያሳፍር ተግባር አልወጣህም፣ ነገ ትመለሳለህ ትፈልጋለህ፡፡ እስከዚያ  እኛ አለንልህ ፡፡የትናንቱ የኢትዮጵያ ድንበር አስከባሪ ፣ የትናንቱ ጀግና፣ የተሻለ እንጂ ያነሰ አትኖርም፡፡ የኛ ወዳጅነት ትርጉም የሚኖረው ዛሬ ነው፡፡ ስለዚህ አታስብ ይልቁንስ ሃሳብህን ግለፅልን ሲሉ፣ ተሰማ ያኢና አበበ ነጋሽ ጠየቁኝ፡፡
“ቤት አድሳለሁ ብዬ ያመጣሁትን ድንጋይ ሸጡልኝ” አልኳቸው፡፡
“ለምን?” አሉኝ
ገንዘብ ስለሌለኝ እድሳቱን ማቆም ስላለብኝ ነው ብዬ መለስኩ፡፡
ነገ ማታ እመጣለሁ ብለው ሄዱ፡፡
በማግስቱ ማታ መጥተው ይህንን ቤት እናድሰዋለን፤ በሠራዊት በኩል እንደጀመሩት፣ በድንጋይና በአሸዋ ማቅረብ በኩል፣ እንዲረዱህ ጠይቅ አሉኝ፡፡ ኮሎኔል መሐመድና ሻለቃ ኪዳኔ ተክሉን ጠይቄ፣ የሚቻለውን ሁሉ እናደርጋለን አሉ:: የቤቱ ስራ በአበበና በተሰማ መሐንዲስነት ኃላፊነት ተጀመረ፡፡
በአምስተኛ ቀን ባለቤቴ ከሆስፒታል ልጄ ከእስር ቤት ወጥተው በአንድ ቀን አሮጌዋ ቤቴ ሞቀች፡፡ ዘመድ ወዳጅም እንደ ዛሬው ተሰበሰበ፡፡ የቤቱም ስራ ቀጥሎ ዛሬ ካለበት ደረጃ ደረሰ፡፡
(“ለወገንና ለአገር ክብር”
ሜጀር ጀኔራል መርዕድ ንጉሤ)

Read 2893 times