Saturday, 10 August 2019 00:00

“የቀጣይ አመት ዋነኛ የኢኮኖሚ እድገት መለኪያ የስራ እድል ፈጠራ ይሆናል”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

  ለ3 ሚሊዮን ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር ታቅዷል

              በቀጣይ አመት ዋነኛው የኢኮኖሚ እድገት መለኪያ የስራ እድል ፈጠራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ያስታወቁ ሲሆን ከ3 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ እድል ለመፍጠር መታቀዱን ገልፀዋል፡፡
መንግስት ላወጣው የስራ እድል ፈጠራ መሳካትም የዘጠኙን ክልሎች ርዕስ መስተዳደር፣ የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች፣ 10 የፌደራል ሚኒስትር መስሪያ ቤቶችን ያካተተና በጠቅላይ ሚኒስትሩና ምክትላቸው የሚመራ ኮሚቴም ተቋቁሟል፡፡
በጠ/ሚኒስትሩ የሚመራው  ይህ ኮሚቴ በዋናነት አራት የስራ ፈጠራ መስኮችን መለየቱ የተገለፀ ሲሆን ግብርና፣ ማዕድን፣ ቱሪዝምና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ የተመረጡ ሴክተሮች ናቸው፡፡
በዚህ ኮሚቴ ውስጥ በዋናነት የግብርና፣ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ፣ የመስኖና ኤሌክትሪክ፣ የማዕድንና ነዳጅ፣ የባህልና ቱሪዝም እንዲሁም የሳይንስና   ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እንዲካተቱ መደረጋቸው ታውቋል፡፡
ሁሉም ክልሎችና የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ከንቲባዎችም በክልላቸውና ከተማቸው የኮሚቴውን እቅዶች የማስፈጸም ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡
ኮሚቴው የዚህን እቅድ የስራ አፈጻጸም በየሁለት ወሩ እየተገናኘ ይገመግማል ክትትል ያደርጋል ብለዋል ጠ/ሚር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል፡፡
በዚህ የኢንቨስትመንትና የሥራ እድል ዋነኛ እቅድ ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚወስዱት የግል ባለሀብቶች መሆናቸውን የገለፁት ጠ/ሚኒስትሩ፤ የክልልና የከተማ መስተዳደሮች ለኢንቨስተሮች ከውጣ ውረድ የፀዳ ምቹ ሁኔታ እንደሚያመቻቹም ጠቁመዋል፡፡
በአመቱ መጨረሻም ክልሎች የከተማ መስተዳደሮች ምን ያህል የስራ እድል እንደፈጠሩ ግምገማ ይደረጋል ተብሏል፡፡
በ2018 በወጣው የአለም ባንክ ሪፖርት መሰረት፤ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከ10 ሚሊዮን በላይ ወጣት ስራ አጥ ሲሆን በየአመቱም ከ2 እስከ 3 ሚሊዮን የሚደርስ ተጨማሪ ለስራ የደረሰ ሃይል አገሪቱ እያፈራች ነው፡፡


Read 3777 times