Saturday, 10 August 2019 00:00

10 ፖሊሶች በስራ አለመግባባት ሰበብ ተገድለዋል

Written by 
Rate this item
(0 votes)



   - በስራ ምደባ ለውጥ ሳቢያ ባለፈው ሳምንት 2 ፖሊሶች በጥይት ሞተዋል
   - አንዱ ላይ ብቻ ነው የተኮስኩት ብሏል - በግድያ የታሰረው ፖሊስ
 - በአዲስ አበባ በአመት 220 ግድያዎች ተፈጽመዋል

                ሟች ብርቱካን ፍሬው ከዋና ሳጅን ብርሃነ ግደይ ጋር በጋብቻ ተሳስረው ሲኖሩ፣ አንድ ወንድ ልጅ አፍርተዋል፡፡ ለ9 ዓመታት በትዳር ቢቆዩም በመሀከላቸው በነበረ አለመግባባት ፍቺ መጠየቋን የፖሊስ መዝገብ ያስረዳል፡፡
ለፍ/ቤት የቀረበው የፍቺ ጥያቄ ለመጋቢት 4 ቀን 2011 ዓ.ም ነበር የተቀጠረው፡፡ ሆኖም ከቀጠሮ በፊት የካቲት 28፣ የፌደራል ፖሊስ ካምፕ አጠገብ በሚገኝ ካፌ ውስጥ ከወንድ ጋር ተቀምጣ አየኋት የሚለው ዋና ሳጅን ብርሃነ፤ ክላሽ በመውሰድ ሟች ብርቱካንን በ15 ጥይት እንደመታትና ህይወቷ እንዳለፈ መዝገቡ ይጠቁማል፡፡
ክስ ተመስርቶ ጉዳዩም ወደ ፍ/ቤት አምርቷል፡፡ የፌደራል ፖሊስ ረዳት ሳጅን ከበደና ዋና ሳጅን ፈይሳ ከድር፤ ከሁለት ዓመት በላይ አብረው ቢሠሩም፣ መልካም ግንኙነት እንዳልነበራቸው ለፖሊስ በሰጠው ቃል ላይ ይገልፃል - ረ/ሳጅን ከበደ፡፡
በማዕከላዊ ስታትስቲክስ ተመድቦ ይሰራ የነበረው ሳጅን ከበደ፣ ሀምሌ 29 ቀን 2011 ዓ.ም ለስራ ወደ ጃንሜዳ አካባቢ እንዲሄድ መልዕክት የደረሰው በዋና ሳጅን ፈይሳ ከድር ነበር፡፡ ለምን አንተ ትነግረኛለህ? ጥፋትም ካለብኝ በደብዳቤ ተገልፆልኝ ነው የምሄደው…›› በማለት ውዝግብ እንደተነሳ ተጠቅሷል፡፡ ወደ በር ሲሄድ ለስራ የተሰጠውን መሳሪያ ከአምስት ካርታ ጥይት ጋር ይዞ እንደነበርና ዋና ሳጅን ፈይሳን በመመልከቱ ሁለት ጊዜ ተኩሶ መግደሉን ለፖሊስ ተናግሯል::
በረዳት ሳጅን ታሪኩ ላይም ግድያ ፈጽመሃል ተብሎ ፖሊስ ቢጠረጥርም፣ እኔ የተከሰስኩት በዋና ሳጅን ፈይሳ ላይ ብቻ ነው፤ ምናልባት እሱን አልፎ በወጣ ጥይት ም/ሳጅን ታሪኩ ተመቶ ሊሆን ይችላል በማለት ነው ቃሉን የሰጠው፡፡
በአዲስ አበባ አስራ አንድ ሰዎች ህይወታቸው ያለፈው የፖሊስ አባላት ነው፡፡ አስሩ በስራ ላይ ባለመግባባት ሰበብ የተፈፀሙ ግድያዎች እንደሆኑ የምርመራ መዝገቦች ያሳያሉ፡፡
በአዲስ አበባ ከሐምሌ 1 ቀን 2010 ዓ.ም እስከ ሰኔ 30 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ ሁለት መቶ ሃያ ሁለት ግድያዎች መፈፀማቸውን የፖሊስ መረጃዎች ይገልፃሉ፡፡   

Read 1544 times