Saturday, 10 August 2019 00:00

የተመዘገበው ባለ ሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ እድገት በብድርና በገንዘብ ኖት ህትመት የመጣ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

ባለፉት አመታት የተመዘገበው ፈጣን አገራዊ የኢኮኖሚ እድገት፣ በውጪ ብድርና በገፍ ገንዘብን በማተም የተገኘ መሆኑ ጥናት ያቀረቡ ምሁራን ገልጸዋል፡፡ የገንዘብ ህትመቱ በየአመቱ 27 በመቶ ሲጨምር እንደነበርም በጥናቱ ተጠቁሟል፡፡
በማህበራዊ የጥናት መድረክ አዘጋጅነት ‹‹የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲና በኢኮኖሚው ውስጥ የመንግስት ሚናጋ በሚል ርዕስ በተዘጋጀ የምክክር መድረክ ላይ ጥናት ያቀረቡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ምሁር ፕ/ር አለማየሁ ገዳ እንደገለፁት፤ ባለፉት አመታት ተመዝግቧል የተባለው በባለ ሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ እድገት በአመዛኙ በብድርና በገንዘብ ህትመት የመጣ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
መንግስት ከውጭ አገራት በገፍ ብድር ሲወስድ እንደነበር ያስገነዘቡት ፕ/ሩ፤ ይህም በአሁን ወቅት አገሪቱን ለ29 ቢሊዮን ዶላር እዳ ዳርጓታል ብለዋል፡፡ ከአገር ውስጥ ባንኮች የተበደረው ብድርም ከውጭ አገራት ከተበደረው የማይተናነስ መሆኑን ፕሮፌሰሩ አመልክተዋል፡፡
መንግስት ባለፉት አመታት የገንዘብ ኖት በገፍ እያተመ ወደ ገበያ ማሰራጨቱም ዜጎችን ለኑሮ ውድነት አጋልጧል፤ ያለው ጥናቱ፤ የገንዘብ ዝውውሩም ከኢኮኖሚ እድገቱ አንጻር በገበያ ውስጥ መኖር ከነበረበት ሦስትና በአራት እጥፍ የበለጠ ነው ተብሏል፡፡  ከ1983 ዓ.ም በፊት በገበያ ውስጥ የነበረው የገንዘብ ዝውውር 68 ቢሊዮን ብር እንደነበር ያወሱት ፕሮፌሰሩ፤ አሁን ግን 740 ቢሊዮን ብር ያህል መድረሱን አስታውቀዋል፡፡  
ይህ የገንዘብ ኖት ህትመት በከፍተኛ መጠን ካልተገታ፣ ዜጎችን ለዋጋ ግሽበት በማጋለጥ ለኑሮ ጉስቁልና እንደሚዳርግም ተጠቁሟል፡፡ በብድርና በገንዘብ ኖት ህትመት ተደግፎ የመጣው የኢኮኖሚ እድገትም በአገሪቱ ያለውን የድህነት መጠን እምብዛም እንዳልቀነሰና ዜጎችን ከኑሮ ጉስቁልና መታደግ እንዳልቻለ በዚህ ጥናት ተመላክቷል፡፡  

Read 862 times