Saturday, 10 August 2019 00:00

አባት ካለህ አጊጥ ጀምበር ካለች ሩጥ

Written by 
Rate this item
(6 votes)

 አባት እና እናት ልጃቸውን ይድሩና ልጃቸው “ሙሽሪት ልመጂ” ተብላ ባሏ ቤት ከርማ፣ እናት አባቷን ለመጠየቅ ወደ ወላጆቿ ቤት ትመጣለች፡፡ ከዚያም ከእናቷ ጋር የሴት - የሴት ነገር ትጫወታለች፡፡
እናት - አንቺ ልጅ
ልጅ - እመት እማዬ
እናት - እንደው ዝም ዝም አልሽ’ኮ! የገንፎ እህል ማዘጋጀት አለ… ጌሾ ማዘጋጀትና ማስወቀጥ አለ፡፡ ከዚያ ድግሱን ማደራጀት አለ፡፡ ኋላ “ሠርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ” ሆነ እንዳንባል… ከወዲሁ ፈሩን ብናስይዘው ይበጀናል፡፡ እንዲያው እንዲያው፤ ለነገሩ ፀንሰሽ ይሆን?
ልጅ - እማዬ፤ እኔ ምኑን አውቄው?
እናት - ለምንድን ነው ‹‹እኔ ምን አውቄው›› የምትይው?
ልጅ - እማዬ፤ አንቺ አብረሺኝ ስለማታድሪ ነው፡፡ በየቀኑ ይጨምርበታል’ኮ!
እናት- በመጀመርያ የወር - አበባሽ ያቆመበትን ጊዜ አታውቂውም ማለት ነው?
ልጅ - ገና ወር መች ሞላኝ?
እናት - በይ አዳምጪው - ማዳመጥ ነው የዚህ አገር ችግር፡፡
***
አገራችን ኢትዮጵያ ታላቅ ችግር ላይ ናት፡፡ ምናልባት ስለ “አዝማሪና ውሃ ሙላት” ያላነበባችሁ ካላችሁ ችግሩ ያን መሳይ ነው፡፡
አዝማሪና ውሃ ሙላት
አንድ ቀን አንድ ሰው
ሲሄድ በመንገድ
የወንዝ ውሃ ሞልቶ ደፍርሶ ሲወርድ
እዚያው እወንዙ ዳር እያለ ጎርደድ
አንድ አዝማሪ አገኘ ሲዘፍን አምርሮ
በሚያሳዝን ዜማ ድምፁን አሳምሮ
ምነው አቶ አዝማሪ ምን ትሠራለህ
ብሎ ቢጠይቀው
ምነዋ ሰውዬ ምን ሁን ትላለህ
አላሻግር ብሎኝ የውሃ ሙላት
እያሞጋገስኩት በግጥም ብዛት
ሆዱን አራርቶልኝ፣ ቢያሻግረኝ ብዬ፤
አሁን ገና ሞኝ ሆንክ ምነዋ ሰውዬ
ነገሩስ ባልከፋ ውሃውን ማወደስ
ግን እንደዚህ ፈጥኖ በችኮላ ሲፈስ
ምን ይሰማኝ ብለህ ትደክማለህ ከቶ
ድምፁን እያሽካካ መገስገሱን ትቶ
እስኪ ተመልከተው ይህ አውራረድ
ያልሰማው ሲመጣ የሰማው ሲሄድ

ተግሳፅም ለፀባይ ካልሆነው አራሚ
መናገር ከንቱ ነው ካልተገኘ ሰሚ
* * *
ኢትዮጵያ ትናገራለች፤ የሚሰማ ግን የለም፡፡ ወላጅ ይናገራል፤ ልጅ ግን አያዳምጥም፡፡ ወላጅ ባለበት ሰዓት፤ ልጅ የነቃና የተጋ አዕምሮ ያስፈልገዋል፡፡ ወላጅ የልጅ ትልቁ ዐይኑ ነው፡፡ አርቆ ማስተዋያው ነው፡፡ አባት ካለህ አጊጥ፤ ጀምበር ካለች ሩጥ የሚባለው ለዚሁ ነው፡፡  

Read 7485 times