Saturday, 03 August 2019 14:27

የ7ኛው “የበጎ ሰው” ሽልማት የመጨረሻዎቹ እጩዎች ይፋ ሆኑ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)


                        ዘንድሮ በ9 ዘርፍና በልዩ ተሸላሚ ዘርፍ ሽልማት ይሰጣል አርቲስት ታማኝ በየነ፣ አቶ ኦቦንግ ሜቶና ዶ/ር ፀጋዬ ታደሰ በዳያስፖራ ዘርፍ ታጭተዋል\

 
             የሰባተኛው “የበጎ ሰው” ሽልማት የመጨረሻዎቹ እጩዎች ይፋ ሆኑ፡፡ ከትናንት በስቲያ ሐሙስ ከሰዓት በኋላ “የበጎ ሰው” ሽልማት አዘጋጆች በኢንተርኮንትኔታል ሆቴል በሰጡት መግለጫ “የበጎ ሰው ሽልማት” ከ2005 ጀምሮ እስከ ዛሬ በተለያዩ ዘርፎች፣ ከፍተኛ ማህበራዊ አገልግሎት የሰጡ ግለሰቦችንና ተቋማት ሲሸልምና ሲያበረታታ የቆየ ቢሆንም በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ሳይመዘገብ መቆየቱ የተገለፀ ሲሆን ዘንድሮ ግን የምዝገባ የምስክር ወረቀት አግኝቶ በተቋም ደረጃ መዋቀሩን የሽልማቱ አዘጋጆች አስታውቀዋል፡፡
የዘንድሮ ሽልማትም በ9 ዘርፎችና በአንድ ልዩ ተሸላሚ ዘርፍ ሽልማት የሚሰጥ ሲሆን ከየዘርፉ ለመጨረሻ ዙር ያለፉ ሶስት ሶስት ዕጩዎች ይፋ ሆነዋል፡፡ በዚህም መሰረት በትምህርት ዘርፍ ፕ/ር ሽታዬ ዓለሙ፣ ወ/ሮ ሕይወት ወልደ መስቀልና ዶ/ር መስከረም ለቺሳ ለመጨረሻው ዙር ሲያልፉ በሳይንስ ዘርፍ (በህክምና፣ ቴክኖሎጂ፣ ፊዚክስ፣ ምህንድስና ኬሚስትሪና አርክቴክቸር) ፕ/ር ለገሰ ነጋሽ፣ ፕ/ር ሰብስቤ ደምሴና ዶ/ር ታደለች አቶምሳ አልፈዋል፡። በኪነ ጥበብ (ስነ ጥበብና በፎቶግራፍ ዘርፍ) አቶ ሚካኤል ፀጋዬ፣ በዛብህ አብተውና ዳኜ አበራ ሲታጩ፤ በበጎ አድራጎት (እርዳታና ሰብአዊ አገልግሎት ዘርፍ) ዶ/ር ጀምበር ተረፈ፣ ዶ/ር አብዱላዚዝ መሐመድና አቶ ሳሌ ላቡኮ እንዲሁም በንግድና ሥራ ፈጠራ ዘርፍ ከተወዳደሩት ውስጥ የዳን ቴክኖክራፍት ቴክኖሎጂ ባለቤት አቶ ዳንኤል መብራቱ፣ የኢንሼቲቭ አፍሪካ መስራች አቶ ክቡር ገናና የነጋ ቦንገር ሆቴል ባለቤት አቶ ነጋ ቦንገር ለመጨረሻው ዙር አልፈዋል። በመንግስታዊ የስራ ተቋማት ሀላፊነት ዘርፍ ለውድድር ከቀረቡት መካከል አቶ በድሩ አድማሴ፣ የኢፌዲሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሚኒስትር፣ ዶ/ር አሚር አማና አቶ ግርማ ወንዳፍራሽ ሲያልፉ በቅርስና ባህል ዘርፍ የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦችን የባህላዊ ዳኝነትና የፍትህ ሥርዓቶችን በመጻፍ የሚታወቁት አቶ አብዱል ፈታህ አብደላ፣ በምስራቅ ጎጃም ዞን በጮቄ ተራራ አካባቢ የሚገኘውን ‹‹አባ ጃሜህ›› ደን ለ52 ዓመታት በግል ተነሳሽነት ሲጠብቁና ሲንከባከቡ የነበሩት አዛውንቱ አርሶ አደር አቶ አድማሴ መላኩና አቶ ሳሙኤል መኮንን ለመጨረሻው ዙር ማለፋቸው የተገለፀ ሲሆን፤ በሚዲያና ጋዜጠኝነት ዘርፍ የሪፖርተር ጋዜጣ አሳታሚ ድርጅት (MCC) መስራችና ባለቤት አቶ አማረ አረጋዊ፣ በኢቢኤስ የሚተላለፈውና በልጆች ፕሮግራም ላይ የሚያተኩረው›› ‹‹ኢትዮጵስ›› አዘጋጅ ወ/ሮ አንድነት አማረና አቶ በልሁ ተረፈ እጩ ሆነዋል፡፡ ለኢትዮጵያ እድገት አስተዋጽኦ ያበረከቱ ዲያስፖራዎች በሚለው ዘርፍ አርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ፣ አቶ ኦቦንግ ሜቶና ዶ/ር ፀጋዬ ታደሰ ለመጨረሻው ዙር አልፈዋል፡፡ በማህበራዊ ጥናት ዘርፍ በቂ እጩ ባለመቅረቡ የዘርፉ ተሸላሚ እንደማይኖር አዘጋጆቹ የገለፁ ሲሆን፤ በልዩ ተሸላሚ ዘርፍ የሚሸለመው ግለሰብ በሽልማት ሥነስርዓቱ ዕለት  ይፋ እንደሚሆን ተጠቁሟል፡፡
የሰባተኛው ዙር የሽልማት ሥነ-ሥርዓት ነሐሴ 26 ቀን 2011 ዓ.ም ከቀኑ 8፡00 ጀምሮ በኢንተርኮንትኔታል ሆቴል በድምቀት እንደሚካሄድም ታውቋል፡፡  


Read 9937 times