Saturday, 03 August 2019 14:29

‹‹ኑሮ MAP›› የዶ/ር ኤርሲዶ መጽሐፍ ገበያ ላይ ዋለ

Written by 
Rate this item
(7 votes)

ከአገር ህልውናና ስልጣኔ እስከ ትርምስና ኋላቀርነት፣ ከኢኮኖሚና ከፖለቲካ ጀምሮ እስከ ልጆች ትምህርትና እድገት፣ ከወጣቶች ፍቅርና የስራ ዓለም እስከ ስነ ምግባር መርሆች ድረስ… በአዲስ አስተሳሰብ የሚዳስስ መጽሐፍ እንደሆነ ዶ/ር ኤርሲዶ ለንደቦ ይገልጻሉ፡፡ የአእምሮ፣ የሃሳብና የንግግር ነፃነት ያስፈልጋል፡፡ ግን፣ አእምሮን ሳይጠቀሙ ሳያስቡ ለመናገር ከሆነ አይዘልቅም:: መባላት ይሆናል፡፡ ልጆችን ነፃ አድርጐ ማሳደግ ሲባል ህፃናትን አለመደብደብና አለማሰቃየት ማለት ብቻ አይደለም፡፡ በእውቀትና በስነምግባር ለመኖር ነው - ነ መሆን፡፡ መረን ማለት አይደለም:: ነፃነት ለኑሮ ያስፈልጋል፡፡ ግን በነፃ መብላት ማለት አይደም:: ሰርቶ፣ ተገበያይቶ፣ በችግር ጊዜ የፈቃደኝነት እገዛ ተጨምሮበት መኖር ማለት ነው፡፡ አለበለዚያ በነፃ ለመብላት መስረቅና መዝረፍ ይሆናል (ፀረ - ነፃነት)::
የራስን ህይወት በነፃነት መምራትም፣ ከግል ኃላፊነት ከተነጠለ፣ ነፃነትንም ህይወትንም የሚያሳጣ እንደሚሆን በየእለቱና በየአካባቢው እያየነው ነው፡፡  
እውነተኛ መረጃዎችን አሟልቶ ማገናዘብ የሚችል ትክክለኛ አስተሳሰብ፣ ገና ከጅምሩ ችግሮች አስቀድሞ ለማወቅ ብቻ ሳይሆን መፍትሄ ለማበጀት እንደሚያገለግል ለማስረዳት ዶ/ር ኤርሲዶ ምሳሌ ይጠቅሳሉ፡፡ ስኳር ኮርፖሬሽንና ሌሎች በርካታ የመንግስት ፕሮጀክቶች በከፍተኛ ኪሳራ ውድቀት እንደሚገጥማቸው ገና ከ2005 ዓ.ም በፊት ማወቅና ማስተካከል ይቻል እንደነበር፤ ይህንንም ዛሬ ሳይሆን ያኔ  ለማስረዳት መሞከራቸውን ተናግረዋል፡፡
ብዙ ሚሊዮን ብር ሳይባክን በፊት መፍትሔውን በመጽሐፉ ውስጥ ከ6 ዓመት በፊት እንዳካተቱ ጠቅሰው፤ ቢዘገይም ዛሬም ቢሆን መፍትሔውን ለመተግበር እየተሞከረ መሆኑ ጥሩ ነው ብለዋል፡፡
እኔ የሌለው “እኛ”፣ የግል ድርሻ የሌለው “የጋራ”፣ ከሃላፊነት ለማምለጥ ቢገለገሉበትም፣ መቼም ቢሆን ከችግርና ከመዘዝ አያመልጥም ነው ነገሩ:: የመንግስት ቢዝነስ አብዛኛውን ጊዜ በብክነትና በሙስና አገርን የሚያከስረው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ የግል ነፃነት ከግል ኃላፊነት ተነጥሎ ሳይሆን ተጣምሮ ካልታሰበ፣ አሁን እንደምናየው፣ በብሔር ብሔረሰብ በመቧደን ከግል ሃላፊነት ለማምለጥ የሚሞክሩ ሰዎች፣ ነፃነትን ያጠፋሉ፤ በየቦታውና በየሰበቡ በሚፈጥሩት ረብሻ የሰው ሕይወትና ንብረት  ሲጠፋ እናያለን፡፡ ይህን የምለው ዛሬ አይደለም፡፡  የአገራችን ዩኒቨርሲቲዎች፣ የትምህርት ማዕከልነታቸው ሲዘጋ፣ የግል ኃላፊነትን የሚሸረሽር የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ ሲስፋፋ፣ የሁለት ተማሪዎች አምባጓሮን ወደ ዘረኝነት ጥፋት የሚለውጡ  የረብሻና የብጥብጥ መናኸሪያ እንዳይሆኑ ከ6 ዓመት በፊት በመጽሐፉ ውስጥ ትንታኔ ማቅረባቸውን ዶ/ር ኤርሲዶ ጠቅሰዋል፡፡
መጽሐፉ በአዲስ ሕትመት ሰሞኑን ለገበያ እንደቀረበ የገለፁት ዶ/ር ኤርሲዶ ለንደቦ፤ ተወዳጅነትን ያተረፈ “የልጆቻችንን ኢትዮጵያ” የተሰኘ ሳምንታዊ የሬዲዮ ፕሮግራም እያዘጋጁ ዘወትር እሁድ ጠዋት ከ3-4፡30 በማቅረብ ይታወቃሉ፡፡ በ204 ገፆች የተቀነበበው “ኑሮ Map”፤ በ120 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡

Read 11031 times