Saturday, 03 August 2019 14:28

“ጥቁር ሽታ” ዛሬ ለንባብ በቅቷል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(4 votes)

 በደራሲና ገጣሚ መሃመድ ነስሩ (ሶፎንያስ አቢስ) የተጻፈው “ጥቁር ሽታ” የአጫጭር  ልቦለዶች ስብስብ መጽሐፍ ዛሬ ማለዳ ለንባብ የበቃ ሲሆን፣ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ለገበያ ቀርቧል፡፡
በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ አጫጭር ልቦለዶችን ያካተተውና በ203 ገጾች የተቀነበበው “ጥቁር ሽታ”፤ የመሸጫ ዋጋው 120 ብር ሲሆን በመጽሐፍት መደብሮችና በአዟሪዎች እየተሸጠ እንደሚገኝ ደራሲው በተለይ ለአዲስ አድማስ ገልጧል፡፡
በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ለረጅም አመታት በስሙና ሶፎንያስ አቢስ በተሰኘው የብዕር ስሙ የተለያዩ መጣጥፎችን፣ ልቦለዶችንና ወጎችን ለንባብ ያበቃው ወጣቱ ደራሲና ገጣሚ መሃመድ ነስሩ፤ ከዚህ በተጨማሪም መዝናኛ፣ አዲስ ነገርና ፍትህን ጨምሮ በተለያዩ ጋዜጦችና መጽሄቶች ላይ ጥልቅ ሃሳቦችን ያዘሉ ጽሁፎቹን ለአንባብያን ሲያደርስ የቆየ ሲሆን አሁንም በፍትህ መጽሔት በአምደኝነት እየጻፈ ይገኛል፡፡
ደራሲ መሃመድ ነስሩ፤ ከዚህ ቀደምም በሳል ግጥሞች የተካተተበትንና የመጀመሪያ ስራው የሆነውን “አሌፋት” የተሰኘ የግጥም መድበል ለንባብ ያበቃ ሲሆን በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የተማሪነት ቆይታውም መቅረዝ በተባለው የኪነጥበብ ቡድን ውስጥ ደማቅ ተሳትፎ ከሚያደርጉና ተወዳጅ ከነበሩ የስነጽሁፍ ሰዎች አንዱ እንደነበር  ይነገራል፡፡

Read 9912 times Last modified on Saturday, 03 August 2019 14:35