Saturday, 03 August 2019 14:24

የአለማየሁ ገላጋይ 13ኛ መጽሐፍ ለገበያ ቀረበ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 የእውቁ ደራሲና ሀያሲ አለማየሁ ገላጋይ 13ኛ ሥራ የሆነው ‹‹ውልብታ›› የተሰኘ መጽሐፍ ከትላንት በስቲያ ጀምሮ ለንባብ በቃ፡፡ መጽሐፉ በአይነትና በይዘቱ ከሌሎቹ የደራሲው መጽሐፍት የተለየ ሲሆን ከ10 ቃላት ታሪክ እስከ 17 ገጽ ያሉ የአጭር አጭር ታሪኮችን (Post card stories) የያዘ ነው፡፡
‹‹ውልብታ” ይህን የአፃፃፍ ስልት ተከትሎ የተጻፈ የመጀመሪያው መጽሐፍ ሳይሆን እንደማይቀርም ተጠቁሟል፡፡
‹‹…ቀደም ሲል ከሀያሲ አብደላ ዕዝራ ጋር ስንወያይ፣ አንድ እቅድ እንደነበረው አጫወተኝ:: ‹‹Postcard stories›› በፖስት ካርድ ጀርባ ላይ ተጽፎ የሚያልቅ /የአጭር አጭር ልቦለድ) መድበል የማሳተም ፍላጎት እንዳለው ነገረኝና ‹‹አንተም ይሄንን የሥነ ጽሑፍ ዘርፍ ብትሞክረው የሚሳካልህ ይመስለኛል፡፡
ከማስረዘም ይልቅ የማሳጠር ችሎታህ ገነን ያለ ነው አለኝ፡፡” በማለት ከዚያን ጊዜ አንስቶ ይህን አይነት አጻጻፍ ሲያስስ ኖሮ፣ ዛሬ እውን ማድረጉን በማስታወሻው ላይ አስፍሯል ደራሲ አለማየሁ ገላጋይ፡፡ ከ70 በላይ ታሪኮችን ያካተተውና በ160 ገፆች የተቀነበበው መጽሐፉ፤ በ71 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡
ደራሲው ከዚህ ቀደም ‹‹ቅበላ››፣ ‹‹የፍልስፍና አጽናፍ››፣ ‹‹ኢህአዴግን እከሳለሁ››፣ ‹‹የብርሃን ፈለጎች›› ‹‹ወሪሳ››፣ ‹‹አጥቢያ››፣ ‹‹ስብሃት ገ/እግዚአብሄር ሕይወትና ክህሎት፣ ‹‹ኩርቢት››፣ ‹‹መልከአ ስብሃት››፣ ‹‹መለያየት ሞት ነው›› እና ‹‹ታለ በዕውነት ስም›› የተሰኙ መጽሐፍትን ለንባብ ማብቃቱ አይዘነጋም፡፡


Read 2784 times