Print this page
Saturday, 03 August 2019 14:01

“ክልል ማቋቋም” በህገመንግስት ይፈቀዳል? ለዚያ ለዚያማ “መገንጠል” ተፈቅዷልኮ!

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(2 votes)


            - ከትዳር ክርክርና ከፍቺ፣ “መገንጠል” ይቀልላል፡፡
           - መገንጠል 3 ዓመት አይፈጅም፡፡ አገርን ያፋጃል እንጂ፡፡
           - “ክልል ለማቋቋም”፣ “ለመገንጠል”፣ ምርጫ የሚዘጋጀው ለማን ነው?
          - በዘር በተወላጅነት ነው? ወይስ የአካባቢው ነዋሪዎች ድምጽ እንዲሰጡ?
                     

           በቀላሉ የማይለወጥና የማይከለስ ህገመንግስት፣ ለአገር ሰላምና ህልውና፣ ለሰዎች ህይወትና ኑሮ ስለሚጠቅም እንጂ፣ ለድርቅና ተብሎ የሚጫን ሸክም አይደለም፡፡ በአንድ ሰው ትዕዛዝ ወይም በህዝብ ተለዋዋጭ ሆይሆይታ ከመገዛት ነፃ የሚይወጣ፣ ለህግ ተገዢ የሆነ፣ የተረጋጋ፣ ሰላማዊና ዘላቂ ስርዓት ነው፤ ትክክለኛው ስልጡን ስርዓት፡፡ በቀላሉ የማይከለስ ህገመንግስት ለዚህ ያገለግላል፡፡
በየቀኑ ፓርላማ በሚያወጣው አዋጅ፣ በየእለቱ እየፈረሰ በየሳልስቱ የሚገነባ አገር፣ በምናብ ዓለም ውስጥ ካልሆነ በቀር፣ በእውኑ ዓለም ውስጥ፣ “አገር” ሆኖ የመሰንበት እድል የለውም፡፡
የአንድ ዞን ምክር ቤት ውሳኔ፣ አልያም በየሳምንቱና በየወሩ እየተከታተሉ ከ10 ዞኖች በሚመጡ ውሳኔዎች፣ ወይም ከዓመት ዓመት እዚህኛውና እዚያኛው ክልል በሚካሄዱ “የውሳኔ ህዝብ” ምርጫዎች አማካኝነት፣ እንደ ክረምትና በጋ፣ በፈረቃ የሚበተንና የሚፈጠር አገር፣ ያለጥርጥር ከ “አገር” ዝርዝር ለመጥፋት የቆረጠና የቸኮለ መሆን አለበት፡፡
በየአምስት ዓመቱ በሚካሄድ ምርጫ ላይ፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እየተወዳደሩና እየተፈራረቁ ስልጣን የሚይዙበት ሰላማዊ ስርዓት መልካም የሚሆነው፤ በህግ የበላይነት ስር የሚከናወን ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ማናቸውም ፓርቲ፣ የእያንዳንዱን ሰው መብት የማስከበር እንጂ የመጣስ ስልጣን እንዳይኖራቸው የሚከለክል፣ እንዳሻቸው የማይቀይሩትና የማይከልሱት ህገመንግስት ሲኖር፣ ለህግ ተገዢ የሆነ ስርዓትና አገር ሲኖር ነው - የፓርቲዎች ምርጫ ፋይዳ የሚኖረው፡፡
በተቃራኒውስ? የመጀመሪያው ፓርቲ ሲያሸንፍ፣ “አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ” ለማጠናከር የሚሰራ፣ ሌላኛው ፓርቲ ሲያሸንፍ ደግሞ አገሬውን ሁለት ቦታ መገንጠል ወይም 12 ቦታ ገነጣጥሎ ማፍረስ የሚችል ከሆነስ? ይሄ፣ ህገመንግስትን መለወጥ ወይም መከለስ ሳይሆን፣ በህገመንግስት መጫወት ነው፡፡ አዲስ ክልል ሲፈጠር ወይም ሲገነጠል፣ በዚያው ልክ ህገመንግስት ይለወጣል፡፡ በዚያው ልክ፣ ሁሌም ተለዋጭ አገር ይኖረናል ብሎ ማሰብ ግን ሞኝነት ነው፡፡
ታዲያ፣ “መገንጠል” የሚሉት ፈሊጥ፣ እንደ ቀላል ጉዳይ መቆጠሩ፣ ሦስት ዓመት የማይፈጅ፣ በአንድ የምክር ቤት ስብሰባና በአንድ ምርጫ የሚያልቅ ሆኖ ህገመንግስት ውስጥ መስፈሩ አይገርምም?
“መገንጠል” እና መዘዙ፣ የሩቅ ስጋት ከመሰለን፣ ተሳስተናል፡፡ “ክልል ማቋቋም”፣ የሩቅ ጉዳይ ነው እንዴ? አይደለም፡፡ የዛሬ ጉዳይ ነው፡፡ ለ10 ዞኖች የመጣ የጉዳይ ጐርፍ በሉት፡፡
“መገንጠል”፣ ከዚህ ብዙም አይለይም፡፡
ክልል ማቋቋም እና መገንጠል በህገመንግስት ውስጥ የተሰጣቸው ቦታ ተመሳሳይ ነው፡፡ አንድ ዓመት የመጠበቅና ሦስት ዓመት የመጠበቅ ጉዳይ ነው ልዩነታቸው፡፡
ለምሳሌ የሲዳማ ዞን፣ አዲስ ክልል ለማቋቋም ያስተላለፈው ውሳኔ፣ ተግባራዊ ለመሆን፣ ብዙ ፈተና አይገጥመውም፡፡ ምርጫ ተዘጋጅቶ 51% ያህል የድጋፍ ድምጽ ካገኘ፣ በቃ፣ ተግባራዊ ይሆናል፡፡
የዚህን ያህል ቀላል ነው፡፡ በዚያ ላይ ጊዜ አይፈጅም፡፡ ምርጫው በአንድ ዓመት ውስጥ መዘጋጀት እንዳለበት በህገመንግስት ተጽፏል፡፡
ለመገንጠልም፣ ጊዜ አይፈጅም፡፡ የዞን ወይም የክልል መስተዳድር ለመገንጠል ከወሰነ፣ በሦስት ዓመት ውስጥ ምርጫ መካሄድ አለበት ይላል - ሕገ መንግስቱ፡፡
በምርጫ ቦርድ የሕግ አተረጓጎም ብንሄድ እንኳን፣ ክልል የማቋቋም ውሳኔ፣ በምክር ቤት በኩል ወደ ምርጫ ቦርድ ለመድረስ ከአንድ ዓመት በላይ መዘግየት የለበትም፡፡ ቦርዱ በተራው ምርጫ ለማዘጋጀት ከአንድ ዓመት በላይ መዘግየት የለበትም፡። በአጠቃላይ፣ ነገርዮው ከሁለት ዓመት በላይ አይፈጅም፡። ለመገንጠልም፣ ስድስት ዓመት በቂ ነው - በዚህ የህግ አተረጓጐም፡፡
ቀለል ያለ የፍርድ ቤት ክርክር፣ ከሁለት ዓመት በላይ ይጓተታል፡፡ ለምርመራ በርካታ ወራት፣ ክስ ለማዘጋጀትና ምስክር ለማሰማት፣ ብይን ለመስጠት፣ መከላከያ ለማቅረብና ለመከራከር፣… ውሳኔና ፍርድ ለመስጠት… ከዚያ በኋላ ደግሞ ለአፈጻጸም፣.. ጣጣው ብዙ ነው፡፡ ነገር ግን ሕግ እንዲከበር፣ ፍትህ እንዲፈጸም ከተፈለገ፣ ህጋዊ ስርዓትን የተከተለ መንገድ ያስፈልጋል (due process እንዲሉ)፡፡ በተቻለ መጠን የፍትህና የዳኝነት አሰራሮችን ማቀላጠፍ የማስፈለጉ ያህል፣ ሕጋዊ ስርዓትን ያሟሉ መሆን ስላለባቸው ጊዜ መውሰዳቸው የግድ ነው፡፡
ቀለል ያለ የሰራተኛና የአሰሪ፣ የአበዳሪና የተበዳሪ፣ የባልና የሚስት የፍርድ ክርክር፣ በሁለት ዓመት ውስጥ ውሳኔ ቢያገኝ፣ ነገሩ እልባት አገኘ ማለት አይደለም፡፡ በይግባኝ ክርክሩ ሲቀጥል.. ወራትና ዓመታት፣ ከዚያም የይግባኝ ይግባኝ ተብሎ ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እየዘለቀ፣ ጉዳዩ አስር ዓመት ሊፈጅ ይችላል፡፡ የይግባኝ አቤቱታና ዳኝነት ያለምክንያት ጊዜ ለማጓተት የተፈጠሩ አሰራሮች አይደሉም፡፡ ህግ ያለ ስህተት በትክክል እንዲከበር፣ ያለ ጥርጥር በአስማማኝ ፍትህ እንዲፈጸም የሚጠቅሙ፣ የሕህጋዊ ስርዓት አካል ናቸው፡፡
ከባልና ሚስት ፍቺ፣ ከአሰሪና ሰራተኛ ውዝግብ፣ ከሁለት ሸሪኮች ወይም ከባለአክሲዮኖች ክርክር፣ ይልቅ  መገንጠል ይቀላል፡፡
‹‹መገንጠል››ን እንዲህ አቅልሎ የሚያይ የሕገ መንግስት አንቀጽ፣ ለአገር ህልውናም፣ ለሰዎች ህይወትም አይበጅም፡፡ አደገኛ ስህተት ነው፡፡ እናም መስተካከል አለበት፡፡ ነገር ግን ህገመንግስት በቀላሉና እንደዋዛ እንዲከለስ መመኘት፣ ሌላ ከባድ ስህተት ነው፡፡ ህገመንግስት ነጋ ጠባ በቀላሉ የሚከለስ ከሆነ፣ ለማስተካከል ብቻ ሳይሆን ለማበላሸትም ቀላል ይሆናል፡፡
በጣም ተበላሽቶ አገር ከፈረሰ በኋላ፣ እንደገና ተመልሶ ለማስተካከል፣ ተጨማሪ እድል ላይገኝ ይችላል፡፡  
ስለዚህ፣ የተሳሳቱና የተበላሹ አንቀፆችን ለማስተካከል መወትወትና መጣር የሚኖርብን፣ የሕገ መንግስትን ጽናት ሳንሸረሽር መሆን አለበት፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡ ‹‹መገንጠል›› ለሚለው አንቀጽ መነሻ የሆኑ፣ የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካንና የዘረኝነት አስተሳሰብን ለማስወገድ መጣር አለብን፡። ይሄ ደግሞ በአዋጅና በውሳኔ የሚሆን አይደለም፡፡ ትክክለኛና ስልጡን አስተሳሰብን በማቅረብ እንጂ፡፡

Read 1421 times